የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር አጭር ቅኝት - ግርማ አውግቸው ደመቀ

*** የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከግሪጎሪያን ብቻ ሳይሆን በዘመን ‘ኢራ’ ረገድ ከቅብጥም ይለያል።

Ethiopian calanadar

Dr Girma Awgichew Demeke Source: Supplied

በኢትዮጵያ በርካታ አቆጣጠሮች አሉ። ከሲቪሉ አቆጣጠር በተጨማሪ፣ ባህላዊ እንዲሁም ከሀይማኖት ጋር የተያያዙ አቆጣጠሮች አሉ። በባህላዊ ረገድ የሲዳማውና በቦረና ኦሮሞ ዘንድ ያሉትን አቆጣጠሮች መጥቀስ ይቻላል።[1] ለኋለኛው ምሳሌ የእስልምናውን አቆጣጠር መጥቀስ ይቻላል። የእስልምና ተከታዩ ህዝብ የሀይማኖቱን በዓላት፣ አፅዋማትና ባጠቃላይ ከእስልምና ጋር የተያያዙ የእምነት ጉዳዮቹን የሚያከናውነው በእስልምናው አቆጣጠር ላይ ተመስርቶ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትናም አብዛኛው በዓላት በሲቪሉ አቆጣጠር ላይ ተመስርቶ የሚከበር ቢሆንም ተንቀሳቃሽ በዓላቱ የሚሰሉበት የተለየ ቀመር አለ። በዚህ ላይ ብዙ ስራዎች አሉና እነሱን ይመልከቱ። ለምሳሌ፣ በአማርኛ ከተፃፉት ውስጥ የሚከተሉትን ይመልከቱ፤ ጌታቸው ኃይሌ (2006) እና አለቃ ያሬድ (2004)። በእንግሊዝኛ ከተሰሩት ውስጥ ደግሞ ኒውጌባወርን (1964፣ 1979፣ 1988፣ 1989) ይመልከቱ። በዚህ ስራ የኢትዮጵያ አቆጣጠር ስንል ሌላ ተቀፅላ እስካላስገባንበት ድረስ፣ የሲቪል አቆጣጠሩን ማለታችን ነው።

ይህ መጣጥፍ ዘመን አቆጣጠር የቀናትና የወራት ስያሜ በሚል በግሪጎርያን አቆጣጠር 2016 በሬድ ሲ ፕረስ ካሳተምኩት መፅሀፍ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎበት የተወሰደ ነው። በዚህ መጣጥፍ ለጠቀስኳቸው ዋቢዎች ሙሉ መረጃ እና ለሰፊ ግንዛቤ መፅሀፉን ይመልከቱ። በዚህ ስራ የተሰጡት ዓመቶች በግልፅ ካልተጠቀሱ በስተቀር የግሪጎሪያኑን የሚመለከቱ ናቸው።

1. የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከቅብጥ አቆጣጠር ያለው ተመሳስሎ

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከቅብጥ/ግብፅ የተቀዳ ይመስላል። ይህ ጉዳይ በርግጥ ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ ነው። ምናልባት አዲስ የሚሆነው በጉዳዩ ላይ ትኩረት ላላደረገበት ሰው ብቻ ነው። ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በተለያዩ የግዕዝ ፅሁፉች መመሳሰሉ ከመገለፁም በላይ በዘመን አቆጣጠር ላይ የተሰሩ ስራዎችም በየግዜው ሲገልፁት ኖረዋል።[2] የኢትዮጵያ አቆጣጠር እንደቅብጡ/እስክንድርያው አቆጣጠር እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሉት 12 ወራትና 5 ተጨማሪ ቀናት በየሊፕ ዓመቱ ደግሞ 6 የምትሆን “ጳጉሜን” አለው።

በሁለቱም አቆጣጠሮች እንደወር አትቆጠርም። ጳጉሜን የሚለው ስያሜ በግዕዝም በአማርኛም ያው ነው። የአማርኛው ከግዕዙ የተወሰደ ነው። ቃሉ ከመሰረቱ የግሪክ ነው። በግሪክ ኤፓጎሜነስ[3] ‘ተጨማሪ’ ማለት ነው። እንግሊዝኛው ይህን ቃል ወርሶታል። በእንግሊዝኛ ኢፓጎሜነልዴይ[4] ‘ተጨማሪ ቀን’ ማለት ነው።

የግዕዝ ተናጋሪው በወቅቱ አለማቀፋዊ ቋንቋ ከነበረው ከግሪክ ጋር ግንኙነት ቢኖረውም፣ ጳጉሜን በቀጥታ ከግሪክ የወሰደው አይመስልም። ይልቁንም ቃሉ በቅብጥ በኩል የመጣ ይመስላል። ይህ ቃል በቅብጥ የወራት ስያሜ ውስጥም አለ። የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ወራቱ ከሚጀምርበት አንስቶ ከቅብጥ ጋር አንድ ነው። ከታች የቀረበውን ሠንጠረዥ  ይመልከቱ፤[5]

ሠንጠረዥ 1፡ የኢትዮጵያ አቆጣጠርና የቅብጥ አቆጣጠር[6]

ቅብጥ[7]

ግዕዝ

ግሪጎርያን

መደበኛ ዓመት

ሊፕ ዓመት/ዘመነ ዮሐንስ

ቶት

መስከረም

11 ሴፕቴምበር – 10 ኦክቶበር

12 ሴፕቴምበር – 11 ኦክቶበር

ፓኦፒ

ጥቅምት

11 ኦክቶበር – 9 ኖቨምበር

12 ኦክቶበር – 10 ኖቨምበር

አቱር

ኅዳር

10 ኖቨምበር – 9 ዲሴምበር

11 ኖቨምበር – 10 ዲሴምበር

ቻዮክ

ታኅሳስ

10 ዲሴምበር – 8 ጃንዋሪ

11 ዲሴምበር – 9 ጃንዋሪ

ቲቢ

ጥር

9 ጃንዋሪ – 7 ፌብሯሪ

10 ጃንዋሪ – 8 ፌብሯሪ

መቺር

የካቲት

8 ፌብሯሪ – 9 ማርች

9 ፌብሯሪ – 9 ማርች

ፓመኖት

መጋቢት

10 ማርች – 8 አፕሪል

10 ማርች – 8 አፕሪል

ፓርሙቲ

ሚያዝያ

9 አፕሪል – 8 ሜይ

9 አፕሪል – 8 ሜይ

ፓቾንስ

ግንቦት

9 ሜይ – 7 ጁን

9 ሜይ – 7 ጁን

ፓይኒ

ሰኔ

8 ጁን – 7 ጁላይ

8 ጁን – 7 ጁላይ

ኢፒፒ

ሐምሌ

8 ጁላይ – 6 ኦጎስት

8 ጁላይ – 6 ኦጎስት

መሶሪ

ነሐሴ

7 ኦጎስት – 5 ሴፕቴምበር

7 ኦጎስት – 5 ሴፕቴምበር

ኢፓጎመናይ/ፒ ኮጊ

ጳጉሜ

6 ሴፕቴምበር – 10 ሴፕቴምበር

6 ሴፕቴምበር – 11 ሴፕቴምበር

የእስክንድርያው/ቅብጥ እና የኢትዮጵያ አቆጣጠሮቹ ቢመሳሰሉም ከላይ በሠንጠረዥ 18 እንደምንመለከተው የግዕዝ የወራት ስሞች ከተወሰኑት (ያውም ያጋጣሚ ከሚመስል መመሳሰል በስተቀር) ከቅብጡ የወራቱ ስሞች ጋር አይገናኙም። የአማርኛና የግዕዝ ግን አንድ ናቸው።[8] ኃይሉ ሀብቱ (2006:8) መስከረም በግዕዝ ሠረቀ ቲቶም ይባላል ይላል። ይህ በቀጥታ ከግብፁ ቶት ጋር ይገናኛል።

ሠረቀ ቲቶ ማለት የቲቶ መውጣት ማለት ነው። የግብፅ ዓመት የሚጀምርበት ቶት ከመነሻው ሲሩስ ከምትባለው ከኮብ ጠዋት ላይ ከምትታይበት ግዜ ጋር ቢያያዝም ቶት በራሱ ኮከብ አይደለም።[9] ቶት የጨረቃ አምላክ ነው። በግዕዝ ኃይሉ እንዳለው ሠረቀቲቶ የሚባል ስያሜ ካለም ስያሜው የወጣው የግብፁን አጠቃቀም በደንብ ካለመገንዘብ ይመስላል።

የእስክንድርያው/ቅብጥ አቆጣጠር ለኢትዮጵያው ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ሌሎች ሀገሮች አቆጣጠር መሰረት ሆኗል። ለምሳሌ፣ በፈረንሳይ አብዮት ወቅት የተፈጠረው አቆጣጠር የግብፅን መሰረት አድርጎ ነበር። አብዛኞቹ አቆጣጠሮች የግሪጎሪያኑ በአለም ላይ ተፅዕኖው እየበረታ ሲመጣ ቢቀሩም፣ እስካሁን ድረስ በአንዳንድ ህብረተሰቦች የሚያገለግሉ አሉ። በዚህ ነጥብ ላይ በማጠቃለያው ክፍል እንመለስበታለን።

የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከእስክንድርያው አቆጣጠር የሚለይበት ዘመን ‘ኢራ’ የሚጀምርበት ነው። የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከሌሎች ክርስትናንን መሰረት አድርገው ዘመን ከሚቆጥሩትም ይለያል። የዚህ ልዩነት ምንጭን አጠር አድርገን በቀጣዩ ክፍል እንዳስሳለን።

2. የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከግሪጎሪያንና ከቅብጥ አቆጣጠሮች ያለው ልዩነት

በአለማችን ወጥ የሆነ ዓመት የሚቆጠርበት አሰራር የወጣው በቅርብ ግዜ ነው። የጁሊያን አቆጣጠርን ብንመለከት በስድስተኛው ክፍለዘመን ነው። ከዚያ በፊት በሮማኖች ዘንድ ዓመት ከተወሰነ ነጥብ ላይ በመነሳት 1፣ 2፣ ወዘተ. እየተባለ ሳይሆን የሚቆጠረው በካውንስሎች፣ “በዚህ ካውንስል ዓመት” እየተባለ ነበር። ለዚህ በምሳሌነት ተዘውትሮ የሚጠቀሰው በቀደምት የክርስትያን ፅሁፎች ላይ ተደጋግሞ ይገለፅ የነበረው ክርስቶስ የተሰቀለበት 29 ጋአ (የጋራ አቆጣጠር) ነው።

ይህ ዓመት በቀደምት ፅሁፎች የሚገለፀው በሁለቱ የሮማን ካውንስሎች ሲ. ፉፊዩስ ጀሚኑስ[10] እና ኤል. ሩቢሉዩስ ጀሚኑስ[11] ዓመት በሚል ነበር (ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ 2005፡111)። ግሪኮች እና አሲሪያኖችም በሮማን ግዛት ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ዓመት መለያ ነበራቸው (ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ 2005፡110)።

በጥንታዊ ግብፅ ደግሞ ዓመትን በንጉሶች መቁጠር የተለመደ ነበር። አንድ ንጉሥ ወርዶ ሌላ ሲተካ እንደአዲስ ይጀመራል። ይህ አይነት ዓመት የመቁጠር ስልት በሌሎች ሀገሮችም፣ ሩቅ ሳንሄድ በኢትዮጵያም የነበረ ነው። የግዕዝ የብራና ፅሁፎችን ማገላበጥ ቀርቶብን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ግዜ የታተሙ መፅሀፎችን ብቻ እንኳ ብንመረምር፣ “ይህ መፅሀፍ ኃይለሥላሴ በነገሱ — ዓመት ታተመ” የሚል አይነት ሀረግ በብዙዎቹ እናገኛለን። ከእንደዚህ አይነት መፅሀፎች አብዛኞቹ ከጎኑ አብረው ዓመተ ምሕረትን ቢሰጡም አንዳንዶቹ የንግስናውን ዓመት ብቻ በማስቀመጥ ዓመተ ምሕረትን ፈፅሞ የማይሰጡም አሉ።

ረጅም ግዜ የሚጓዝ ቀጣይነት ያለው ዘመን የሚለካበት ቆጠራ በአብዛኛው ጥንታዊ ህብረተሰብ ባይኖርም ባሁኑ ግዜ እብራውያን አለም ተፈጠረ ብለው ከሚያስቡበት በመነሳት ዓመትን ይቆጥራሉ። ለዚህም፣ ለዘመን አቆጣጠር እየተጠቀሙበት ያለውን 3761 ቅጋአ መነሻ አድርገው ወስደዋል።

በዚህም ለምሳሌ፣ የእብራይስጥ አዲስ ዓመት ሮሽሀሸና በእብራዊያን አቆጣጠር ትሽሪ 1፣ 5775፣ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 15፣ 2007 ላይ ነው ያረፈው።[12] በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ሮሽሀሸና በእብራዊያን የጀመረው መስከረም 2፣ 2008 ማታ ላይ ነበር። ከቀኑ/ከብርሀን ከተነሳን መስከረም 3 መሆኑ ነው።

የክርስትናው እምነት የእብራውያን እምነት ላይ ተመስርቶ የመጣ ነውና ዓመትን ዓለም ተፈጠረች ብለው ሁለቱም እምነቶች ከሚያስቡበት ጀምሮ መቁጠርም ያለ ነው። እብራውያን በዓመተ ዓለም ዘመን መቁጠርን የጀመሩት ክርስትያኖች መጠቀም ከጀመሩ በኋላ እጅግ ዘግይተው በ14ኛው ክፍለዘመን ነው (ሪቻርደስ 1998፡226)።[13] ይህ አይነቱ አቆጣጠር በኢትያጵያም በተለይ በቀደምት ብራና ላይ ፅሁፎች በስፋት ይገኛል።

አቆጣጠሩ በግዕዝ፣ ዓመተ ዓለም (ዓዓ) ሲባል በላቲን ደግሞ አኖሙንዲ[14] ይባላል። ምንም እንኳ ለሁለቱም መሰረት ብሉይ ኪዳን ቢሆንም፣ በክርስትያኖች እና በእብራውያን የዓመተ ዓለም ስሌት መካከል ልዩነት አለ። ለዚህ ዋንኛው ምክንያት የሚጠቀሙበት መፅሀፍ ቅጂ መለያየት ነው። በመጀመሪያዎቹ ክርስትያኖች ለስሌቱ የተጠቀሙበት ቅጂ የግሪኩ ሴፕቱአጂንት[15] በመባል የሚታወቀውን ነው።[16]

በክርስትያኖች ረገድ ፍጥረተ ዓለምን ለማስላት ከሞከሩት ውስጥ የመጀመሪያው ተደርጎ የሚወሰደው የሶስተኛው መቶ ክፍለዘመን ሴክቱስ ጁሊየስ አፍሪካነስ የተባለው ነው (ሞስሻመር 2008፡28 & ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ 2005፡120)። በርግጥ ከሱ በፊት ቲዎፍሎስ (115-181) በወቅቱ ለነበረው ገዢ ከአዳም ጀምሮ እስከወቅቱ ድረስ ዝርዝር ዘመን ‘ክሮኖሎጂ’ አቅርቦለት ነበር። በዚህ ሰው ስሌት ፍጥረተ ዓለም 5529 ቅጋአ (ቅድመ የጋራ አቆጠጠር) ነው።

አፍሪካነስ በበኩሉ በ221 አካባቢ የክርስቶስ የመወለድ ብስራትን/የማርያም ክርስቶስን  መፀነስን ቀን ማርች 25፣ 5501 ዓመተ ዓለም የመጀመሪያ ቀን አደረገው። ከዚያ በኋላ የተነሱ የሀይማኖት ሊቃውንት ከአፍሪካኑስ የተለየ ቀመር እየያዙ ብቅ ብለዋል።[17] ከነዚህ ውስጥ በጣም ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው በ5 መቶ የመጀመሪያው ዓመታት የነበረው የእስክንድርያው አኒያኑስ ያወጣው ቀመር ነው። ይህ ቀመር የፍጥረተ ዓለም መጀመሪያ ቀንንም እሁድ ላይ እንዲያርፍ አድርጎት ነበር።

በአኒያኑስ ስሌት የፍጥረተ ዓለም መጀመሪያ ቀን ሱልሊኪዩስ ካሜሮኑስ[18] እና ጋዩስ ፖምፒዩስ[19] የሮማን ካውንስል ከነበሩበት ሲሰላ ማርች 25፣ 5501 ነው። ይህም በእስክንድርያው ዓመት የሚጀምረው በቲቶ ‘መስከረም’ ስለሆነ በጁሊያን/ግሪጎሪያን አቆጣጠር ማርች 25፣ 5501 ቅጋአ ያረፈበት ዓመት በእስክንድርያው አንድ ዓመት ወደኋላ ይሄዳል።

ስለዚህ በእስክንድርያው አቆጣጠር የሲቪል ዓመት መጀመሪያውን ቀን፣ ማ. ቲቶ 1፣ ሳይለቁ ፍጥረተ ዓለም መጀመሪያ (ሱልሊኪዩስ ካሜሮኑስ እና ጋዩስ ፖምፒዩስ የሮማን ካውንስል ከነበሩበት ወቅት) ኦገስት 29፣ 5500 ነው (ሞስሻመር 2008፡357)። ይህ በግሪጎርያን አቆጣጠር 8 ጋአ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያው አቆጣጠር ዘመን ‘ኢራ’ ከዚህ ስሌት የተገኘ ነው።[20]

በአብረሀም እምነት ተከታዮች ዘንድ ፍጥረተ ዓለም ከሚባለው ጀምሮ ከመቁጠር በተጨማሪ በክርስትያኖች ዘንድ ከክርስቶስ ጋር በማያያዝ ዘመንን መጀመር በአሁኑ ግዜ ለሲቪሉ (በበርካታ ሀገሮች ለሚያገለግለው) የግሪጎሪያን አቆጣጠር መሰረት ሆኗል። ይህ አቆጣጠር በኢትዮጵያው የሲቪሉ አቆጣጠርም የተመሰረተበት ነው። ከእምነት ጋር በተያያዘ ዓመት መቁጠር የእስልምናውንም አቆጣጠር መጥቀስ ይቻላል።

ከአንድ ታሪካዊ ክንዋኔ አንስቶ ዘመን መቁጠርም ከእምነት ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም። እንዲያውም የክርስትናው ዘመን ‘ኢራ’ በዓለማችን ከመሰራጨቱ በፊት፣ በላይኛው ክፍል እንደገለፅንው፣ ከንጉሶች ንግስና ዓመት፣ ከካውንስሎች ምርጫ፣ ከተለያዩ አበይት ድርጊቶች፣ ወዘተ. በመነሳት ዓመት ይቆጠር ነበር። ከክርስትናው እና እስልምናው ዘመን ‘ኢራ’ መስፋፋት በኋላም ሌላ ዘመን ‘ኢራ’ ለመጠቀም የሞከሩ ነበሩ። አሁንም አሉ። በዚህ ረገድ የፈረንሳይ አብዮት አቆጣጠርን መጥቀስ ይቻላል።

የፈረንሳይ አብዮት አቆጣጠር የተመሰረተው በ1773 ሲሆን፣ ዘመኑ የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ከተመሰረተበት ከሴፕምቴበር 22፣ 1772 አንድ ብሎ እንዲጀምር አድርገው ነበር። በቅርብ ግዜ ደግሞ የተወሰኑ የበርበር ዘመን አቆጣጠር ተጠቃሚ በርበሮች ለአቆጣጠራቸው የዘመን መነሻ 950 ቅጋአ አድርገዋል። ይህ በግብፅ የ22ኛው ስርወመንግስት መስራች የሆነው ሾሼንቅ ቀዳማዊ ስልጣን ይዟል ተብሎ የሚገመትበት ዓመት ነው።[21]

በታሪክ እንደሚታወቀው፣ የግብፅ 22ኛው ስርወመንግስት የሊቢያን ሰዎች ግብፅን ተቆጣጠረው ያስተዳደሩበት ነው። ሾሼንቅ ቀዳማዊ በርበር እንደሆነ ይነገራል። አሲሪያኖችም ባሁኑ ወቅት ለአቆጣጠራቸው መነሻ 4750 ቅጋአ አድርገዋል።[22] ምክንያታቸው፣ 4750 ቅጋአ በአሹር (በአሁኑ ወቅት ሰሜን ኢራቅ) የመጀመሪያው ቤተመቅደስ የተገነባበት ዓመት ነው በሚል ነው።[23]

የኢትዮጵያው አቆጣጠር ልክ እንደግሪጎሪያኑ ዘመን የሚለካው ከክርስትና እምነት ጋር በተያያዘ ቢሆንም፣ የአዲስ ዓመት ቀንና የዘመን ‘ኢራ’ መጀመሪያ የተለዩ ናቸው። እነዚህ ልዩነቶች ከምን እንደመጡ በሚቀጥለው ንኡስ ክፍል እንዳስሳለን።

2.1 የኢትዮጵያና የግሪጎሪያን አቆጣጠር ልዩነት

አሁን ባለንበት ክፍለዘመን፣ የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከግሪጎርያን አቆጣጠር ከሴፕቴምበር 11 (በሊፕ ዓመት ከሴፕቴምበር 12) እስከ ዲሴምበር 31 በሰባት ዓመት፣ ከጃንዋሪ 1 እስከ ሴፕቴምበር 10 (በሊፕ ዓመት እስከ ሴፕቴምበር 11) ደግሞ በስምንት ዓመት ይለያል። በተወሰኑ ወራት የሰባት ዓመት በተወሰኑት ደግሞ የስምንት ዓመት ልዩነት የመኖሩ ምክንያት አዲስ ዓመት የሚጀምርባቸው ግዜያት በሁለቱ አቆጣጠሮች በመለያያታቸው ነው።

ሁለቱ አቆጣጠሮች አዲስ ዓመትን በተለያየ ቀን መጀመራቸው፣ ከእምነት መለየያት ጋር በተያያዘ ወይም በአተረጓጎም ልዩነት ምክንያት የመጣ አይደለም። አንዳንድ ሀገሮች ከባህላቸው እና ከእምነት ጋር በማያያዝ የዓመት መጀመሪያውን የለወጡ ቢኖሩም የጁሊያን አቆጣጠር ከመነሻው ዓመቱ የሚጀምረው ጃንዋሪ አንድ ነበር።[24] በጥንቱ የሮማን አቆጣጠር ላይ ማስተካከያ በማድረግ ስሙን ለአቆጣጠሩ የተወው ጁሊየስ ቄሳር የነበረው ከክርስትና መነሳት በፊት ነው።

በሊፕ ዓመት ረገድ የተወሰነ ለውጥ ቢኖርም የግሪጎሪያን አቆጣጠር በመሰረቱ ከጁሊያን አቆጣጠር ጋር አንድ ነው። የወራቱ ስም እና በየወራቱ ያሉት የቀናቱ ብዛት ብቻ ሳይሆን ዓመቱ የሚጀምረውም በጀነዋሪ 1 ነው።

የኢትዮጵያ አቆጣጠርም ከግብፅ በመምጣቱ እና የግብፁ አቆጣጠር ዓመት የሚጀምርበት ቲቶ 1 (በኢትዮጵያው መስከረም 1) ጥንት ክርስትና ቀርቶ ለክርስትናው መሰረት የሆነው የአይሁድ እምነት እራሱ ገና ሳይታሰብ የነበረ በመሆኑ ከክርስትና እምነት ጋር አይያያዝም።

የኢትዮጵያውም ሆነ የግሪጎሪያን አቆጣጠር የዓመት መጀመሪያ የክርስትና እምነት መሰረት ባይኖረውም፣ የዘመን ‘ኢራ’ መጀመሪያ ግን በሁለቱም አቆጣጠሮች ከክርስትና እምነት ጋር ይያያዛል። ሁለቱም መነሻ ነው የሚሉት ገብሬል ለማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን ትፀንሻለሽ ብሎ የነገረበት ቀን ነው ብለው ክርስትያኖች የሚያስቡትን ወይም ፈጣሪ በማርያም ያደረበትን፣ ማ. እየሱስ ክርስቶስ የተፀነሰበትን፣ ቀን ይመለከታል።[25] ይህ ከሆነ በሁለቱ አቆጣጠሮች መሀከል ያለው ልዩነት እንዴት ሊመጣ ቻለ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

አንዳንድ በአማርኛ የወጡ ስራዎች በግሪጎሪያን እና በኢትዮጵያ አቆጣጠሮች መሀከል ያለው የ7/8 ዓመት ልዩነት የመጣው የክርስቶስ መፀነስ/ልደት በፀሀይና በጨረቃ የዘመን አቈጣጠር ስለተሰላ ነው የሚል አንድምታ ያቀርባሉ። ከላይ እንደገለፅንው ለሁለቱም ዘመን ‘ኤራ’ መነሻ በሀሳብ ደረጃ የክርስቶስ መወለድ/መፀነስ ዜና ነው። ይሁን እንጂ፣ ለቀመሩ ልዩነት የሆነው አንዱ አቆጣጠር በፀሀይ ዓመት ሌላኛው በጨረቃ ዓመት ግዜውን ስላሰላው አይደለም። ልዩነቱ የመጣው የእየሱስ በማሪያም እንደሚያድር የተበሰረበትን/የተፀነሰበትን ቀን በማስላት ሂደት በተፈጠረ አለመግባባት ነው።

          የግሪጎርያን አቆጣጠር የሚከተለው ዲዮኒሱስ ኤክስጉስ[26] ያወጣውን ስሌት ነው። ይህ ሰው ዘመን የሚጀምርበት ከክርስቶስ መወለድ/መፀነስ ጋር መሆን አለበት በሚል በ525 ጋአ “የራሱን ቀመር” አበጀና ከዚያን ግዜ ጀምሮ ያለውን አኖዶሚኒ ‘አመተ እግዚእ’ የሚል ስያሜ ሰጠው። ይህ ከሱ ከመቶ ዓመት በፊት የነበረው አኒያኑስ የተባለው የእስክንድርያ ሊቅ ካስቀመጠው የስምንት ዓመት ልዩነት ነበረው።[27]

በሁለቱም እሳቤ ለማርያም/ለዮሴፍ ገብሬል የእየሱስን መፀነስ አብስሯል የተባለበት ቀንና ወር ግን አንድ ነበር። ይህም በጁሊያን አቆጣጠር ማርች 25 ነው። ይህም የኢትዮጵያው አቆጣጠር የክርስቶስን መፀነስ በጁሊያን አቆጣጠር ረገድ ማርች 25፣ 9 አኖ ዶሚኒ ‘አመተ እግዚእ’ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያው አቆጣጠር አዲስ ዓመት የሚጀምረው በመስከረም 1 በመሆኑ የክርስቶስ ዘመኑን አንድ ብሎ መቁጠር የጀመረው ወደኋላ ሰባት ወራት ሄዶ ነው። ይህም በጁሊያን አቆጣጠር ኦገስት 29፣ 8 አኖዶሚኒ ‘አመተ እግዚእ’ መሆኑ ነው።

ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ እንደገለፀው ዲዮኒሱስ የብስራቱ ቀን “ይሄ ነው” ብሎ አቀረበ እንጂ እንዴት እዚያ ቁጥር ላይ እንደደረሰበት ያሳየው ነገር የለም (2005፡122)። ቀመሩንም እራሱ ይስራው/ይፍጠረው ወይስ ከሱ በፊት ከተደረጉ ከሌሎች ስራዎች ይውሰደው የገለፀው ነገር የለም (ዝኒከማሁ)። ወደኋላ ላይ እንደምንመለከተው ምንጭ አይጥቀስ እንጂ ዲዮኒሱስ ቀመሩን ከሌላ ነው የወሰደው። ያም ሆኖ ይህ ቀመር በኋላ ሲሰላ ስህተት እንዳለው ሊታወቅ ችሏል። ይህ ማለት ግን የአኒያኑስ ቀመር ትክክል ነው ማለት አይደለም።

የእየሱስ ክርስቶስ ልደትን በትክክል ቀኑን የሚገልፅ በወቅቱ የተሰራ አይገኝም። በማቲወስ እና ሉቃስ ወንጌሎች ላይ ስለልደቱ የተሰጡትም እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ናቸው። ብዙ ምሁራን በተለይ በሉቃስ የሚገኘው የተምታታና የተሳሳተ እንደሆነ ይናገራሉ።[28] ሆኖም ልደቱን ለማስላት እነዚህ ወንጌሎች መሰረታዊ ናቸው።

የመስኩ ተመራማሪዎች በወንጌሎቹ ላይ ስለልደቱ የተገለፀውን እንዲሁም እየሱስ ማስተማር ጀመረ (በሉቃስ 3፡23 ላይ ከተገለፀው) የተባለበትን ዓመት ከሌሎች ታሪካዊ ክስተቶች እና ሰነዶች ጋር በማመሳከር የእየሱስ ልደትን ለማስላት ሞክረዋል። ለምሳሌ፣ ፓውል ማየር (1989)ን እና በዚያ የተጠቀሱ ስራዎችን ይመልከቱ።

ምንም እንኳ አጥጋቢ ማስረጃ ባይገኝም፣ ከላይ እንደገለፅንው፣ የሉቃስ እና ማቲዎስ ወንጌሎች የእየሱስ ልደትን ለማስላት መሰረታዊ ናቸው። በሁለቱም ወንጌሎች እየሱስ የተወለደው በንጉሥ ሔሮድ ዘመን ነው (ሉቃስ 1፡5፣ ማቲወስ 2፡1)። ንጉሥ ሔሮድ ደግሞ የሞተው 4 ቅጋአ ነው (ፓውል ማየር 1989፡116)።[29] የእየሱስ ልደት ከ4 ቅጋአ ወዲህ ሊሆን አይችልም ማለት ነው።

ብዙዎቹ ሊቃውንት ልደቱን ከ7 እስከ 4 ቅጋአ ባለው ውስጥ ያስቀምጡታል።[30] እየሱስ ማስተማር ሲጀምር 30 ዓመት አካባቢ ነው ከሚለው ከሉቃስ 3፡23 በመነሳት ወደኋላ በመሄድ ከታሪክ አንፃር ተገናዝቦ ሲሰላም በየስራዎቹ የተወሰነ ልዩነት ቢኖርም የእየሱስ ልደት ከ7 እስከ 4 ቅጋአ ያለው ዓመት ነው (ዝኒከማሁ)። ፓውል ማየር (1989) የእየሱስ ልደት ሊሆን የሚችለውና አሳማኙ 5 ቅጋአ ነው ይላል።[31] ይህ ከግሪጎሪያኑም ሆነ በአኒያኑስ ስሌት ከሚቆጥረው የኢትዮጵያ አቆጣጠርም አይገጥምም።[32]

2.2 የኢትዮጵያና የቅብጥ አቆጣጠሮች ልዩነት

የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከግሪጎሪያን ብቻ ሳይሆን በዘመን ‘ኢራ’ ረገድ ከቅብጥም ይለያል። የቅብጡ አቆጣጠር የሚጀምረው በጁሊያን አቆጣጠር ኦገስት 29፣ 284 ጋአ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ደግሞ የሚጀምረው፣ ከላይ እንደገለፅንው፣ ኦገስት 29፣ 8 ጋአ ነው። ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያው 2007 በቅብጥ 1731 ነው። የኢትዮጵያው ሲቪል አቆጣጠር ከጋራ አቆጣጠር ያለውን የዓመተ ምሕረት (ዓም) በሚል ያቀርባል።[33] የቅብጡ ደግሞ ዓመተ ሰማዕታት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በቅብጡም ዘመን መነሻ ትጠቀማለች።

በቅብጥ አቆጣጠር የዘመኑ መጀመሪያ ክርስትያኖችን ከጨፈጨፈው ዲዮክሌትያን የተባለው የሮማን ኢምፐረር የሆነበት 284 ጋአ ነው። ዓመቱም የሚጀምረው ቲቶ 1 ‘መስከረም 1’ በጁሊያን አቆጣጠር ኦገስት 29፣ 284 ጋአ ነው። በጥንታዊ ግብፅ፣ ከላይ እንደገለፅንው፣ ዓመትን በንጉሶች መቁጠር የተለመደ ነበርና ዲዮክሌትያን ሲነግስ ከሱ ጀምሮ መቁጠር ተጀመረ። ይህ ሰው ከሞተ በኋላም ግን በአዲስ በነገሰው ዘመኑን መጀመር ቀርቶ፣ ዲዮክሌትያን ከነገሰ ይህን ዓመት እየተባለ መቁጠሩ ቀጠለ።

ለዚህ ምክንያቱ አዲሱ ገዥ እንደሌሎቹ የሮማን ግዛቶች ግብፆችም በካውንስሎች እንዲቆጥሩ አዋጅ አውጥቶ ነበር። ይህ ደግሞ በግብፅ ያልተለመደ ከመሆኑ ባሻገር የግብፅ ስነፈልክ ሊቃውንት የሚስማማ ሆኖ አላገኙትም (ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ 2005፡122)። ዲዮክሌትያን ከሞተም በኋላ በዚያው ቀጠለ። ይህ በሂደት ተለመደና ንጉሶች ቢለዋወጡም ዓመቱ ዲዮክሌትያን ከነገሠበት እየተባለ እስከ 7ኛው መቶ ድረስ ተጓዘ።

ዘመኑም በስሙ ዓመተ ዲዮክሌትያን እየተባለ ይጠራ ነበር። ይህ ንጉሥ በመጨረሻው የንግሥና ዘመኑ በርካታ ክርስትያኖችን ጨፍጨፎ ስለነበር በስሙ መጠራት የለበትም በማለት በ7ኛው መቶ ክፍለዘመን ዓመተ ዲዮክሌትያን “ዓመተ ሰማዕታት” በእንግሊዝኛው ኢራ ኦፍ ማርትሪዪስ[34] በላቲኑ ደግሞ አኖ ማርቲረም[35] ተባለ (ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ 2005፡122፣ ሪቻርደስ 1998:159)። ከዚያ ወዲህ ይህ ዘመን በበርካታ ክርስትያኖች አቆጣጠርም እንደዘመን መለኪያ በአማራጭነት እየዋለ ዓመተ ሰማዕታት በመባል ይጠቀሳል። በርግጥ፣ አሁንም ዘመኑ በተለዋጭነት ዓመተ ዲዮክሌትያንም እየተባለ ይጠራል።

በላይኛው ክፍል እንደገለፅንው፣ የኢትዮጵያ አቆጣጠር ዘመን ‘ኢራ’ ከአኒያኑስ ቀመር ላይ በመነሳት የተጀመረ መሆኑ በተለያዩ ስራዎች ተጠቅሶ ቢገኝም፣ ከዚሁ ጋ ደግሞ አቆጣጠሩ ከፓኖዶሩስ ነው የሚልም እናገኛለን። ለኋለኛው ኡሊሽ (2003፡733)ን ይመልከቱ። ፓኖዶሩስ እና አኒያኑስ ሁለቱም ባንድ ዘመን የኖሩ የእስክንድርያ ሰዎች ነበሩ። የእነዚህ ሊቃውንት ስራ ለዘመናችን አልተረፈም።

ስለስራዎቹ የምናውቀው ከነሱ በኋላ ሌሎች ከጠቀሱት፣ በተለይ ደግሞ በዘጠነኛው መቶ የነበረው ጆርጅ ሲይንቸሉስ ከፃፈው በሳል የዓለም ታሪክ መፅሀፍ ነው።[36] እንደጆርጅ ከሆነ ፓኖዳሩስ እና አኒያኑስ በቲዎፍሎስ ጵጵስና ወቅት (385-412 ቅጋአ) ነበሩ (ሞስሻመር 2008፡357)።

በፓኖዳሩስ ስሌት የፍጥረተ ዓለም መጀመሪያ ቀን (ሱልሊኪዩስ ካሜሮኑስ እና ጋዩስ ፖምፒዩስ የሮማን ካውንስል በነበሩበት ወቅት) ማርች 25፣ 5493 ሲሆን በእስክንድርያው ዓመት የሚጀምረው በቲቶ ‘መስከረም’ ስለሆነ ፍጥረተ አለም የተከናወነበት ዓመት 5492 ነው። ይህ የቅብጡ አቆጣጠር ከሚጀምርበት ቲቶ 1፣ 1 ዓመተ ሰማዕታት (እንደጁሊየስ አቆጣጠር ኦገስት 29፣ 284 ጋአ) 6226 ዓመተ ዓለም መሆኑ ነው። ይህ የፓኖዳሩስ ቀመር የሚያስገኘው የግሪጎሪያኑን ዘመን ‘ኢራ’ ነው።[37]

አኒያኑስ የፓኖዳሩስ ስሌት በዓለማዊ ላይ የተመረኮዘ ነው በማለት የራሱን ቀመር አወጣ። ከላይ እንደገለፅንው፣ በአኒያኑስ ስሌት የፍጥረተ ዓለም መጀመሪያ ቀን (ሱልሊኪዩስ ካሜሮኑስ እና ጋዩስ ፖምፒዩስ) የሮማን ካውንስል ከነበሩበት ሲሰላ ማርች 25፣ 5501 ዕለተ እሁድ ነው። በእስክንድርያው ይህ ዓመት 5500 ላይ ያርፋል። እንደግሪጎሪያን አቆጣጠር ማርች 25፣ 360 ጋአ 11 ዑደተ ፋሲካ ነው።[38] ይህ በእንግሊዝኛው ‘ኢራ/ይር ኦፍ ግሬስ’ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ደግሞ ዓመተ ምሕረት ይባላል።

በአንዳንድ ፅሁፎች ማዘበራረቅ ቢኖርም በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ዓመተ ምሕረት ሲባል በጁሊያን አቆጣጠር ከኦገስት 359 ጋአ ጀምሮ 1 ብሎ በመቁጠር ነው። በሲቪል አቆጣጠሩ ዓመተ ምህረት የሚባለው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ዓመተ ሥጋዌ በእንግሊዝኛው ‘ይር ኦፍ ኢንካርኔሽን’ ነው። ዓመተ ሥጋዌ መባሉ ፈጣሪ (በክርስትያኖች እምነት) በማርያም አድሮ እንደሰው ሥጋ የሆነበትን፣ በሌላ አነጋገር እየሱስ ክርስቶስ የተፀነሰበትን የሚመለከት ነው። በአኒያኑስ ስሌት በዓመተ ሰማዕታት (284 ጋአ)እና በዓመተ ምሕረት ‘ይር ኦፍ ግሬስ’ (360 ጋአ) መሀከል ያለው የ76 ዓመት ልዩነት 4 አበቅቴ ‘ኤፓክት’[39] ነው። አንድ ዓውደ አበቅቴ 19 የጨረቃ ዓመት ነው።

አንድ የጨረቃ ዓመት (12 ወራት የያዘ) 354 ቀን አለው። ይህ በአማካይ 11 ቀን ከትሮፒካል/ፀሀይ ዓመት ያንሳል። ጥንታዊ ባቢሎንያን ይህን ችግር ለመቅረፍ በየ19 ዓመቱ 7 የጨረቃ ወራት ሳጋ በማስገባት ከፀሀይ ዓመት እንዲስተካከል ያደርጉ ነበር። ይህ የ19 ዓመት ዑደት በኋላ ላይ ተንቀሳቃሽ በዓላትን ለማስላት ክርስትያኖች ተጠቅመውበታል። በቀዳሚ ክፍል እንደገለፅንው፣ በእንግሊዝኛ ኤፓክት ወይም ዑደተ ሜቶኒክ ይባላል።

የኤፓክት ጥንተ-ፍጥረት ግሪክ ነው። ትኩረታችን የሲቪሉ አቆጣጠር ላይ ነውና ስለፋሲካ እና ስለሌሎች ተንቀሳቃሽ በዓላት ስሌት በዚህ ስራ ዝርዝር ውስጥ አንገባም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ስላለው የቀመሩ አጠቃቀም፣ ከብዙ በጥቂቱ፣ ኦቶ ኒውጌባወር (1979)ን እንዲሁም በአማርኛ ከተሰሩ ውስጥ አለቃ ያሬድ (2004)ን እና ጌታቸው ኃይሌ (2006)ን ይመልከቱ።

3. የኢትዮጵያ አቆጣጠርና የፀሀይ ዓመት ስሌት

የኢትዮጵያ፣ የጁሊያን፣ እና የቅብጥ አቆጣጠሮች በዓመት ስሌት፣ ማለትም (ማ.) ዓመት በሚይዛቸው ቀናት ብዛት ከሄድን አንድ ናቸው። በሶስቱም አቆጣጠሮች አንድ ዓመት በአማካይ 365.25 ቀናት ነው። ይህ አሀዝ ከኮከብ ዓመት፣ ማ. መሬት ፀሀይን ለመዞር ከሚፈጅባት ግዜ፣ ጋር እጅግ የቀረበ ቢሆንም፣ ከትሮፒካል/ፀሀይ ዓመት፣ ማ. ወቅት ከሚፈራረቅበት፣ የተወሰነ ልዩነት አለው።

የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር ተከልሶ በግሪጎርያን እንዲተካ ያስደረገው ይኸው ከፀሀይ/ትሮፒካል ዓመት ጋር ያለው መጠነኛ ልዩነት በግዜ ሂደት እየሰፋ መምጣቱ ነው። ከላይ እንደገለፅንው፣ የጁሊያን ዘመን አቆጣጠርና የኢትዮጵያን ዘመን አቆጣጠር የሚያመሳስላቸው ሁለቱም ያለ ልዩነት በየአራት ዓመቱ አንድ ቀን በመጨመራቸው ነው። ይህም የዓመቱን ቀናት በአማካይ 365.25 ያደርገዋል።

ከፀሀይ ዓመት እየተጎተተ የሚመጣውን ለማስተካከል እንደግሪጎሪያኑ በ400 ዓመት ሲካፈል ሙሉ ቀን የማይሰጠውን ክፍለዘመን ተራ ዓመት ማድረግ ይቻላል። ያም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ከፀሀይ ዓመት ጋር የተጣጣመ ነው ማለት አይደለም። ከዚያም በተሻለ ለምሳሌ ጆን ኸርሺል (1849) እንዳቀረበው ማድረግ ይቻላል።[40] ዘመን አቆጣጠራችንን ሳንለቅ፣ እንደግሪጎሪያን አቆጣጠር የሊፕ አመታትን ለማድረግ ቢሞከር (ወደ ኋላ ሄደን እናስተካክል ካላልን በቀር) ለውጡ ሊከሰት የሚችለው ያለንበት ክፍለዘመን ሲደፍን፣ ማለትም ከ87 ዓመት በኋላ በ2100 ነው።

ምንም እንኳ ዋናው ጉዳያችን ይህ ባይሆንም ወራቱ ከወቅቱ ጋር እንዲጓዙ ካስፈለጉ በሊፕ አመት ላይ ማስተካከያ ማድረጉ ግድ ነው። አለበለዚያ ክረምቱ በሰኔ ሲጀምር፣ አበባው በመስከረም ሲያብብ ማለቱ ዘፈን ብቻ ሆኖ ይቀራል። ለምሳሌ፣ 200 ጋአ ያከበርንው አዲስ ዓመት መስከረም 1 ዛሬ ላይ ሆነን ካከበርንው አዲስ ዓመት አንፃር ቢሰላ (2007-200/128) 14 ቀን አካባቢ ወደኋላ ሄዷል።

በትክክለኛው የፀሀይ ዓመት በ2007 መስከረም አንድ ያልንው በ200 ዓመት አካባቢ ነሃሴ 21 ነበር ማለት ነው። ማስተካከያ ሳይደርግ በዚሁ ከቀጠለ ወቅቶቹ አሁን ካሉት ከወራቱ ጋር አንድ አይሆኑም—ለምሳሌ ከ8320 ዓመት በኋላ የዘመን መለወጫችን መሀል ክረምት በግሪጎሪያን አቆጣጠር ጁላይ 7 ላይ ነው የሚሆነው።

4. ማጠቃለያ

በሀገራችን ያለው የዘመን አቆጣጠር ከጁልያን ዘመን አቆጣጠር ይልቅ ከቅብጥ ዘመን አቆጣጠር የተመሳሰለ ነው። የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር ከኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ጋር የሚለይባቸው ሶስት መሰረታዊ ነጥቦች አሉ።

አንደኛ፣ አዲስ ዓመት የሚጀምርባቸው ወራት የተለያዩ ናቸው። በኢትዮጵያው ዓመት የሚጀምረው መስከረም 1 የሚያርፈው በጁሊያኑ ኦገስት 29 ነው። ኦገስት ደግሞ ስምንተኛ ወር ነው። በጁሊያኑ ዓመት የሚጀምረው ጃንዋሪ 1 በኢትዮጵያው አቆጣጠር የሚያርፈው ታህሳስ ላይ ነው።

ሁለተኛ፣ ዘመናቱ የሚጀምሩበት የጋራ አቆጣጠር የተለያዩ ናቸው። በሁለቱ አቆጣጠሮች መሀከል የ7/8 አመታት ልዩነት አለ። ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ ህዳር 25፣ 2007 በጁሊያን ኖቨምበር 21፣ 2014 ሲሆን፣ በግሪጎሪያን ደግሞ ዲሴምበር 4፣ 2014 ነው።

ሶስተኛ፣ የወራቱ ቀናት በሁለቱ ዘመን አቆጣጠሮች የተለያዩ ናቸው። የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 30 ቀናት ያሉት 12 ወራትና 5 ቀናት (በሊፕ ዓመት ደግሞ 6 ቀናት) ያለው ጳጉሜን በዓመቱ መጨረሻ ሲኖር፣ የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር 12 ወራት ብቻ ነው ያለው። ወራቱም አሁን የግሪጎሪያን ዘመን አቆጣጠር የሚጠቀሙባቻው ናቸው። በሊፕ ዓመት የሚጨመረው ቀን በፌብሯሪ ላይ እንጂ በዓመቱ መጨረሻ ላይ አይደለም። የጁሊያን እና የኢትዮጵያ አቆጣጠሮች የሚመሳሰሉበት ዋንኛው በየአራት ዓመቱ ሳያዛንፉ አንድ ቀን በመጨመራቸው በአማካይ አንድ ዓመት 365.25 ቀናት መያዙ ነው።

ጁሊየስ ቄሳር በሮማን ዘመን አቆጣጠር ላይ ማስተካከያ ያደረገው የግብፁን ከተመለከተ በኋላ ነው። ይሁን እንጂ፣ የግብፅ ዘመን አቆጣጠር እራሱ የተስተካከለው አጉስተስ ግብፅን ማስተዳደር ከጀመረበት በኋላ ነው። ምናልባት ለዚህም ይሆናል የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በስህተት የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር እየተባለ በስፋት ይነገር የነበርው።[41] ምንም ጥያቄ በሌለው መልኩ የኢትዮጵያ አቆጣጠር የተቀዳው ከግብፅ እስክንድርያው/ቅብጥ አቆጣጠር ነው። ይህ አቆጣጠር በበኩሉ ባለ365-ቀን ከነበረው ጥንታዊ የግብፅ አቆጣጠር ሲወርድ የመጣ ነው።

ግብፆች ይጠቀሙባቸው ከነበሩት የዘመን አቆጣጠሮች ውስጥ አንዱ የሆነው የፀሀይ አቆጣጠር 365 ቀናት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ግዜ መኖሩን በማስተዋል በአራት ዓመት አንድ ግዜ አንድ ቀን እንዲጨመር ያደረጉት በ238 ቅጋአ በንጉሥ ፕቶለሚ 3ኛ ግዜ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ማስተካከያ ተግባራዊ የተደረገው ቆይቶ በ22 ቅጋአ፣ አፄ አጉስተስ ግብፅን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው።

የግብፅ ዘመን አቆጣጠር ተፅዕኖ ያሳደረው በኢትዮጵያ አቆጣጠር ላይ ብቻ አይደለም። በሌሎችም በርካታ አቆጣጠሮች ላይ ነው። ከነዚህ ህብረተሰቦች ውስጥ፣ (ኢትዮጵያን ጨምሮ) አርሜንያን እና ፋርስን ሪቻርደስ እንደምሳሌ ይጠቅሳል (1998፡154)። የፈረንሳይ አብዮት አቆጣጠርም የግብፅን መሰረት አድርጎ የወጣ ነው።

     የፈረንሳይ አብዮት የዘመን አቆጣጠር ከኢትዮጵያና ከቅብጥ ጋር ተመሳሳይ ነበር። ዓመቱ እያንዳንዳቸው 30 ቀናት በያዙ 12 ወራት እና 5 በሊፕ ዓመት ደግሞ 6 ቀናት በያዘች ጳጉሜን የተከፈለ ነበር። እያንዳንዱ ወር 10 ቀናት ባሉት ሳምንት የተከፈለ ሲሆን፣ ሙሉ ቀኑም በ10 ሰዓት እያንዳንዱ 100 ደቂቃ በያዘ ይከፈል ነበር። ይህ አቆጣጠር የተመሰረተው በ1773 ሲሆን፣ ዘመኑ የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ከተመሰረተበት ከሴፕቴምበር 22፣ 1772 አንድ ብሎ እንዲጀምር አድርገው ነበር። ዋናው አላማው ከእምነት ጋር ያልተገናኘ አቆጣጠር ለማውጣት ነበር።[42]

     በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን ቀዳሚውን የግብፅ አቆጣጠርንም ሆነ የተሻሻለውን የቅብጥ/እስክንድርያ አቆጣጠር የወረሱ ወራትን በ30 ቀናት ማደራጀቱን እና ተጨማሪ ቀናቱን ለብቻ፣ ብዙውን ግዜ ከዓመት መጨረሻ ላይ ማስቀመጥ እንጂ ሙሉ በሙሉ ዓመት መጀመሪያን እና የወራቱን ስሞች ሁሉ ወርሰዋል ማለት አይደለም። የወራት ስሞቹን ጭምር በመውሰድ የሚታወቀው ፋስሊ ወይም ሶር ሳን አቆጣጠር የሚባለው ነው።

ይህ አቆጣጠር እስልምና ከመነሳቱ በፊት 600 ጋአ በትንሿ ኤሽያ[43] የተመሰረተ ሲሆን፣ እስካሁን አልፎ አልፎ በተለያዩ ቦታዎች እንደሚያገለግል ሪቻርደስ (1998:159) ይገልፃል። አርመኒያኖች መጀመሪያ ላይ የሚጠቀሙበትን ጨረቃ-ፀሀይ ‘ሉኒሶላር’ አቆጣጠር ትተው የግብፅ አቆጣጠርን የወሰዱት 460 ቅጋአ እንደሆነ ይነገራል።[44]

     ሪቻርደስ (1998:160) የሮም ተፅዕኖ እና በኋላም የክርስትያን ተፅዕኖ ባይኖር ኖሮ ምናልባት የግብፅ አቆጣጠር በአለማችን ዋናው አቆጣጠር መሆኑ አይቀርም ነበር ይላል። ከሪቻርደስ አባባል አለመስማማት ይከብዳል። የግብፅ አቆጣጠር ውስብስብ አለመሆኑ ትልቅ የአቆጣጠር ግኝት መሆኑ ብዙም የሚያጠያይቅ አይመስለንም። ሪቻርደስ እንደገለፀው የእስልምና መነሳት ደግሞ ከክርስትናው እና ከሮማን ተፅዕኖ የተረፉትን የግብፅ አቆጣጠር ያገለግል የነበረባቸውን አብዛኛውን ባህሎች አጠፋቸው (ዝኒከማሁ)። ኢትዮጵያ ሁለቱንም ተፅዕኖ መቋቋም መቻሏ ይህን አቆጣጠር ይዛ ለመቆየቷ ምክንያት እንደሆነ ብዙም አከራካሪ አይደለም።

          የኢትዮጵያው አቆጣጠር ከግብፁ የሚመሳሰልበት በንጉሳኑ የንግስና ዘመን ዓመት በመቁጠርም ነው። ይህ አይነቱ ዓመት የመቁጠሪያ መንገድ የጋራ አቆጣጠር ከመስፋፋቱ በፊት በብዙ ሀገር ያገለግል ነበር። ይህ በራሱ በዓለም የተስፋፋው በግብፅ ተፅዕኖ ነው ተብሎ ይገመታል። ኢትዮጵያ ከግብፅም በላይ ግንኙነትና ቅርርብ በነበራት በጥንታዊ ደቡብ አረቢያ ግን የዚህ አይነቱ በንጉሶች ላይ ዓመት መቁጠር እንዳልነበር ቤስተን (1956:25) ይገልፃል። እጅግ የሚገርመው፣ ኢትዮጵያ ከደቡብ አረቢያ በዘመን ረገድ ምንም የሚያገናኛት ነገር አለመኖሩ ነው።

ለዚህ አንዱ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ከደቡብ አረቢያ ጋር የጠበቀ ግኙነት ማድረግ ከመጀመሯ በፊት ከግብፅ አቆጣጠር ጋር ትውውቅ ኖሯት ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ከደቡብ አረቢያ ጋር የነበራት ግንኙነት መነሻ 900 ቅጋአ ድረስ ወደ ኋላ ይሄዳል። ከዚህ በፊት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ውል ያለው በንጉሥ ላይ የተመሰረተ ስልጣኔ ለመኖሩ ብዙም ማስረጃ የለም። ይሁን እንጂ ፑንት ስለሚባል ሀገር እና ስለሀበሻ ህዝቦች በሁለተኛው ሺህ ቅጋአ በግብፅ ምንጮች የተጠቀሰ ነገር እናገኛለን (ግርማ እና አህመድ 2014)።

ይህ ግን ስለአቆጣጠሩ ብዙ አይነግረንም። የኢትዮጵያ አቆጣጠር በትክክል ከአንደኛው ሺህ ቅጋአ በፊት ከግብፅ ገብቶ ይሆናል የሚለውን በማያሻማ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለማስረገጥ ባሁኑ ግዜ አይቻልም። እስከምናውቀው ድረስ በዚህ ረገድ በቂ የሰነድ መረጃ ከየትኛውም ወገን ቢሆን የለም።

በዚህ ምዕራፍ እንደተመለከትንው፣ በዘመናት አቆጣጠር ደረጃ በንጉሶች ከመቁጠር በተጨማሪ ዘመን የሚጀመርበት በብዙ ሀገሮች የተለያየ ሆኖ ይገኛል። የቱርክ ከ1923 በፊት የነበረው በጁሊያን አቆጣጠር መሰረት ያደረገው ማሊ (ፋይናንሽያል) አቆጣጠር ልክ እንደቀድሞው ሊቢያ አቆጣጠር ዘመኑን ይቆጥር የነበረው፣ በዓመተ ሂጅራ ላይ ተመስርቶ ነው (ጆርጀን 2011፡182)።

ምናልባት ለማናችንም እንግዳ ነገር ያልሆነው የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከግሪጎሪያን አቆጣጠር በሰባት/ስምንት ዓመት መለየቱ ነው። የኢትዮጵያ አቆጣጠር በዘመን ስሌት ከቅብጥ አቆጣጠርም ይለያል። ከቅብጥ መለየቱ የኢትዮጵያው የሚቆጥረው በመርህ ደረጃ ከክርስቶ መፀነስ ‘ኢንካርኔሽን’ ጋር ሲያያዝ የቅብጡ ደግሞ ከዲዮክሌትያን ስልጣን ከያዘበት በመጀመሩ ነው። ይህ ንጉሥ በስተመጨረሻው ላይ ክርስትያኖችን አብዝቶ በመጨፍጨፉ ዘመኑ ዘመነ ዲዮክሌትያን መባሉ ቀርቶ ከ7ኛው መቶ ወዲህ ባብዛኛው ዓመተ ሰማዕታት በመባል ይታወቃል። ይህ ዘመን በኢትዮጵያ እና በሌሎች አብያተ ክርስትያናትም ዓመተ ሰማዕታት በሚል ለስሌት በተወሰነ ደረጃ ያገለግላል።

በዓመተ ዓለም ደረጃ በእብራውያን እና በክርስትያን ቀመር ልዩነቱ ሰፊ ነው። የእብራውያኑ 3761 ቅጋአ ሲሆን የክርስታያኑ 5493 ቅጋአ ነው። በኢትዮጵያውና በግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በዚህ ረገድ ልዩነት የለም። ልዩነቱ የዚህ ዘመንን መነሻ የኢትዮጵያዊው አቆጣጠር አኒያኑስን ቀመር በመከተል 5500 ቅጋአ አድርጎ ሲወስድ፣ ግሪጎሪያኑ ደግሞ በ“ዲዮኒሱስ” ስሌት መሰረት  5493 ቅጋአ አድርጎ መውሰዱ ነው። ለሁለቱ ልዩነቶች ምክንያት የሆነው፣ ለቀመራቸው የሚይዙት ነጥብና የሚጠቀሙበት ቅጂ መለያየት ነው።

ይህ ማለት ግን በብሉይ ኪዳን መሰረት ዓለም ተፈጠረችበት ተብሎ የሚታሰበው ልዩነት በክርስትያኖችና እና በእብራውያን አቆጣጠሮች ውስጥ ብቻ ያለ ነው ማለት አይደለም። ልዩነቱ በሁለቱ ሀይማኖቶች ብቻ የተወሰነ አይደለም። የቅጂዎችና ለቀመር የሚጠቀሙባቸው ዘመናት መለያየት እንዲሁም የመረጃዎቹ በራሳቸው ግልፅ አለመሆን አሁንም በአብርሀም ሀይማኖት ስሌት ዓለም ተፈጠረችበት የሚባለው ቀን ላይ በክርስትያኖች ውስጥም ስምምነት የለም። ለምሳሌ፣ የ19ኛው ክፍለዘመን የሀይማኖት ተመራማሪ ክራውፎርድ (1887) በመፅሐፉ ርዕስ እንደ አዋጅ አድርጎ ባወጣው ላይ ከአዳም እስከ አብርሀም ያለው ዓመት ብቻ አስር ሺህ አምስት መቶ ነው።

ይህ ሰው (1887፡164) ከሱ በፊት የተለያዩ ሊቃውንት ያወጡትን ቀመሮች በአባሪ ሠንጠርዥ ባቀረበበት ክፍል አነስተኛ ዓመት ባቀረበው ፔላቪዩስ[45] 3983 ቅጋአ እና ረጅም ዓመት ባቀረበው በበንሰን[46] (20,000 ቅጋአ) መሀከል ያለው ልዩነት ከ16ሺህ ዓመት በላይ ነው። በቅርቡ ደግሞ ጆን ማክኦውን (2005) ፍጥረተ ዓለምን 11,013 ቅጋአ አድርጎታል። በዚህ ደረጃ ያለው ቀመር ብዛቱ እንደስራው ነው። በየክፍለ ዘመናቱ በተነሱት የሀይማኖት ሊቃውንት ስራዎች የተለያየ ቀመር ማግኘቱ ከባድ አይደለም።

ከአብርሀም ሀይማኖቶች ውጭ በተለያዩ ህብረተሰቦች ያለውን እሳቤ ብንመለከት ልዩነቱ እንደእምነቱ የሰፋ ሆኖ እናገኘዋለን። በጥንታዊ የሱሜሪያን የንጉሶች ዝርዝር ጥራዝ መሰረት ፍጥረተ ዓለም ከሁለት መቶ አርባ ሺህ ዓመት በላይ አስቆጥሯል።[47] በቱሪን ፓፒረስ የመንግስታቱ ዝርዝር መሰረት የጥንታዊ ግብፆች የመንግስታቸው መነሻ (አማልክቱ ነገሱበት ከሚሉት ጭምር) ከሰላሳ ስድስት ሺህ ቅጋአ በላይ ነው።

ዲዮዶሩስ ከቀሳውስቱ አገኘሁት ባለው ስሌት ደግሞ በግብፅ የመጀመሪያው ጣኦት ነገሠ ከሚሉበት እስከ የማቅዶኒያው ታላቁ እስክንድር ወደ ኤሲያ ሲዘምት የነበረው ግዜ ሀያ ሶስት ሺህ ዓመት ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ከዚህም በላይ አስፍተው ይናገሩ ነበር (ዲዮዶሩስ/ቡዝ እንደተረጎመው 1814:32)።[48] ጥንታዊ ባቢሎንያን የማቅዶኒያው ታላቁ እስክንድር ወደ ኤሲያ ሲዘምት መንግስታቸው አራት መቶ ሰባ ሶስት ሺህ ዓመት አስቆጥሮ ነበር የሚሉት ዲዮዶሩስ ሲቹልስን አስገርሞት ነበር።

ቴሬሲ (2002:7-8) እንደዘገበው በአምስተኛው መቶ ጋአ የነበረ ህንዳዊ የመሬትን እድሜ 4.3 ቢሊዮን ዓመት መስጠቱ ከዘመናችን ሳይንስ ግምት 4.6 ቢሊዮን ዓመት ከማናቸውም ሀይማኖቶች የስነፍጥረት እሳቤ እጅግ የቀረበ ያደርገዋል። ከሳይንስ ጋር በጣም ይቀራረባል የሚባለው የሂንዱይዝም የስነፍጥረት እድሜ ብቻ ሳይሆን ስለአጠቃላይ ዩኒቨርስ ያለው እሳቤ ነው። በዚህ ነጥብ ላይ ከብዙ በጥቂቱ ቴሬሲ (2002)ን እና ሳጋን (1985)ን ይመልከቱ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቆጣጠርም ሆነ የግሪጎሪያኑ በአሁኑ ወቅት ዘመንን የሚለካው የጋራ አቆጣጠር ብለው ከወሰዱት ነጥብ በመነሳት ነውና የዓመተ ዓለም እሳቤ ብዙም ቦታ የለውም። ሆኖም፣ በቀደምት ስራዎች በሀገራችን በዓመተ ዓለም መቁጠር የተለመደ ነበርና የታሪክ ሰነዶችን ለመረዳት አቆጣጠሩን ማወቁ አይከፋም።

ልክ እንደሱሜሪያን፣ ባቢሎንያን እና ግብፆች፣ በግዕዝ ስራዎች የነገስታቱ ዝርዝር ከዓመተ ዓለም በመነሳት ይቀርብ ነበር። የኦቶ ኒውጌባወርን (1989) ክሮኖግራፊ ኢን ኢትዮጲክ ሶርስስ ይመልከቱ። ይህ ሰው፣ በዚህ ደረጃ ከተለያዩ ስራዎች በመንቀስ ከመፅሐፍ ቅዱስ ዘፍጥረት ጀምሮ በተለያዩ ሰነዶች የሚገኙ በሀገራችን የተነሱትን የነገስታት ዝርዝር የዘመን ቀመርን  አቅርቧል።

 

ማስታወሻዎች



[1]             ስለቦረና ኦሮሞው ባህላዊ አቆጣጠር አስመሮም ለገሰ (1974)ን ይመልከቱ።


[2]      ለአብነት ያህል የሚከተሉትን ስራዎች ይመልከቱ፤ ሪቻርደስ (ከ1998፡154) እና ጌታቸው ኃይሌ (2006፡36)።


[3]             Epagomenos.


[4]             Epagomenal day.


[5]      በሚከተለው ሠንጠረዥ የቅብጡ አቆጣጠር የወራት ስሞች የተወሰዱት ከፓርከር (1950:8) ነው።


[6]      በሠንጠረዡ ከግሪጎሪያኑ የቀን ቀመር የሚያመለክተው የዚህ ክፍለዘመንን ብቻ ነው። 2100 በግሪጎሪያን ሊፕ ዓመት ስላልሆነ በ22ኛው ክፍለዘመን ልዩነቱ በአንድ ቀን ይጨምራል።


[7]    የወራቱ ስያሜዎች በበርካታ ስራዎች ማለት ይቻላል (በተለይ በአፃፃፍ ረገድ) መጠነኛ ልዩነት ያሳያሉ። እነዚሁ የወራት ስሞች በአረብኛም የተለየ አቀራረብ አላቸው። በየወሮቹ በተለያዩ ስራዎች ከሚገኙት አንዳንዶቹን የሚከተሉት ናቸው፤ Thuout/Thoth, Paopi/Phaophi, Hathor/Athor/Athyr, Koiak/Khoiak/Choiak, Tobi/Tybi, Meshir/Mekhir/Mecheir, Paremhat/Fameno/Pharamhat/Phamenoth, Parmouti/Farmou/Pharmuthi, Pakhon/Pashons/Pachons, Paony/Payni/Paoni, Epep/Epiphi/Epip, Mesori/Mesore & Pi Kogi/Enavot/Epagomenai.


[8]             ለዝርዝሩ ምዕራፍ ሶስትን ይመልከቱ።


[9]      ከብዙ በጥቂቱ፣ ፓርከርን (1950)ን፣ ዊልሰን (1956)ን፣ እና ሪቻርደስ (1998)ን ይመልከቱ። ግብፆች የሲሩስ ኮከብ በንጋት ላይ መታየትን የዓመት መጀመሪያ ሲያደርጉ፣ ይህ ቀን አለም የተፈጠረችበት ነው ብለው ከማሰብ እንደሆነ ይታመናል። ፓርከር (1950፡47)ን ይመልከቱ።


[10]    C. Fufus Geminus.


[11]    L. Rubellius Geminus.


[12]    የእስራኤል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ድረገፅ: http://www.science.co.il/Jewish-Holidays.asp. Accessed 8/21/2015.


[13]           ሞስሻመር (2008፡87ቀቀ)ንም ይመልከቱ።


[14]    Anno mundi.


[15]           Septuagint.


[16]           የዚህ ቃል መነሻው ላቲን ሲሆን ትርጉሙም ሰባ ማለት ነው።


[17]    በዚህ ጉዳይ ላይ ክራውፎርድ (1887፡164)፣ ሞስሻመር (2008፡28) እና ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ (2005፡120) ይመልከቱ። ሞስሻመር (ዝኒከማሁ) እና ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ (ዝኒከማሁ) እንደገለፁት፣ ከአፍሪካኑስ በማስከተል የቃሳሪያው ኢስቡስ የፍጥረት ዘመንን 5200 ቅጋአ በማድረግ እየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን 5199 ዓዓ አደረገው። ይሁን እንጂ፣ ሆልፈርድ-ስትሪቨንስ (2005፡121) ኢስቡስ ይህን ዓመት የአብረሀም ዓመት ማለትን መርጦ እንደነበር ይገልፃል። ሌላው በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚገባው በምዕራቡ/በሮማን ቤተክርስትያን ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው የቤዴ ቀመር ነው። ቤዴ በፍጥረተ ዓለም እና በክርስቶስ ውልደት መሀከል ያለውን ዘመን 3952 አመታት አደረገው። ይሁን እንጂ ይህ በሁሉም ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም።


[18]           Sulpicius Camerinus.


[19]           Gaius Pompeius.


[20]    በተለያዩ ስራዎች ስለአኒያኑስ የዘመን ቀመር የተሳሳተ መረጃ ስለሚገኝ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ አድርገን በኋላ እንመለስበታለን።


[21]    Berber calendar https://en.wikipedia.org/wiki/Berber_calendar Accessed 9-12-2015.


[22]    Alkhas, Wilfred. Assyrian calendar. www.nineveh.com. Accessed 9-10-2015።


[23]           Timeline of Assyria. www.meta-religion.com


[24]    እዚህ ላይ የጁሊያን አቆጣጠር የተመሰረተበት የሮማን አቆጣጠርን ማለታችን እንዳልሆነ ልብ ማድረግ ያስፈልጋል። በቀዳሚው ክፍል እንደገለፅንው፣ ጁሊየስ ቄሳር ከማስተካከሉ በፊት የነበረው የሮማን አቆጣጠር ከመነሻው ዓመቱ የሚጀምረው ከማርች ነበር። ለዚህም ነው እነሴፕቴምበር፣ ኦክቶበር፣ ኖቬምበር እና ዲሴምበር በጥሬ ትርጉማቸው እንደቅደምተከተላቸው 7ኛ፣ 8ኛ፣ 9ኛ፣ እና 10ኛ የሚል ስያሜ የያዙት። እነዚህ ወሮች ባሁኑ ግዜ ከዘጠንኛ እስከ 12ኛ ያሉትን ወራት እንደሚያመለክቱ ልብ ይሏል።


[25]    ይህ በእንግሊዝኛው አኑንሴሽን (Annunciation) ወይም የእየሱስ ኢንካርኔሽን (Incarnation of Jesus) ይባላል።


[26]           Dionysius Exiguus


[27]    በላይኛው ክፍል እንደገለፅንው፣ አኒያኑስ የፍጥረተ አለም መጀመሪያን ከእስክንድርያው አቆጣጠር ዓመት እንዲስማማ በተደረገው መሰረት፣ የሚያርፈው 5943 ቅጋአ ነው።


[28]           ለምሳሌ፣ ሬይመንድ ብራውን (1977፣ 1988)ን እና ዱን (2003)ን ይመልከቱ።


[29]    ስለንጉሥ ሔሮድ እና በወቅቱ ስለነበረው ጥሩ መረጃ ተደርገው የሚወሰዱት የፍላቪዩስ ዮሴፍ ጂዊሽዋር ‘Jewish War’ እና አንቲኩቲስ ‘Antiquities’ ናቸው። ለነዚህ ስራዎች እንግሊዝኛ ትርጉም ዊስተን (1829)ን ይመልከቱ።


[30]    ለዝርዝር ቅኝት ከብዙ በጥቂቱ፣ ፓወል ማየር (1989)ን እና በዚያ የጠቀሱትን ስራዎች ይመልከቱ።


[31]    ማየር (1989፡124) የቀድሞ ስራውን በመጥቀስ እየሱስ የተሰቀለበትን ዕለተ ዓርብ አፕሪል 3፣ 33 ጋአ ያደርገዋል። እንደማየር (ዝኒከማሁ) ይህ ስሌትም የእየሱስ ልደቱ 5 ቅጋአ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ይሰጣል።


[32]    በዚህ በእየሱስ ልደት ቀን ስሌት ላይ ከብዙ በጥቂቱ ሬይመንድ ብራውን (1988)ን፣ ዱን (2003)ን እና በነዚህ የተጠቀሱ ስራዎችን ይመልከቱ።


[33]    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ይህ በሲቪሉ ዓመተ ምህረት የሚባለው ዓመተ ሥጋዌ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከታች እንመለስበታለን።


[34]           Era of Martyrs.


[35]           Anno Martyrum, commony abrivated as A.M.


[36]    የዚህ ሰው ስራ በቅርቡ ከግሪክ ወደ እንግሊዝኛ በዊሊያም አድለር እና ፓውል ቱፊን (2002) ተተርጉሟል።


[37]    ከላይ እንደገለፅንው ለግሪጎሪያኑን ዘመን መስራች የሚባለው ዲዮኒሱስ ምንጭ ሳይጠቅስ እንዳለ የፓኖዳሩስን ስራ እንደወስደ ዴኒስ ፔታው (Denis Petau 1630) ይገልፃል (በሞስሻመር 2008:357 ውስጥ)። ምንም እንኳ ከዚያ በኋላ የወጡ ስራዎች ይህን ላለመቀበል የተለያየ ምክንያት ቢፈጥሩም ዲዮኒሱስ ከፓኖዳሩስ መውሰዱ የሚያጠያይቅ አይደለም (ሞስሻመር 2008:357)።


[38]    5500 + 360-8 ÷ 532። አንድ ዑደተ ፋሲካ 532 የፀሀይ ዓመት ነው። ይህን ስሌት ለመጀመሪያ ግዜ ያስተዋወቀው እራሱ አኒያኑስ እንደሆነ ይነገራል (ኖታፍት 2012፡63)። የ532-ዓመት ዑደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ዓውደ ቀመር ይለዋል።


[39]           Epact.


[40]    ከግሪጎሪያን ዓመት በተሻለ ከፀሀይ ዓመት በጣም የቀረበ አቆጣጠር የግሪጎሪያኑ ከመፈጠሩም በፊት ሀሳብ ያቀረቡ አሉ። ለምሳሌ፣ የአስራ አንደኛው መቶ ክፍለዘመኑ (በአብዛኛው በግጥም ስራዎቹ የሚታወቀው) ኡመር ካያም ከግሪጎሪያኑ የተሻለ ለፀሀይ ዓመት የቀረበ አቆጣጠር አቅርቦ ነበር (ቴሬሲ 2002፡73)።


[41]   የጁሊየስ ቄሳር ዘመን አቆጣጠርን የለወጡት አንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች በ20ኛው ክፍለዘመን ነው። ዝርዝሩን ከሪቻርደስ (1998:248-249) ይመልከቱ።


[42]           ሰፋ ላለ ትንታኔ ሻው (2011)ን ይመልከቱ።


[43]    Asia Minor. ይህ አንዳንዴ አናቶሊያ በመባል የሚታወቀውን ባህረገብ ሀገር ‘peninsula’ ይመለከታል።


[44]           ሪቻርደስ (1998:159)ን ይመልከቱ።


[45]           Pelavius


[46]           Bunsen


[47]    ለዚህ ስራ እንግሊዝኛ ትርጉምና አንድምታ ጃኮብሰን (1939)ን ይመልከቱ።


[48]    “The .Egyptian priests in the:r computation of time do reckon above three and twenty thousand years from the reign of Sol, to the passage of Alexander the Great into Asia.

“In their fabulous stories they say, that the most ancient of their God’s reigned twelve hundred years, and the latter no less than three hundred years a-piece.” (ዲዮዶሩስ፣ ቡዝ እንደተረጎመው 1814: 32).

*** ዶ/ር ግርማ አውግቸው ደመቀ - የ "ዘመን አቆጣጠር፣ የቀናትና የወራት ስያሜ" መጽሐፍ ደራሲ ናቸው። በ girmaad@gmail.com ይገኛሉ።

 




Share

Published

Updated


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service