የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ሊካሄድ ነው

***ከምርጫው ጋር አብሮ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲካሔድ ታቅዶ የነበረው የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ በተመሳሳይ በሰኔ 14 ቀን እንዲከናወን ተወስኗል።

Solyana Shimeles

Spokesperson of the National Election Board of Ethiopia (NEBE) Solyana Shimeles. Source: Getty

አስቀድሞ በኮሮና በመቀጠልም በመራጮች ምዝገባ መዘግየት ምክንያቶች የተራዘመውና ለግንቦት 28/2013 ሊካሄድ ታስቦ የነበረው 6ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

 ሐሙስ ግንቦት 11 በ ዴሊኦፖል ሆቴል ለአገር ውስጥና ዓለምአቀፍ ዘጋቢዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሶሊያና ሽመልስ እንዳሉት ቦርዱ በተቻለው መጠን በክረምት ምርጫ እንዳይካሄድ ጥረት ሲያደርግ የቆዬ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሲገፋ በመቆየቱ አንፃራዊ የዝናብ መጠን በማይበዛበት በሰኔ አጋማሽ እንዲካሄድ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ሶሊያና እንዳሉት ምርጫው በተወሰኑ አካባቢዎች ማለትም በፀጥታ ችግሮች ሳቢያ የመራጮች ምዝገባ በዘገየባቸው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋና ቄለም ወለጋ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሺና መተከል ዞኖች ብሎም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ምርጫው በሰኔ 14 አይካሄድም ብለዋል። እንደ ሶልያና ገለፃ በሌላ መልኩ ደግሞ  በመራጮች ምዝገባ ላይ ቅሬታዎች በተነሳባቸው አካባቢዎችም ምርጫው እንደማይካሔድ ተነግሯል፡፡ ሶልያና አክለውም ምርጫው የሚካሔድበት ቀን አለመወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ ሐረሪዎች የመምረጥ ጉዳይን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በፍርድ ቤት እንዲመርጡ የተወሰነላቸው ቢሆንም ቦርዱ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማለቱ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ላይከናወን ይችላል ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከምርጫው ጋር አብሮ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲካሔድ ታቅዶ የነበረው የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ በተመሳሳይ በሰኔ 14 ቀን እንዲከናወን መወሰኑን ተናግረዋል።

ሶሊያና እንዳሉት ምርጫውን ለማሳካትም አሁን በስራ ላይ ካሉት 138 ሺህ በላይ ምርጫ አስፈጻሚዎች በተጨማሪ አዳዲስ አስፈጻሚዎችን በመጨመር በድምሩ 245ሺህ አስፈፃሚዎች ይኖሩናል ፤ ስልጠናዎችንም በቅርቡ እንሰጣለን ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካና ዱባይ እየተከናወኑ ያሉት የቁሳቁስ ሕትመቶች በ10 ቀናት ተጠናቅቀው ስርጭቱን በአጭር ጊዜ ለማከናወንም የትራንስፖርት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል ቀርቧል ፤ የክልሎች ትብብርም እየተሻሻለ በመሆኑ ዕቅዱ መሰረት እንደሚከናወን ቦርዱ ተስፋውን ገልጿል።

ቁሳቁሶቹ በጥራትና ብዛት አትሞ የሚያቀርቡ አካል በአገር ውስጥ ማግኘት ባለመቻሉ እንዲሁም ለተለያዩ የደህንነት ስጋቶች በማይጋለጥ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዲውል በማሰብ በውጭ አገራት እንዲታተሙ መደረጉም ተገልጿል።

[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]

 


Share

Published

By Demeke Kebede

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service