አውስትራሊያ በኮሮናቫይረስ መንስኤ ላይ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲካሔድ ግንባር ቀደም ጠንካራ አቋም አሳይቻለሁ ያለችውን ቻይና "ቧልት" ስትል አጣጣለች።
ሰኞ ምሽት በዓለም የጤና ጉባኤ ላይ የታደሙ 110 አገራት ምርመራው እንዲካሄድ በጋራ ባቀረቡት ረቂቅ ውሳኔ ላይ ቻይና የስምምነት ድጋፏን ሰጥታለች።
የዓለም ጤና ጉባኤ በውሳኔው ላይ ወረርሽኙን ተከትሎ የተከወኑ ዓለም አቀፍ ግብረ ምላሾችን ዘመምተኛ ያልሆነ፣ ነፃና ሁሉን አቀፍ ግምገማ እንዲደረግ ወስኗል።
የአውስትራሊያ የቫይረሱ አነሳስ ላይ ምርመራ ይካሄድ ብሎ መግፋት ከቤጂንግ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብርቱ ለሆነ ውጥረት ዳርጎታል።
በአውስትራሊያ የቻይና አምባሳደር በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ የዓለም ጤና ጉባኤ አውስትራሊያ ካቀረበችው ረቂቅ የምርመራ ዕሳቤ የተለየ መሆኑን ጠቁመው፤ የዓለም ጤና ጉባኤ ውሳኔን የአውስትራሊያ ማስመሰሉ "ቧልት" ነው ብለውታል።
በሌላ በኩል የአውስትራሊያ ግብርና ሚኒስትር ዴቪድ ሊትልፕራውድ "ይህ ክስ ሳይሆን፤ 300 000 ሕይወቶችን ስለ ቀጠፈው ወረርሽኝ ግንዛቤን ለመጨበጥ ነው" ሲሉ የአውስትራሊያን የምርመራ ይካሄድ አቋም ዛሬ ረቡዕ ከቀትር በፊት ገልጠዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ግምገማው በተቻለ መጠን ቀደም ብሎ እንደሚከናወን ቃል ገብቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የSBS/AAP ዜናን አጣቅሰው ምርመራው እንዲካሄድ ድጋፋቸው መቸራቸውን በቲዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ትናንት ሰኞ ማምሻውን በተካሄደው የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ ቻይና ለኮቪድ - 19 መከላከያና በምጣኔ ሃብትና ማኅበራዊ ዕድገት ለተጎዱ አገራት በተለይም ለታዳጊ አገራት ማንሰራሪያ የሚውል 2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላርስ መመደቧን ፕሪርዚደንት ሺ አስታውቀዋል።

