ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ወቅቱ ኮቪድ 19 የተባለ አደገኛ በሽታ በዓለም ላይ ተሰራጭቶ የሚገኝበት ወቅት በመሆኑ፣ ይህንን ታላቅ በዓል ከሌላው በተለየ ሁኔታ እንድናከብረው ተገደናል።
ስለረመዳን ስናወሳ ብዙ ነገሮችን ማስታወስ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።
አንደኛ፣ በዓሉ የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶቻችንን አብረን የምንፈትሽበት መልካም አጋጣሚ ነው። ታሪካችንን ወደኋላ መለስ ብለን ካየን፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለዓለም ካበረከቱት ታላላቅ ሥራዎች መካከል ለእስልምና እምነት ልደትና ዕድገት ያደረጉት አስተዋፅኦ በዋነኛነት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነው።
የእስልምና እምነት በነቢዩ መሐመድ አስተምሮ እየጠነከረ፣ ተከታዮቻቸውም እየበረከቱ ሲሄዱ ያዩት አብዛኞቹ የትውልድ አገራቸው ሰዎች የማጥፋት ርምጃ ሲወስዱ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ግንየነቢዩን ቤተሰብ ፣ ባልንጀሮቻቸውንና ተከታዮቻቸውን ተቀብላ መጠጊያ ሰጥታ፣ በማስተናገድ የእምነቱን ደጋፊዎች ከተደቀነባቸው የሞት አደጋ አድና በሕይወት አቆይታለች። ሊያጠፏቸው ሲሉ ተከታትለውዋቸው የመጡት ጦረኞች ፣ በርካታ የእጅ መንሻ ፣ እንዲሁም የወርቅና ሌሎች የተለያዩ ውድ ስጦታዎች በመስጠት ጥገኞቹን አሳልፎ እንዲሰጣቸው አጥብቀው ቢጠይቁም እምቢ ከማለት ዐልፎ፣ጥገኞቹ በኢትዮጵያ ምድር እስካሉ ድረስ ማንም ሳይነካቸው በእምነታቸው ጸንተው መቀጠል እንደሚችሉ አረጋግጦላቸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ነቢዩ እንዳሉላት፣ የፍትህና የርትዕ፣ ማንም በእምነቱ የማይሰደድበት ነፃ አገር መሆኗን አስመሰክራለች።
ሕዝባችንም ማንንም በእምነቱና በዘሩ ሳይለይ ከፍተኛ አስተናጋጅና ተወዳጅ መሆኑን ለነቢዩ ስደተኞች ባሳየው እንክብካቤና ፍቅር አሳይቷል። ነቢዩ መሐመድ በመጀመሪያው ሂጂራ ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ሲልኳቸው፣“ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ!” ሲሉ፣ ይኸንን የሕዝባችንን ልበሰፊነትና እንግዳ አፍቃሪነት በመረዳት መሆኑ አያጠራጥርም።
ረመዳንን የመሰለ ታላቅ በዓል በምናከብርበት ሰዓት፣ ከፊታችን የሚደቀን የታሪክ መጻሕፍት የሚተርኩልን ነገር ቢኖር፣ ይህንን ዐይነቱን የተስፋ ስንቅ የሰነቁ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የገጠማቸዉ ፍርሃት ሳይሆን ደስታና እፎይታ ነበር ።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ከመካ ነዋሪዎች መካከል በቅድሚያ እስልምናን የተቀበለና የነቢዩም ቀዳሚ ተከታይ እንደሆነ የሚነገርለት ቢላል ኢትዮጵያዊ ነበር። በነቢዩ መሐመድ ከመላው ዓለም አገራት መካከል፣ “አትንኩዋት የተባለላት ሀገርም ኢትዮጵያ ብቻ ነች” ።
ሁለተኛ፣ ከታሪክ ባሻገር፣ረመዳን ያለንን ተካፍሎ የመብላት ፣ ለደሀ ወይም ለሌለው የማካፈል፣የመስጠት፣ ወንድም ወንድሙን የሚደግፍበት ጊዜ ነው፣ ረመዳን ከምግብና ከመጠጥ ተርቆ ሥጋን በድሎ ወደ አላህ/ፈጣሪ የሚጸልይበት ወቅት ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን በመስቀልኛ መንገድ እንዳለች ብዙዎቻችን እንደምናምን አይካድም።
በዚህ በረመዳን በዓል ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ትብብር ለፍትኅ የእስልምናንም ሆነ የክርስትናን እምነት ተከታይ ሁሉ፣ ዘመናት ያስቆጠረውን የመተሳሰብና የመደጋገፍ ብሎም አብሮነታችንን አጠናክረን የምንሄድበት ወቅት መሆኑን በሚገባ መመርመር ይኖርብናል በማለት ዓለም ዐቀፍ የኢትዮጵያውያን ትብብር ለፍትኅ ጥሪውን ያቀርባል።
በመጨረሻም በሚቀጥለው ዓመት ይህ አስከፊ ኮቪድ 19 በሽታ ተወግዶ፣
በሀገራችን ኢትዮጵያ ፍትኅና የሕግ የበላይነት ተከብሮ፣
የታገቱት ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሕይወት ተለቀው፣
በስደት የሚንገላቱ ኢትዮጵያውያን ወደ ቅድስት ሀገራችው ተመልሰው እንድናይ እንዲያበቃን፣
ሁላችንም እንደየእምነታችን ምስጋና የምናቀርብበት እንዲሆን ዓለም ዐቀፍ የኢትዮጵያውያን ትብብር ለፍትኅ መልካም ምኞቱን በአክብሮት እየገለጸ እንኳንም ለታላቁ የረመዳን / ኢድ ሙባረክ በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለ መልካም ምኞቱን ይገልጻል ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ፣
ኢድ ሙባረክ!
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ትብብር ለፍትኅ