በስፔን ማድሪድ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው በ24 ኛው የአለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ወንጪ ሐይቅ የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጡ ትናንት ይፋ ተደርጓል።
በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ከ170 የቱሪዝም መንደሮች መካከል ቀዳሚ ሆኖ በጉባኤው መመረጡ ላይ ይፋ የተደረገው።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር ያለው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ፥ ወንጪ ሐይቅ በዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ በመመረጡ ደስታቸውን ገልጠዋል።

ድንቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የሆነው የወንጪ ሃይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ የተመረጠው ባለው ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት መሆኑን ገልፀዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ሚኒስትሯ ፥ የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ ተንከባክበው ለዚህ እንዲበቃ ላስቻሉት የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

