ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ወደር ከማይገኝላቸው በጣት ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንዱ ነበሩ:: ከሰባት አስርተ አመታት በላይ በግዕዝ ቋንቋ ምርምርና ትርጉም ፤ በገዳማትና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥልቅ የሆነ ምርምር በማካሄድ ብዙ መፃህፍትንና የምርምር ፅሁፎችን ለትውልድ አበርክተዋል:: ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ወደር የማይገኝላቸው የታሪክ ሊቅ ብቻ ሳይሆኑ ለሀገራቸው አርበኛም ነበሩ::
ከምርምር ስራቸው ባልተናነሰ ኢትዮጵያ የተሻለ ስርአተ መንግስት እንዲኖራት በተደረጉት እልህ አስጨራሺ ጥረቶች ሁሉ ከግምባር በመሆን አቅጣጫ በማመላከትና በማስተባበር እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ የላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል:: ፕ/ር ጌታቸው እጅግ ለሚወዷት አገራቸው ኢትዮጵያና ለትውልድ ያስተላለፉት ቅርስ በጣም ጥልቅና በርካታ ነው:: እርሳቸው ከሚጠበቅባቸው በላይ አበርክተው አልፈዋል::
ዋናው ጥያቄ የአሁኑና መጪው ትውልድ ይህንን የእርሳቸውን አደራ ተቀብሎ አርያቸውን ተከትሎ አገርንና ታሪክን በአግባቡ የመጠበቅና ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት በብቃት የመወጣት መሆን ይኖርብታል ብሎ ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት በፅኑ ያምናል:: የፕሮፌሰር ጌታቸው እውቅ ስራወችም በትውልዱ እንዲሰርፁና እንዲዘከሩ ህብረቱ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል::
በተለይ በአሁኑ ወቅት የአገራችን ጥንተ ታሪክ እኩይ በሆኑ የፓለቲካ ኃይሎች በሀሰት ትርክት እየተበረዘ ባለበት አስጊ ሁኔታ የፕሮፌሰር ጌታቸውና መሰል እውነተኛ ምንጮች በመጠቀም የቀረቡ ስራወች ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ተፈላጊነታቸው የጎላ ነዉ:: ከዚህም የተነሳ ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት የኢትዮጵያም ሆነ የአማራው ታሪክና ስልጣኔ በተገቢው ሁኔታ ትውልድ እንዲያውቀው ፤ እንዲጠብቀውና: ለመጪው ትውልድም ማስተላለፍ እንዲችል የሚያግዝ ስራ መጀመር ብቻ ሳይሆን በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥልበት ቃል ይገባል::
ይህን በማድረግ ፕ/ር ጌታቸው ለትውልዱ ያስተላለፉትን አደራ ለመወጣት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ምሳሌ ይሆናል:: በእውነት ኢትዮጵያ ትልቅ ሰው ፣ትልቅ ሊቅ አጣች:: ስራወቻቸው ግን ህያው ሆነው በትውልድ ሲዘከሩ ይኖራሉ:: ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ቤተሰቦች፣ ጏደኞች፣ የስራ ባልደረቦችና: ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ይመኛል::
ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑርልን:: ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት (Global Amhara Coalition)