ዛሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው መግለጫቸው እንደተናገሩት "ተቋርጦ የሰነበተው የህዳሴ ግድብ የሶስቱ አገራት ድርድር ተጀምሯል። በተፈለገው መልኩ ስምምነት ላይ አለመደረሱ እጥረት ነው። በተለይ በአፍሪካ ኤክስፐርቶች ሚና ላይ አልተስማማንም" ብለዋል።
አምባሳደር ዲና " የአፍሪካ ኤክስፐርቶች ሚና ከፍ እንዲል የተፈለገው የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ነው በሚል ሲሆን ኢትዮጵያና ሱዳን የተስማሙ ሲሆን ግብፅ ሃሳቡን አልተቀበለችውም። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኤክስፐርቶች ሚና ለአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ትልቅ ሚና ስላለው ነው።" ሲሉ አብራርተዋል።
በወቅታዊው የህወኃትና የማዕከላዊው መንግስት ጦርነት ጉዳይ ብዙ መረጃ ለመስጠት የተቆጠቡት ቃል አቀባዩ በደፈናው "የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች በወቅታዊው ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጎን ናቸው። ኤርትራ፣ ሱዳን ፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የኛም ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።" ያሉ ሲሆን ጥልቅ መረጃዎችን ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ማግኘት ይቻላል ብለዋል ለጋዜጠኞች።
አምባሳደር ዲና " አንድ የማረጋግጥላችሁ ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ እየተደረገ ያለው ውጊያ ከህወኃት ጋር እንጂ ከህዝቡ ጋር አይደለም።" ሲሉ ተናግረዋል።
ደመቀ ከበደ፡
አዲስ አበባ