ወደ አገር ቤት ለሚመጡ አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ሆቴሎች 30 በመቶ ቅናሽ እንደሚያደርጉ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ
ዓለም አቀፍ ጫናውን ለመቀነስና የኢትዮጵያን በተለይም የአዲስ አበባን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማሳየትና በዚያውም የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ ለማስገኘት ዓላማ ያደረገ የ”አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት” ጥሪ በኢትዮጵያ መንግስት መተላለፉ ይታወቃል፡፡
ይህንን ጥሪ ተክትሎ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ድምጽ ሆነው አገራቸውን እየደገፉ ነው ብለዋል፡፡
ከታህሳስ ወር ጀምሮ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ለዚህም የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻ ጋር በተደረገው ውይይትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በአዲስ አበባና በክልሎች የሚገኙ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች እና አስጎብኚዎች እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የአገልግሎት ቅናሽ ለማድረግ መስማማታቸውነን ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡
(ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ)