አዲስና አንጋፋ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመረቁ

*** ከአዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአራት ኮሌጆች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመደበኛ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 501 ወንድ እና 353 ሴት ተማሪዎቹን አስመርቋል

Graduation ceremony

Graduation ceremony Source: Demeke Kebede

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አንጋፋና አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመርቀዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በተለምዶ ሰኔና ሐምሌ የሚያስመርቁ ቢሆንም በኮቪድ 19 የተነሳ ትምህርት በመቋረጡ በመልሶ ቅበላ የተቋረጠውን አካክሰው ነው ከታህሳስ መጨረሻ ጀምሮ ብዙዎቹ በያዝነው የጥር ወር እያስመረቁ የሚገኙት።

  • ጎንደርዩኒቨርሲቲ
አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ  በተለያዩ መርሐ ግብሮች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ፣ በሦስተኛ ዲግሪ፣ በስፔሻሊቲ እና ሰብ-ስፔሻሊቲ ኘሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ከ7000 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የተለያዩ የክብር እንግዶችና ወላጆች በተገኙበት የምርቃት ስነ ስርዓት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶክተር አስራት አፀደወይን "የዚህ ዓመት ተመራቂዎች በርካታ የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን እና ውጣ ውረዶችን አልፈው ለዚህ የበቁ በመሆናቸው ከሌሎች ጊዜያት ተመራቂዎቻችን ልዩ ያደርጋቸዋል" ብለዋል።

  • ደብረማርቆስዩኒቨርሲቲ
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ12ኛ ዙር ዛሬ ጥር 15 ተማሪዎቹን አስመርቋል። ነገ ጥር 16/2013 ዓ/ም ቀሪዎቹን ያስመርቃል።

ዩኒቨርስቲው በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 3 ሽህ 893 ተማሪዎችን ነው ያስመርቀው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሬት አስተዳደር ዘርፍ ያስተማራቸውን 30 ተማሪዎችም ለምረቃ ያበቃል፡፡

በዛሬው የዩኒቨርሲቲው ምርቃት የተዘጋጁትን የላቁ ተማሪዎች ሽልማቶች ሴት ተመራቂዎች ሁሉንም ዋንጫዎችና ሜዳልያዎች ወስደዋል፡፡

  •  እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ
በ2010 ማስተማር የጀመረው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ የመጀመሪያ ምርቃቱን አከናውኗል። በ4 ኮሌጆች ስር በሚገኙ 21 ትምህርት ክፍሎች ያሰለጠናቸው 525 ወንድ እና 432 ሴት በድምሩ 957 ተመራቂ ተማሪዎችን ነው ዛሬ ያስመረቀው።

በዛሬው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የተማሪ ወላጆች ፣ ቤተሰቦች፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ፣ አርቲስት ታማኝ በየነ፣ ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ተብሏል።

  • ደብረብርሃንዩኒቨርሲቲ
የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ለ12ኛ ጊዜ በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 3 ሽህ 284 ተማሪዎች ነገ እሑድ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በሦስተኛ ዲግሪ ያስመርቃል፡፡

  • ወራቤዩኒቨርሲቲ
ወራቤ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዙር ተመራቂ  ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

በ5 ኮሌጆች ስር  በሚገኙ በ14 ፕሮግራሞች በመደበኛው መርሃ-ግብር ወንድ-629  ሴት- 503  በድምሩ 1,132  ትምህርታቸውን ከተከታሉት ውስጥ 1077 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።

  • ጂንካዩኒቨርሲቲ
ከአዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው የጂንካ ዩኒቨርሲቲም ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎቹን አስመርቋል።

ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአራት ኮሌጆች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመደበኛ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 501 ወንድ እና 353 ሴት በድምሩ 854 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።

[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]


Share

Published

Updated

By Demeke Kebede

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service