በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የኢትዮጵያና ኒውዝላንድ የማኅበረሰብ አባላት አማካኝነት "ለአገር ሞታችኋል፤ ምስጋና ያንሳችኋል" በሚል መሪ ቃል ለኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት ምሥጋና ለማቅረብ ዛሬ እሑድ ዲሴምበር 3 - 2021 የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
በውውይቱ ላይ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጊ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትና የመከላከያ ሠራዊት ዘመቻ መምሪያ ዋና ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው በተጋባዥ እንግድነት ተገኝተዋል።
ስብሰባውን በንግግር የከፈሉት አቶ በሪሁን ደጉ፤ በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለ ሙሉ ሥልጣን ሚኒስትርና ምክትል ሚስዮን መሪ የዕለቱን ፕሮግራም በማስተዋወቅ አስጀምረዋል። በስብሰባው ታዳሚዎችም የአንድ ደቂቃ የኅሊና ፀሎትም ተደርጓል።
አቶ በሪሁን በማያያዝም ለውጡ ካስገኛቸው ትሩፋቶች አንዱ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ካንብራ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ያላቸው ግንኙነት መነቃቃትና መሻሻል እንደሆነ ገልጠው፤ የማኅበረሰባቱ አባላት ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በገንዘብና በሙያ ያበረከቱትን አስተዋፅዖ በአብነትነት በመንቀስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Beryihun Degu Source: SBS Amharic
ከተጋባዥ እንግዶች በቀዳሚነት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት "የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ መቋቋም አንዱ የኢትዮጵያ መንግሥት በተቻለ መጠን እያደረገ ያለው የዜጋ መር ዲፕሎማሲ ማሳያ" እደሆነ ገልጠዋል። ለማኅበረሰቡ አባላት ባስተላለፉት መልዕክትም "አንድነታችሁን ጠብቃችሁ፤ በችግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለልማቱም በጋራ በመቆም የበለጠ ሥራ እንደምትመሩ እምነት አለኝ" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ "ኤምባሲውና በአካባቢው ያሉ የማኅበረሰብ አባላት ያደረጉትን የመድረክ ዝግጅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በራሴ ስም አመሰግናለሁ" በማለት ጀምረዋል።
አክለውም፤ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የሚገኙ የማኅበረሰቡ አባላት ለኮቨድ-19፣ ለኅዳሴ ግድብ አሁንም በሰብዓዊ ድጋፍ በኩል ያደረጉት አስተዋፅኦዎችን በመጥቀስ "እጅግ በጣም ነው የምንኮራባችሁ" በማለት ምስጋናና አድናቆታቸውን ገልጠዋል።

Selamawit Dawit Source: SBS Amharic

Ambassador Birtukan Ayano Source: SBS Amharic
የአገር መከላከያ ሠራዊት ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጊም በበኩላቸው "አገራዊ አንድነታችንን በሚያስጠብቅ፣ ሕዝባዊ አንድነታችንን በሚያስከብር መልኩ ከጎናችን በመቆማችሁ እናመሰግናለን። የሞራል ድጋፋችሁ ለሠራዊታችን ስንቅ ነው፤ ለዚያም ትልቅ አክብሮት አለን" ካሉ በኋላ አጋጣሚውን ተጠቅመው "መንግሥት በሚያደርገው ጥሪ መሠረት በሰብዓዊ አገልግሎት፣ በልማትና በሙያዊ ድጋፋችሁን እንድታደርጉልን ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ዘመቻ መምሪያ ዋና ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ለማኅበረሰቡ አባላት ባደረጉት ገለጣ " [የሕወሓት] የክልል ቢሮ ኃላፊና በሚኒስትር ደረጃ የነበሩ ከ10-12 የሚደርሱ እጃቸውን ሰጥተዋል። ተፈላጊዎቹ [የአመራር አባላት] የሚገኙት ተምቤን በረሃ ውስጥ ነው ያሉት። ሠራዊቱ 'እነሱን ሳንይዝ እንመለስም' በማለት 360 ዲግሪ እየፈተሸ ነው። ሕ ብለዋል።
ንግግራቸውንም ሲያጠቃልሉ "የእናንተ ጥረትና ድጋፍ ሠራዊቱ በጣም ደስተኛ ሆኖ ግዳጁን እንዲወጣ ስላደረገው ትልቅ ሚና አለው። ከልብ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" በማለት ተናግረዋል።

Marta Luwigi Source: SBS Amharic

B/General Tesfaye Ayalew Source: SBS Amharic
በመቀጠልም፤ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላትን በመወከል የቪክቶሪያ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ፕሬዚደንት አቶ ተስፋዬ እንደሻው ሲናገሩ "ባሕር ማዶ መኖራችን ኢትዮጵያዊነታችንን ቅንጣት አይቀረውም፤ ምናልባትም ይጨምረው ይሆናል እንጂ" ብለዋል።
በማከልም የማኅበረሰብ አባላቱ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ፣ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታና ለአገር መከላከያ ሠራዊት መርጃ ያበረከቱትን የገንዘብና የሙያ አስተዋፅኦዎች በመዘርዘር ገልጠዋል።

Tesfaye Endeshaw Source: SBS Amharic
ከንግግሩ ማብቂያ በኋላም ከማኅበረሰብ አባላቱ፤
- ጥፋተኞች ለፍርድ የሚቀርቡት እንዴት ነው?
- ሕወሓት አሸባሪ ተብሎ ያልተፈረጀው ለምንድነው?
- ሰላምና ጸጥታ በሌለበት ምርጫን እንዴት ማካሔድ ይቻላል?
- ሕግ የማስከበሩ እርምጃ ምን ያህል ተሳክቷል?
- ስለ ተያዙት፣ የተደመሰሱትና ያመለጡት ይፋ የማይደረገው ለምንድነው? የሚሉና በጎሳ የተደራጀው የልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ሠራዊት አባላት የወደፊት ዕጣ ፈንታ የተመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ጥያቄዎችን አስመልክቶ ተጋባዥ እንግዶቹ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤
ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ በሰጡት ምላሽ "አሁን ያለው ሠራዊት የጎሣ ሠራዊት አይደለም። ኢትዮጵያ ሠራዊት ነው። የሚዋደቀው ለጎሣውና ለመንደሩ አይደለም። በግሌ የክልል ልዩ ኃይል አያስፈልግም የሚል አቋም አለኝ። እንደ ተቋም ገና አልተነጋገርንበትም። ከአብዲ ኢሌ መማር አለብን። የአማራ ክልል ባለስልጣናት የተገደሉት በክልል ልዩ ኃይል ነው። ከፖሊስ ኃይል ጋር ቢቀላቀል ጥሩ ነው። ክልል ኃይል የሚባል ነገር ሊኖረው አይገባም የሚል አቋም ነው ያለኝ" ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ደኤታ ማርታ በበኩላቸው " የፀጥታ ኃይሉን በሚመለከት የክልልና ፌዴራልን አስመልክቶ የተናበበ አሠራር ለማካሔድ ጥናቶች እየተካሔዱ ነው። የጥናቱ ውጤት እንዳበቃም ማስተካከያ የሚደረግ ይሆናል። ይህን አስመልክቶ በመንግሥት በኩል ግንዛቤ አለ" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ብርቱካንም "አንድን ድርጅት በአሸባሪነት ለመፈረጅ የራሱ የሆነ ሂደት ስላለው በሂደት የሚወሰን ይሆናል። ቀዳሚው ጉዳይ ሕግን የማስከበሩ እርምጃ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።