በመከበር ላይ ያለውን የ1442ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ግንቦት 4, 2013 ባስተላለፉት መልዕክት ከበዓሉ ታላቅነት ጋር አሰናስለው ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የዘንድሮውን ዒድ አል ፈጥር የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እያስታወስን ነው። ክፉውን ጊዜ እንደ ዒድ ሶላት ሰብሰብ ብለን ልንጋፈጠው፣ የአንድነታችንን ልክ አሳይተን ልናልፍ ይገባል። በኅብረታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች እንደ ምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን እድል በእኛው እንጂ በሌላ በማንም እጅ እንዳልሆነ ለዓለም ማሳየት ይኖርብናል” ሲሉ በመልዕክታቸው ላይ አፅንዖት ሰጥተዋሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ገጥመው ላሉት ፈተናዎች ዋነኛ አስባብ ያሏቸውን ሁለት ዐበይት ምክንያቶች ሲያስገነዘቡም “በሕዳሴ ግድብ እና ከፊታችን ባለው ምርጫ ምክንያት ሀገራችን ፈተናዎቿ በዝተው አይተናል። እነዚህ ሁለቱን ማሳካት ለእኛ ቀላል የማይባል የስኬት በሮችን እንደሚከፍቱልን እናውቃለን። ምርጫውን በስኬት ማከናወን አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ እንደሚከፍትልን ግልጽ ነው። የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅም ግዙፍ የብልጽግና ፋና እንደሚለኩስልን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያውቃል” ብለዋል።

Abiy Ahmed, Ethiopia's prime minister. Source: Getty
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በበኩላቸው በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “መልካም አጋጣሚዎችን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የኢፍጠር መርሃ ግብሮች ላይ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ማዕድ የተጋራንባቸው መድረኮች የአብሮነታችን ውሃ ልክ ትክክለኛ ማሳያዎች ነበሩ” በማለት መልካም ልባዊ መልዕክታቸውን ለሕዝበ ሙስሊሙ አስተላልፈዋል።
በሌላም በኩል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ በመላው ኢትዮጵያና በየክፍለ ዓለማቱ ለሚሀኙ ሙስሊሞች በሙሉ 1442ኛውን ኢድ አልፈጥር በሐሴት የተመላ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።
አክለውም ስለ ሰላም አስፈላጊነትና የአንድነትን ጠቀሜታ ልብ አሰኝተዋል። ለድሆች ማብላት፣ ሕመምተኞችን መጠየቅና ድሆችን መርዳት ሃይማኖታዊ ተግባራት መሆናቸውን አሳስበዋል።

Ethiopian deputy prime minister and Foreign Minister Demeke Mekonnen. Getty Source: Getty

Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council (EIASC) head Hajji Mufti Omar Idris. Source: Getty