ለብዙዎቻችን፣ ይህ ትጥቅ መፍታት የሚሉት ነገር፣ አንዴ በመንግሥትና በዓማጽያን መካከል ስምምነት ከተደረሰ፣ ታጣቂዎቹ ወዲያውኑ ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ ይመለሳሉ የሚል የተሳሳተ ግምት ይሠጣል።
በስምምነቱ ተፈጻሚነት ሂደት ሊከተል የሚችለው ችግር ግን ከሚገመተው በላይ መጠነ ሰፊ ስለሆነ፣ በቀላሉ ትጥቅ ተፈትቶ ሰላም ይሰፍናል ብለን እያሰብን ሂደቱ ሲጓተትና ጠብመንጃና ወጣቱን ማለያየት ሲያቅተን፣ እርስ በርስ መወቃቀስንና አለመተማመንን ያስከትላል።
ስለሆነም፣ ይህንን የሰሜኑን ትጥቅ መፍታትና መልሶ የማቋቋም ሂደት ያጋጠመውን ችግር በውል ማወቁና ከዚያ የሚቀሰመው ልምድ፣ ለወደፊት መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) እና ከፋኖ ጋር ለሚያደርገው ውይይትና ድርድር አዎንታዊ አስተዋጽዖ ስለሚኖረው የትጥቅ መፍታትና መልሶ የማቋቋም ተግዳሮቶችን ከወዲሁ ማወቁ ጠቃሚ ነው የሚል ግምት አለኝ።
ማኅበረ ሰባዊ አለመግባባት ወይም ግጭት ለሰው ልጅ አዲስ አይደለም። በፍጥረት ለምናምን ሰዎች፣ ይህንን ዛሬ ብዙ ቢሊዮን ሕዝብ የሚኖርባትን ምድር ሲገዟት የነበሩት አራት ፍጡራን፣ ማለትም አዳም፣ ሔዋን፣ ቃየልን አቤል ብቻ በነበሩበት ዘመን እንኳ “ምድሩ ጠቧቸው”፣ አቤልና ቃየል ተጣልተው ቃየል አቤልን ገደለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ እየተጋጨና እየተዋጋ እየተገዳደለ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ አብዛኞቹ በኤኮኖሚያቸው ያደጉ አገራት ግን ሠልጥነው አለመግባባቶቻቸውን በጠብመንጃ ሳይሆን በውይይት የመፍታት ደረጃ ላይ ደርሰው፣ ከተዋጉም ደግሞ፣ ጦርነቱን የሚያቆሙት አብዛኛውን ጊዜ ቂምን በማያስከትል መልኩ በሰላማዊ ድርድር ነው።
ይኸው ዘግይተንም ቢሆን፣ ዛሬ እኛም “ከቀረ የዘገየ ይሻላል” ብለን አለመግባባትን በሰላም ፈትተን ተዋጊ ኃይላት ትጥቃቸውን ፈትተው በክብር ወደ ማኅበረሰባቸው ለመመለስ በባሕላችን እምብዛም ያልተለመደውን “ከጠላት” ጋር በእኩልነት ተቀምጦ መደራደርና ብሎም የመስማማትን ሂደት አሓዱ ብለን ጀመርን።
ታላቅ የታሪክ ክስተት!
ዓማጽያንን ትጥቅ የማስፈታት (Disarmament)፣ ከግጭት ቀጠና ማግለል (Demobilization) እና ወደ ሰላማዊው ማኅበረ ሰብ መልሶ ማቋቋምን (Re-integration) በተግባር መተርጎም እጅግ በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው።
በመሠረቱ በማንኛውም የግጭቶች ጊዜ ድርድር ወይም ውይይት ሂደት ውስጥ እጅግ በጣም አወዛጋቢውና የውይይቱ ምሰሶ የትጥቅ መፍታቱ ጉዳይ ነው ቢባል የተጋነነ አይደለም። ምክንያቱም፣ ትጥቅ በማስፈታቱ ሂደት ውስጥ አንዳች ቦታ ላይ ስሕተት ከተፈጸመ፣ ታጣቂዎቹ ዳግም ነፍጥ አንስተው ወደ ተላመዱት “የጫካ” ሕይወታቸው ለመመለስ ቅጽበታዊ ውሳኔ ላይ ሊደርሱ ይችላሉና!
ከጥቂት ዓመታት በፊት የኦነሠ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ አንድ በደንብ ያልተጠናበት ውሳኔ ላይ ተደርሶ፣ የተወሰኑ ታጣቂዎችን ትጥቅ ካስፈቱ በኋላ፣ በሂደቱ ብቻ ሳይሆን ከመሠረቱ ውሳኔው የተደረሰበት ሂደት የተሳሳተ ስለነበር፣ ታጣቂዎቹን መልሶ የማቋቋሙ እንቅስቃሴ እንደ ታቀደለት በተግባር ሊተረጎም አልተቻለም።
ዓማጽያኑ ወጣቶች የወሰዱትና እየወሰዱ ያሉት እርምጃ ትክክል ነው ወይም አይደለም ብሎ መከራከር አሁን ቦታው አይመስለኝም። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም እርምጃቸውን ለማወደስ ወይም ለመኮነን አይደለም። ዓላማዬ፣ የትጥቅ ትግል (በመሠረቱ የእርስ በርስ ግጭት ነው) በማኅበረ ሰብ ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ለመዳሰስ፣ ወጣቶቹን ለትጥቅ ትግል የሚገፋፋቸውን ምክንያት ለማወቅና፣ አንድ ቀን ስምምነት ላይ ሲደረስ ደግሞ ወጣት ዓማጽያንን ወደ ሰላማዊ ማኅበረ ሰብ መልሶ ለማቋቋም ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮችና ተጓዳኝ መፍትሔዎችን ለመጠቆም ነው።
1) የትጥቅ ትግል እና ማኅበረሰባዊ አደጋው፣
የትጥቅ ትግል በሚል የሚታወቀው የእርስ በርስ ግጭት በቀላል አማርኛ የአንድ አገር ዜጎች በሃሳብ ሳይስማሙ ሲቀሩና ባለመስማማታቸው ተስማምተው ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በሰላም አብሮ መኖር ሲያቅታቸው ወይም ሳይፈልጉ ሲቀሩ፣ በጠብመንጃ ድጋፍ የሃሳብን አሸናፊነት በተግባር ለማዋል የሚደረግ የመገዳደል ድርጊት ነው።
በዚህ የግድያ ወንጀል፣ ተፋላሚ ወገኖች የሚያሳትፏቸው አብዛኛውን ጊዜ ወጣቱን ትውልድ ነው። በተፈጥሮ ምክንያት ሴቶች፣ ሕጻናትንና አዛውንቶችን ወደ ትጥቅ ትግል መጋበዙ አመቺ ስላልሆነ፣ ተፋላሚ ወገኖች ያለ አንዳች ማመንታት ለትጥቅ ትግል አብዛኛውን ጊዜ የሚመለምሉት ወጣቱን የማኅበረ ሰብ አባላትን ነው።
በሰላሙ ጊዜ አምርቶ የራሱን፣ የቤተ ሰቡንና የማኅበረ ሰቡን አባላትን ቁሳዊ ፍላጎት የሚያሟላውን ወጣት ወደ ግድያው ሜዳ ማሠማራት በተለይም ደግሞ ግጭቱ ከተራዘመ ማኅበረ ሰቡን ለረሃብ ይዳርጋል፣ አዛውንት እንክብካቤ ያጣሉ፣ ሚስቶች ባሎቻቸውን፣ እናቶች ልጆቻቸውን ያጣሉ፣ ብዙ ወጣቶች ይገደላሉ፣ ቀባሪ ጠፍቶ የዱር አውሬ ሲሳይ ይሆናሉ።
በአብዛኛውን ጊዜ ወላጆች የልጆቻቸውን መኖር ወይም መሞት ስለማያውቁ አልቅሰው እርም ስለማይወጣላቸው፣ ዘላለማቸውን ውጭ ውጭ ሲያዩ ይኖራሉ።
አብዛኛው ወጣት ጠብመንጃ አንግቶ በየዱሩ ሲዟዟር የቀን ተቀኑን ምግብ የሚያገኘው በአደን አለያም በዘረፋ ስለሆነ ማኅበረሰቡን የማስቀየም ዕድሉ የሰፋ ነው። ተፈጥሮያዊ ፍላጎትን ለማርካት ከማለት ከማኅበረ ሰቡ ባሕላዊ እሴት ውጪ ሴቶችን አስገድደው ይደፍራሉ፣ ሌላም ሌላም።
ይህንን መስመሩን የሳተውን ማኅበረ ሰባዊ ቀውስ ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ እጅግ በጣም አዳጋች ይሆናል። ከእርስ በእርስ ግጭት በኋላ የሚወረሰው ማኅበረ ሰብ፣ ወጣቱ የተገዳደለበት፣ ማኅበረ ሰባዊ እሴቶች የፈረሱበት፣ ሕጻናት ያለ አባት፣ ሚስቶች ያለ ባሎቻቸው፣ ወላጆች ያለ ልጆቻቸው የሚያድጉበት፣ ወጣት ልጃገረዶች ተደፍረው የአእምሮ ጠባሳ ከማስተናገድም በላይ በሕጻንነት ዕድሜያቸው አባት አልባ ሕጻናትን የሚያሳድጉበት ማሕበራዊ መስተጋብሩ የፈራረሰ ዝብርቅርቁ የወጣ በደም የተጨማለቀ ማኅበረ ሰብ ነው።
ከቅርቡ የትግራይ ጦርነት በኋላ የትግራይ ሕዝብ ዛሬ ያለበትን ሁኔታ ያየ ሰው፣ የእርስ በርስ ግጭት መጨረሻው በአጭሩ ይህንን እንደሚመስል አጥብቆ ይረዳል። በዚህ አሸናፊና ተሸናፊ በሌለበት የእርስ በርስ መገዳደል በኋላ አንዳች ስምምነት ላይ እንኳ ቢደረስ፣ ፖሊቲከኞች አንጻራዊ ድልን ይጎናጸፉ (ባዶ ድል) እንደሆን እንጂ ሰፊው ሕዝብ ግን መቶ በመቶ ተሸናፊ ነው።
በየእርስ በርስ ጦርነት ጊዜ ከነፍስ መጥፋት ቀጥሎ የሚጎዳው የኤኮኖሚ ዘርፉ ነው። ጦርነት በተፈጥሮው አውዳሚ ስለሆነ፣ ተፋላሚ ኃይላት አንዳቸው በሌላው ላይ የበላይነትን ለመጎናጸፍ፣ በተቻላቸው መጠን በእጃቸው የሚገኘውንና ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ማንኛውንም የጥፋት መሳርያ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም።
ተፋላሚው ወገን ይጠቀምበታል ብለው የሚያስቡትን ለምሳሌ፣ አውራ መንገድ፣ ድልድይ፣ ሕንጻዎችን ያፈርሳሉ። ለራሳቸው ሊጠቀሙበት ካልቻሉ፣ ሰብልና መንደርን ያቃጥላሉ። ውሃ ይመርዛሉ፣ ተሽከርካሪዎችን ያቃጥላሉ፣ ለጥቃት መሣሪያዎች መገልገያ ይውላሉ ተብለው ከተገመቱ የጋማ ከብቶችን ሳይቀር ይገድላሉ፣ ሌላም ሌላም።
በብዙ ቦታዎች ደግሞ፣ ተፋላሚ ኃይላትን ለመቅጣት ከማለት መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እንኳ ተፋላሚው ኃይሉ ወደሚቆጣጠራቸው ግዛት እንዳይደርስ ስለሚያደርግ፣ ሕጻናት ሴቶች እና አዛውንት ለረሃብ አደጋ ይጋለጣሉ። ዓሳውን ለመግደል ባሕሩን ማድረቅ ያዋጣል ተብሎ፣ ሰላማዊው ማኅበረ ሰብ ለዓማጽያን ድጋፍ እንዳይሠጥ ከማለት ከቄያቸው ይፈናቀላሉ።
በግጭቱ ምክንያት ትምሕርት ቤቶች ይስተጓጉላሉ፣ ይዘጋሉ። መምህራን ይታሠራሉ፣ ይገደላሉ። አንድ ቀን ስምምነት ላይ እንኳ ቢደረስ፣ ማኅበረ ሰቡ የሚወርሰው፣ ሜዳው በጤፍና ማሽላ ምርት ሳይሆን በሰው ልጆች አጽም የተሸፈነ፣ ትምህርት ቤቶች የተፋላሚ ኃይላት መምርያ ቢሮዎች ሆነው፣ በዘመናዊ የሳይንስ ዕውቀት ሳይሆን ያደጉ አገራት አምርተው እንዲገዳደሉበት በሚያቀብሏቸው ዘመናዊ የመገዳደያ መሣርያ የታጠቀና ጠብመንጃ አፍቃሪ ወጣት ይሆናል። ሌላም ሌላም!
በእርስ በርስ ግጭት ወቅት ተፋላሚዎቹ የአንድ አገር ሕዝቦች በመሆናቸው፣ ገዳዩም ሟቹም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጥልቁ የሚተዋወቁ ናቸው። የእርስ በርስ ግጭት ከውጪ ወራሪ ኃይል ጋር ከሚደረገው ጦርነት ይበልጥ ውጤቱ እጅግ በጣም ጎጂ የሚሆነው፣ ተፋላሚዎቹ በሰላሙ ጊዜ የእርስ በርስ ጓዳን በደንብ ስለሚተዋወቁ፣ በግጭቱ ወቅት የሚጎዳዱት እስከ ጓዳ ድረስ ስለሆነና በጣም የሚቀራረቡ ሰዎች የሚጠፋፉበት ክስተት በመሆኑ ነው።
ከግጭት በኋላም አንድ ቀን አንጻራዊ ሰላም እንኳ ሰፍኖ ተፋላሚ ኃይላት ወደ ቀድሞ ሠፈራቸው ሲመለሱ በየዕድሩ፣ በየአብያተ ክርስቲያናትና በመስጊዶች የሚያገኟቸው ቀድሞ ጎረቤት የነበሩ ሰዎችን ስለሆነ፣ በተገናኙ ቁጥር አንደኛው ወገን በሌላኛው ላይ ያደረሰው በደል ሁልጊዜ እንዳገረሸ ይቀራል።
ከሰላሳ አምስት ዓመት በፊት በሴሬብሬኒሳ (ቦስኒያ) የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በፈጸሙ ሴርቦችና ስምንት ሺህ ልጆቻቸው በአንድ ቀን ተገድለው በጅምላ የተቀበሩባቸው ቦስኒያኮች፣ ዛሬም ሴርቦችን በጠላትነት ዓይን ስለሚያዩአቸውና፣ ከጦርነቱ በፊት የነበረው ወዳጅነትና ዝምድና እንዳይመለስ ሆኖ ስለፈረሰ፣ ውሃና ዘይት ሆነው ጎን ለጎን እየኖሩ ነው።
ግጭቱ ከውጪ ወራሪ ኃይል ጋር ቢሆን ኖሮ ግን፣ ቁስሉ በቶሎ ይድን ነበር። ኢትዮጵያን ወርሮ መቶ ሺ ሕዝቦቻችንን ከጨረሰቡን ሱማሌዎች ጋር ዛሬ የጠለቀ ጠላትነት ስሜት አናስተናግድም። በተቃራኒው ግን፣ ለምሳሌ በአንዳንድ የብሔር ፖሊቲከኞች ዘንድ ጣሊያኖች የዛሬ ሰማኒያ ዓመት በሕዝቦቻችን ላይ ካደረሱባቸው ዘግናኝ ጭፍጨፋና ተጓዳኝ ግፍ ይልቅ አጼ ምኒልክ የዛሬ ሁለት መቶ ዓመት የፈጸመባቸው በደል የበለጠ ይጠዘጥዛቸዋል።
2) ወጣቱን ነፍጥ አንግቦ ጫካ እንዲገባ ከሚያደርጉ ገፊ ምክንያቶች ጥቂቶቹ፣
ወጣቱን ከመጀመርያው ምን ቢገፋፋው ነው ነፍጥ አንግቦ ለሆነ ዓላማ ስኬት ከማለት የገዛ ወገኑን ለመግደል ወደ ጫካ የሚሄደው የሚለውን ጥያቄ ባጭሩም ቢሆን መመለሱ፣ አንድ ቀን ግጭትን ለማቆም በተፈላሚ ወገኖች መካከል ስምምነት ላይ ቢደረስ፣ የቀድሞ ዓማጽያንን ከትጥቃቸው ለይቶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለሱን ሂደት ያቀልላል።
በሌላ አነጋገር ወጣቱ ከመጀመርያው ለምን ወደ ጫካ እንዳመራ (ያነሳ የነበረውን ጥያቄ ወይም ቅሬታ) በትክክል ታውቆ በድርድሩ ሂደት አጥጋቢ መልስ ካልተሠጠው በስተቀር፣ ወጣቱ በቀላሉ ከጠብመንጃው ተላቅቆ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ይመለሳል ተብሎ አይጠበቅም።
የሰው ልጅ ያለ ምክንያት መሰል ፍጡርን ለመግደል ከቄዬው ተሰናብቶ አይወጣም። በቂም ይሁን አይሁን የሆነ ምክንያት ይኖረዋል። ምክንያቶቹ በቂ ይሁኑ አይሁኑ ጥልቅ ምርመራ ውስጥ ሳንገባ በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ወጣቱን ትውልድ ለዓመጽ ወደ ጫካ እንዲያመሩ ከሚገፋፏቸው ብዙ ምክንያቶች ጥቂቶቹን ማንሳት በቂ ይመስለኛል።
ሀ) አለ መግባባትን በውይይት የመፍታት ባሕል አለ ማዳበር (የጉልበት/የአሸናፊ ፖሊቲካ)
ሳያድለን ቀርቶ፣ ተማሩ በምንላቸው ያገራችን ምሁራንና ኤሊት መካከል እንኳ ሳይቀር፣ የሃሳብ ልዩነትን አቻችሎ በአንድ ጥላ ሥር ሆኖ ለትልቁ አገራዊ የጋራ ዓላማ መተባበር በአገራችን ከቶውኑም የማይገኝ ውድ ሸቀጥ ነው።
በአካደሚክ ትምሕርት እስከ ኅዋ ድረስ የሚያስመጥቅ ዕውቀት ቀስመው፣ ኃያሉን ተፈጥሮን ከተቻለ ለመቆጣጠር፣ ካልተቻለ ደግሞ አብሮ ለመኖር ሳይንሳዊ መፍትሔ ለማግኘት ሌት ተቀን የሚጥሩ ምሑሮቻችን ሳይቀር፣ ዝቅተኛ የዲሞክራሲን ሀሁ እንኳ መማር አቅቷቸው፣ ሕዝቦቻችን ልዩነቶቻቸውን አቻችለው አብሮ መኖር እንዳለባቸው ሊያስተምሩ አልቻሉም ወይም አይፈልጉም። ሁላቸውም በትርፍ ጊዜያቸው የሰላምን ሳይሆን የጦርነትን ነጋሪት ይጎስማሉ።
እነዚህ በትምሕርት የላቁ ወገኖቻችን አገራዊ ቀውሶቻችንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የማይፈልጉ ወይም የማይችሉ መሆናቸውን ቆሞ የሚያስተውለው ወጣቱ ትውልድ ደግሞ፣ እሱም በተራው ከተፋላሚው አካል ጋር ያለውን የሃሳብ ልዩነት በሠለጠነ መንገድ ፈቶት ተቻችሎ ለአንድ የጋራ ዓላም ከመቆም ይልቅ፣ ልክ እንደ እኛው አንጋፋዎቹ፣ አለመግባባትን በጠብመንጃ ብቻ ለመፍታት ነፍጥ አንግቶ ወደ ጫካ ያመራል።
ለ) የሕግ የበላይነት አለ መከበርና የዜጎች መብት በሰፊው መጣስ፣
ዜጎች ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው ሲጣሱባቸውና አቤት የሚሉበት የፍትሕ ጎዳና ሲጠብባቸው፣ በመንግሥትና በዜጎች መካከል ያለው ማኅበረ ሰባዊ ውልና የሕግ የበላይነት ይሳሳል፣ ይሸረሸራል፣ ይፈርሳል። የሕግ የበላይነት ከሌለ ደግሞ፣ የግልና የቡድን መብቶች በገፍ ይጣሳሉ። ዳኛ የሚወስነውን ፖሊስ ይሽረዋል። ዜጎች ያለ አንዳች የፍርድ ቤት ውሳኔ ይታሠራሉ፣ ቤታቸው ይበረበራል። ግለ ሰቦች የታሠሩበት ቦታ ሳይታወቅ ወራት ያልፋሉ።
ለዚህ ዓይነት ጥቃት ከሁሉም በላይ የሚጋለጠው ደግሞ ወጣቱ ነው። የሆነ ታጣቂ / ተቃዋሚ ኃይልን ትደግፋለህ ተብሎ በገፍ ይታሠራል፣ ይገረፋል፣ ይገደላል። ሌላም ሌላም። ይህንን ሁሉ ግፍና የመብቶች ጥሰትን ቆሞ የሚያስተውለውና፣ ገፈቱን በመጀመርያ ረድፍ ሆኖ የሚቀምሰው ወጣት፣ “ቤቴም ሆኜ የግሌም ሆነ የቡድኔ መብቴ የማይጠበቅልኝ ከሆነና ባልሠራሁት ወንጀል ተጠርጥሬ በየፖሊስ ጣቢያው በግፍ መሠቃየቴ ካልቀረ፣ ነፍጥ አንስቼ በሕግ የተደነገገልኝንና ተፈጥሮ በነፃ የለገሠኝን ሰብዓዊ መብቴን በጉልበት አስከበራለሁ” ብሎ መብት ጣሹን መንግሥት ለመዋጋት ጫካ ይገባል።
ሐ) ተምሮ ሥራ ማጣት፣ ብሩኅ ነገን አለማየት፣
የአገራችን የኑሮ ውድነት ከሁሉም በላይ እየጎዳው ያለው ተምሮ ሥራ አጥቶ በፊንፊኔና በየክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እንደ ጎርፍ የሚፈሰውን ወጣት ነው። ማትሪክ የወደቁ ወጣት ልጆችን ተቀብሎ ሙያዊ ዕውቀት ሊሠጥ የሚችል የሙያ ሥልጠና ትምሕርት ቤቶች ባለመስፋፋታቸው፣ ሴቶች በአብዛኛው ወደ ዓረብ አገር ተሰደው ለግርድና ሲዳረጉ፣ ወንዶች ደግሞ መሄጃ ጠፍቷቸውና ብሩኅ ነገ አልታይ ስላላቸው፣ ወላጅ ጋ ተመልሶ ሸክም ላለመሆን ወይም በወንጀል ድርጊት ከመሠማራት ከማለት ዓማጽያን ወዳጆቻቸውን ተቀላቅሎ “ለዓላማ” ለመዋጋት ከማለት ጠብመንጃ አንስተው ወደ ጫካ ይገባሉ።
መ) የታጣቂ ኃይላት የምልመላ እንቅስቃሴ
ብሩኅ ነገን አጥሮ በየጎዳናው የሚዋትተው ወጣት፣ መንግሥትን ለሚገዳደሩ ዓማጽያን በቀላሉ የሚጠመድ ዓሳ ነው። በቀሰመው ትምሕርት የሥራ ዕድል አግኝቶ፣ ራሱንና ወላጆቹን ለመርዳት ላልታደለው ወጣት፣ “ለአንድ የሆነ ቅዱስ ዓላማ ስኬት” ጠብመንጃ አንሥቶ ወገንን ለመግደል ወይም ለዚያ “ቅዱስ ዓላማ ለመሠዋት” ወደ ጫካ ማምራት የሚያኮራና ታሪካዊ ሚናን መጫወት ነው የሚለው የዓማጽያን ውትወታ በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ይኖረዋል።
ጤነኛ ጎረምሳ ሆኖ ዓማጽያንን አለመቀላቀል ደግሞ በማኅበረ ሰቡ ባሕል የሚያሳፍር ድርጊት ሆኖ ይቆጠርና፣ አብዛኛው ወጣቱ፣ ለዓላማ ጽናት ሳይሆን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ብቻ አስቀድመው የሸፈቱትን ጓደኞቹን ከመቀላቀል ወደ ኋላ አይልም።
ሠ) የጽንፈኛ ሚዲያ ተቋማት አሉታዊ ሚና።
የግል ሚዲያ ተቋሞች በተለይም ደግሞ በውጭ አገር የመሸጉ የጽንፈኛ ብሔርተኞች ሚዲያ፣ አብዛኛው ለሕዝብ የሚያደርሱት ዜናዎቻቸውና ፖሊቲካዊ ትንተናዎቻቸው፣ ዕውነተኛ መረጃም ሆነ በቂ ማስረጃ የሌላቸው ቢሆንም፣ ወጣቱን ነፍጥ አንስቶ ወደ ዱር እንዲገባ አሉታዊ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው።
ከምንጩ እውነተኛውን ዜና ግልጽና ነጻ በሆነ መንገድ ለሕዝብ የሚያቀርብ የመንግሥትም ሆነ የግል ነጻ ሚዲያ ባለመኖሩ፣ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ እንደ ዕውነተኛ የዜና ምንጭ የሚያዳምጣቸው እነዚህን በውጭ አገር የመሸጉትን የጽንፈኛ ሚዲያ ዜናዎች ስለሆነ ወጣቱ በውትወታቸው እምብዛም ጥርጣሬ ስለማይኖረው፣ በቀላሉ ወደ ጫካ ያመራል።
3) ወጣቱን ከጠብመንጃ ለማላቀቅ የሚያጋጥሙ ችግሮች፣
ትጥቅ መፍታት ማለት ወጣት ዓማጽያንን ከጠብመንጃ ማለያየት ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ አስተሳሰባቸውን መቀየርንም ያካትታል። የተወሰነ የሕይወት ዘመኑን ከዘመድ ወዳጅ ተለይቶ ለተለያዩ ምክንያቶች ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ወስኖ በዱር በገደሉ ረኃብና ጥማትን እንዲሁም የዱር አውሬና የመንግሥት ሠራዊትን ጥቃት ተቋቋሞ መኖር የለመደን ዓማጺ ወጣት፣ በቀላል ትጥቁን ፈትቶ ወደ ሰላማዊው ማሕበረ ሰቡ ያለ አንዳች ችግር ይመለሳል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ወጣት ዓማጽያንን ከጠብመንጃ ማላቀቅ ይከብዳል። ግን ደግሞ ከቶውንም የማይቻል ነገር አይደለም።
አዎ! ሂደቱ እጅግ በጣም አድካሚና ጊዜ የሚፈጅ፣ በአስተዋይነትና በጥንቃቄ ካልተሠራ ደግሞ ከቀድሞው የባሰ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ፈታኝ የቤት ሥራ ነው። ለዚህም ነው፣ ተፋላሚ ወገኖች ይህንን አድካሚ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት፣ ወጣቱን መጀመርያውኑ ለዚህ አደገኛ ተልዕኮ እንዲያመራ የገፋፉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች በውል አውቆ ተገቢ ፍኖታ ካርታ በማዘጋጀቱ ላይ መስማማት ያለባቸው።
ይህም ማለት፣ ከፖሊቲካ ሥልጣን ጥያቄው መፍትሔ በተጨማሪ፣ ማኅበረ ሰቡ የቀድሞ ዓማጽያንን በደስታ እንዲቀበላቸውና፣ ተመልሰው ከተቋቋሙም በኋላ ከመንግሥት ወይም መንግሥታዊ ኃይላት መብታቸውን የሚነካ ጫና እንዳይደርስባቸው፣ የቀድሞ ታጣቂዎቹም በማኅበረ ሰቡ ላይ ሳይጫኑና የሰውን እጅ ሳያዩ ሠርተው ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩበት ሁኔታዎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል ማለት ነው።
የግጭቶቹ መፍትሔዎች እንደየአገሩ ፖሊቲካዊና ማኅበራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ሊለያይ ቢችልም፣ የትጥቅ አፈታት ሂደታቸው ግን በቅርጽ ይለያይ እንደሁ እንጂ በይዘት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። ከሁሉም በላይ ወጣት ዓማጽያንን አንድ የሚያደርጋቸው ዕውነታ ደግሞ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብም ሆነ በመንግሥት የፈለገውን ያህል ቃል ቢገባላቸው፣ ትጥቃቸውን ለመፍታት በፍጹም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው።
ከዩጎዝላቭያ ጦርነት በኋላ አንድ ሺ የማይሞሉትን የክሮኤሽያ ወጣቶችን ከጠብመንጃ አላቅቆ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ከዓመት በላይ ድርድር እንዳስፈለገ በቦታው ሆኜ የታዘብኩት ነበር። ለዚያውም በአውሮፓ ኅብረት ለያንዳንዳቸው ቤትና ለማቋቋሚያ ተብሎ ብዙ ሺ ኢዩሮ ጥሬ ገንዘብ ተከፍሎአቸው!
አገራችንን በተመለከተ ትጥቅ መፍታትን አስቸጋሪ ከሚያደርጉ ምክንያቶቹ ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፣
ሀ) “ወንድ ልጅ ትጥቅ አይፈታም” የሚባለው ፊውዳላዊ ባሕል ከጥንት ጀምሮ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ጭንቅላት የተቀረጸ በመሆኑ፣ አንድ ቀን ድርድሩ ተሳክቶ የሰላም ስምምነት ላይ እንኳ ቢደረስ፣ ዓማጽያኖቹ ትጥቅ ፈትተው “ፈሪ” ላለመባል ከጠመንጃ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ማሻከር አይፈልጉም።
ለ) ለዓማጽያን፣ ጠብመንጃ ከማንም እና ከምንም በላይ የቅርብ ወዳጅና ታማኝ ጓደኛ ነው። በነሱ ግምት፣ ጠብመንጃ የግልና የቡድን መብት ማስከበርያ ፍቱን መሳርያ ነው፣ ጠብመንጃ የግል ደኅንነትን መብት ማስከበርያ ነው። ጠብመንጃ የገቢ ምንጭ ነው፣ ጠብመንጃ በሰላሙ ወቅት የማይሞከረውን፣ የጠሉትን ሰው የማገት፣ የመግደል ወይም የተመኟትን ሴት የመድፈር መብት ያጎናጽፋል። በጠብመንጃ ብርታት የሰላማዊውን ማኅበረ ሰብ ሕይወት ያመሰቃቅላሉ።
ስለዚህም ነው ዓማጺው ሲተኛም ሲነሳም በጠብመንጃውና በራሱ መካከል ነፋስ እንኳ እንዳይገባ ተጣብቆት የሚኖረው። ጠብመንጃ፣ ዓማጽያኑ በሰላሙ ጊዜ ያልነበራቸውን የትየሌለ ጉልበት የሚያጎናጽፋቸው፣ “ታማኝ ወዳጅ” ነው ብለው ያምናሉ።
ሐ) የዓማጺያኑ ቅድመ ግጭት ማንነት፣ ትጥቅ በመፍታት ሂደት ላይ ወሳኝነት አለው። ለምሳሌ የተማረ ወጣት ዓማጺ ከጠብመንጃ ተላቅቆ በሙያው ሰርቶ ለመተዳደር ያለው ዕድል የተሻለ ስለሚሆን ካልተማረው ዓማጺ ይልቅ ቶሎ ከጠብመንጃ ፍቅር ሊገላገል ይችላል።
ዓማጽያኑ የነበራቸው የቤተ ሰብ ሁኔታም ወሳኝነት አለው። ከልምድ እንደ ተገነዘብኩት፣ የቤተሰብ ኃላፊነት ያለበት ተዋጊ ትጥቁን ፈትቶ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ ያለው ፍላጎት ከፍ ያለ ነው። ቤተሰቡ፣ ቄዬውና ተጓዳኝ ኃላፊነቱ ስለሚስቡት፣ ሁኔታው ከተመቻቸለት በአስቸኳይ ትጥቁን ፈትቶ ወደ ማኅበረሰቡ ይመለሳል። የራሱን ቤተሰብ ያልመሠረተ፣ በተለይም ሥራ አጥ ለነበረና አንዳችም ኃላፊነት ለሌለበት ወጣት ዓማጺ ግን፣ የሚያጓጓው ቄዬም ሆነ ኑሮ ስለሌለው ከጠብመንጃ ተላቅቆ ወደ ማሕበረ ሰቡ ለመመለስ ያለው ፍላጎት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው።
መ) የአገሪቷ ኤኮኖሚ ሁኔታ ሌላው ወሳኝ ዕንቅፋት ነው። ዓማጽያኑን ከጠብመንጃ አላቅቆ መንግሥት እያንዳንዳቸውን ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊና ሌላም ተጓዳኝ ፍላጎቶቻቸውን የማሟላት ዓቅም ከሌለውና ዓማጽያኑ ጠብመንጃን የሚተካ ተጨባጭ ጥቅም ካላገኙ በስተቀር፣ ከቁርጥ ቀን ጓደኛቸው ከጠብመንጃ ሊላቀቁ አይፈልጉም። ትምሕርቱን ጨርሶ ሥራ ያጣ ወጣት በበዛበት፣ ብሩኅ ነገን የሚጠብቁበት የሰላም ድባብ ካልሰፈነና መንግሥት በቂና የማያቋርጥ ቁሳዊ ድጋፍ ካልሠጣቸው፣ ዓማጽያን በቀላሉ ትጥቅ አይፈቱም።
ሠ) የዓማጽያኑ ድርጅት ጥንካሬና የተዋጊው ኃይል ብዛት፣ ማዕከላዊ አመራሩና የበላይ መኮንኖቹ በበታቾቻቸው ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲያዝዙ የሚያስችል ወጥ የሆነ የዕዝ ሰንሰለት ከሌለው፣ በበላይ ደረጃ የሚካሄደው ድርድርና የሚደረስበት ስምምነት በበታቾቹ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል። ብሎም፣ ስምምነቱ ድርጅቱን ሊከፍልና የተወሰኑ ቡድኖች የጫካን ሕይወት መርጠው ጠብመንጃቸውን እንዳነገቱ ግጭቱን ነፍስ እየዘሩበት ሊቀጥሉ ይችላሉ።
ረ) የሕዝቡ / ማኅበረ ሰቡ ስሜትና የቀድሞ ዓማጽያንን ተቀብሎ የማስተናገድ ፍላጎት ወይም ችሎታ አንድ ራሱን የቻለ ዓማጽያን በቀላሉ ትጥቅ እንዳይፈቱ የሚያደርግ ሁኔታ ነው። ዓማጽያን ማኅበረ ሰቡ ላይ የተለያዩ ወንጀሎችን (ለምሳሌ፣ ሰብልን የማቃጠል፣ የመዝረፍ፣ የማጉላላት፣ ሴቶችን የመድፈርና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎችን ፈጽመው ከሆነ) ማኅበረ ሰቡ በቀላሉ መልሶ ሊያቅፋቸው ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ይህም የትጥቅ መፍታት ሂደቱን በጣም ያዘገያል።
ታዲያ ምን ቢደረግ ነው ዓማጽያን ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ማኅበረ ሰብ የሚመለሱት?
ከላይ እንዳልኩት ዓማጽያንን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስ፣ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስን ለምታስተናግድ አገር ይቅርና፣ አንጻራዊ ሰላምና የተረጋጋ ኤኮኖሚ ባላቸው አገር እንኳ እጅግ አታካች የሆነ ተልዕኮ ነው። ለዚህም ነው ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት ከመንግሥት ቁርጠኛ ውሳኔ ባሻገር በመስኩ የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበቱ የአገር በቀልና የዓለም ዓቀፍ ሙያተኞች ተሳትፎ እጅግ በጣም ወሳኝ የሚሆነው።
አዎ! ከሁሉ በፊት ዓማጽያኑ ቀድሞውኑ እንዲያምጹ ያደረጋቸው ምክንያት(ቶች) አጥጋቢ መልስ ማግኘት አለበት። ለዚህ ተቀዳሚው ግዴታ የመንግሥት ይሆናል። በመቀጠል ደግሞ ስለ ትጥቅ አፈታቱ ሂደትና ለቀድሞ ዓማጽያኑ በተፋላሚዎቹ መካከል ቃል የሚገባቡት ዘላቂ የድኅረ ግጭት መፍትሔ ግልጽና ዘርዘር ባለ መልክ በስምምነቱ ሰነድ ውስጥ መካተት አለበት።
በዛሬው ያገራችን ሁኔታ መንግሥት ብቻውን የነዚህን ሁሉ የቀድሞ ዓማጽያን ወጣቶችን ቁሳዊ ፍላጎት ሊያሟላ ይችላል ብሎ መገመት ይከብዳል።
መንግሥት በራሱ ለብቻው ለማመቻቸት የሚችለውና ማድረግም ያለበት ለፖሊቲካ ጥያቄው መፍትሔ መስጠት ነው። ከዚያ ባሻገር ደግሞ ለምሳሌ በእርሻ ሙያ ለመተዳደር እንፈልጋለን ለሚሉ የቀድሞ ዓማጽያን የእርሻ መሬትንና የእርሻ መሣርያ በመስጠት ዓማጽያኑን ወደ ሰላማዊ ኑሮ ሊመራቸው ይችላል። ወደ ዩኒቬርሲቲ ተመልሰው ትምሕርታቸውን ለመጨረስ ለሚፈልጉም አመርቂ ድጋፍ ሊሠጥ ይችላል። ወደ ቀድሞ የንግድ ሙያቸው መመለስ ለሚፈልጉትም እንደዚሁ።
ይህ እንግዲህ የቀድሞ ዓማጽያኑ የተወሰኑ አባላትን ይመለከታል። የአብዛኛውን የቀድሞ ዓማጽያኑን ጠቅላላ ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ግን በግድ የዓለም ዓቀፍ ማኅበረ ሰቡ (የአውሮፓ ኅብረት፣ ተመድ፣ ወዳጅ መንግሥታት ወዘተ) ቁሳዊና ሙያዊ ድጋፍ ያስፈልጋል። (ዝርዝሩ በአተገባበር መመርያው ውስጥ ተካትቷል፣ ባለ ድርሻ አካላት መመርያውን ጠይቀው ሊያገኙ ይችላሉ)።
የዓለም ዓቀፉ ማኅበረ ሰብ ድጋፍ ቢያንስ ሁለት ዓይነት ነው።
የመጀመርያው፣ የቀድሞ ዓማጽያን ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ በያሉበት ጊዜያዊ ፍላጎታቸውን የማሟላት (መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስ እና ሌላ ሳይኮሎጂያዊ ድጋፍ ወዘተ) ተልዕኮ ሲሆን፤
ሁለተኛው ደግሞ፣ የወጣቱን ጉልበት በመሸመት ሊሆን ይችላል። አብዛኛው የአውሮፓ አገራት እያጋጠማቸው ባለው የዲሞግራፊ ችግር ምክንያት ሠርቶ ግብር በመክፈል ለአገራቸው ኤኮኖሚ አስተዋጽዖ ሊያደርግ የሚችል ወጣት ኃይል ያስፈልጋቸዋል። ይህን ኃይል ደግሞ በአገራቸው ውስጥ ሊያመርቱ ስለማይችሉ፣ ከውጭ ሰራተኛ ጉልበትን መግዛት ግድ ይላቸዋል። ስለዚህ መንግሥት ፈጣን እርምጃ ወስዶ ከነዚህ የተለያዩ የአውሮፓ አገራት ጋር “የሠራተኛ ጉልበት ኤክስፖርት” የሁለትዮሽ ውል ቢፈራርረም የቀድሞ ዓማጽያንን ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን ሥራ አጥ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ሳይቀር ለሁሉም ወገን ትርፍ ሊያስገኝ የሚችል ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል።
በዚያውም ልክ፣ ከብዙ የአውሮፓ አገራት ጋር ሰፋ ያለ የስኮላርሽፕ ዕድል ፈጥሮ በትምሕርታቸው ሊገፉ የሚችሉትን/የሚፈልጉትን የቀድሞ ዓማጽያንን ወደ ውጭ በመላክ ከጠብመንጃ ሊገላግላቸው ይችላል።
ይህ የሠራተኛ ጉልበትን ወደ ውጭ የመላክ ፕሮግራም፣ ከሌሎች አገራት ልምድ እንደምናየው ከሆነ፣ ከሌሎች መፍትሔዎች ሁሉ በበለጠ መልኩ ለአገሪቷም ሆነ ለወጣቶቹ ዘላቂ ጥቅም የሚሠጥ፣ ለነገ ተብሎ የማይታደር አስቸኳይ የመንግሥት ተቀዳሚ ተልዕኮ መሆን አለበት።
ወገኖቼ፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ነውና እስቲ እንወያይበት!
*** ባይሳ ዋቅ-ወያ ቀደም ሲል በራሺያ ፌዴሬሽን - ሞስኮ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ እና ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያ ናቸው።
ስቶክሆልም ሰኔ 2024 ዓ/ም
wakwoya2016@gmail.com