የአሰብ ወደብ ጉዳይ (ለውይይት መነሻ)

የአሰብ ጉዳይ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ካገራችን የፖሊቲካ ውይይት መድረክ የተለየበት ጊዜ ባይኖርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የዘወትር እንጉርጉሮ ሆኖአል ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም። ብዙ ብዙ አነጋጋሪ የሆኑ ሃሳቦችም ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየመነጩ ነው። በመንግሥት በኩል በግልም ሆነ በኦፊሴላዊ ደረጃ የሚሠነዘረው ሃሳብ “አሰብን በፈለገው መንገድ ማለትም ቢቻል በሰላም፣ ካልሆነ ደግሞ በጉልበትም ቢሆን ማስመለስ አለብን” የሚል ማስፈራርያ አይሉት ማባበያ መሰል ንግግሮች እየተደመጡ ነው። ጉዳዩ ከኢትዮጵያም አልፎ የዓለም ዓቀፉን ማኅበረ ሰብ እያሳሰበም ስለ መጣ እኔም በበኩሌ መሆን አለበት ብዬ የማምንበትን ሃሳብ በጽሁፍ መልክ ለኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማጋራት ለውይይት ልጋብዛቸው ወሰንኩ። ጉዳዩን በበለጠ ለመረዳት እየተነሱ ያሉትን ሃሳቦች በጥያቄ መልክ አስቀምጬ አስተያየት ብሠጥባቸው የተሻለ ይመስለኛል።

Assab.png

Assab. Credit: Google Maps

ሀ) ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል ወይ?

የባሕር በር ለአንድ አገር ምንኛ አስፈላጊ እንደ ሆነ በአገረ ብሔር ምሥረታ ሂደት ውስጥ የአውሮፓ አገራት ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያሳለፉት አውዳሚ ጦርነቶችን ማውሳቱ ብቻ በቂ ይመስለኛል። አስፈላጊነቱ ኦክሲጂን ለሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ያሕል ባይሆንም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው የሚል ዓረፍተ ነገር በደንብ የሚገልጸው ይመስለኛል።

የባሕር በር ማጣት ግን የባሕር በር አልባ አገሮች በሞትና በሕይወት መካከል የሚኖሩ ገመምተኞች ናቸው ብሎ መደምደም ደግሞ ትክክል አይሆንም። እንዲያውም አንዳንድ ባሕር በር አልባ አገሮች ከብዙ የባሕር በር ካላቸው አገራት ይበልጥ ሃብታም ሆነው እናገኛቸዋለን።

ስዊዘርላንድ፣ ሃንገሪ ሉከሴንቡርግ እና ሊሽተንሽተይን የመሳሰሉ ሃብታም አገራትን ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው። የባሕር በር እያላቸውም ደግሞ ሕዝቦቻቸውን በድኅነት የሚያኖሩ ብዙ አገራት አሉ። ኤርትራን ለምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ስለዚህ የባሕር በር ማጣት ለድኅነት ይዳርጋል፣ የባሕር በር መኖር ደግሞ አንድን አገር ሃብታም ያደርጋል ብሎ አጠቃላይ ድምደማ ለስሕተት ይዳርጋል ለማለት ነው።

ኢትዮጵያ፣ አዎ የባሕር በር ያስፈልጋታል። እጅግ በጣም ያስፈልጋታል።

ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ይዛ፣ ይህን ሁሉ ሕዝብ ለማኖር የሚያስፈልጓትን ዕቃዎች (መድኃኒት፣ ማዳበርያ፣ የጦር መሣርያዎች፣ እና ሌሎችም የፍጆታ ዕቃዎች) ለማስገባት ዘላለም ለአንድ ጎረቤት አገር ቀረጥ እየከፈለች መኖር ያንገሸግሻል። በመሠረቱ፣ የባሕር በር የሌላት አገር ዘላለሟን በባሕር በሩ ባለቤት መልካም ፈቃድ አየር እየተነፈሱ እንደ መኖር ማለት ነው። በሆነ ምክንያት የባሕር በሩ ባለቤት ለምሳለ ጂቡቲ ብታኮርፍና በሯን ብትዘጋ፣ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ መጠነ ሰፊ የሆነ ጥፋት እንደሚያጋጥመው ለመገመት አይከብድም።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ዘላለሟን ጂቡቲን እየተለማመጠች ከምትኖር የራሷ የሆነ ለሰላምም ሆነ ለአገር መከለካከያ የሚረዳትን የባሕር በር ማግኘት አለባት። ስለዚህ የባሕር በር/ወደብ አያስፈልጋትም የሚል ኢትዮጵያዊ ካለ ከሃዲ ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም።

ለዚህም ነው አቶ መለስና ግብረ አበሮቹን “አሰብ የኢትዮጵያ አይደለችም” ብለው በአደባባይ ወጥተው በማወጃቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለዘላለም እንደ ከሓዲ የምንቆጥራቸው።

ዛሬ ሁላችንም ልንወያይበት የሚገባን ተቀዳሚው ጥያቄ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል ወይ የሚለው ሳይሆን በሩን እንዴት ማግኘት አለባት የሚለው መሆን አለበት።
ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳን ዘንድ እየተሠነዘሩ ያሉትን አንዳንድ ግምቶችን፣ አስተሳሰቦችና ሃሳቦችን አንስቼ በበኩሌ ትክክል ነው ብዬ የምገምተውን እንደሚቀጥለው ላካፍላችሁ።

ለ) አሰብ የማን ናት?

ይህ ጥያቄ በኢትዮጵያውያኖች ዘንድ በተለያየ መልኩ እየተነሳና እያወያየ ነው። ለብዙ ኢትዮጵያውያን የባለቤትነቱ ጉዳይ ግልጽ ቢሆንም፣ አሰብ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ሕጋዊ ባላቤቶች እንደ ነበሯት ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል።

መጀመርያ ላይ ሱልጣን ኢብራሂም የተባለው የአፋር መሪ፣ በ1869 ዓ/ም በ6000 ማሪያ ቴሬዛ ሩባቲኖ ለተባለው የጣሊያን የመርከብ ኩባኒይ ሽጧት አሰብ ለመጀመርያ ጊዜ የወደብ አገልግሎት መስጠት ጀመረች።

ከዚያም በ1882 ዓ/ም የጣሊያን መንግሥት አሰብን ከኩባኒያው ነጥቆ የመንግሥት ንብረት አደረጋት።

ይህ የጣሊያን መንግሥት ውሳኔ፣ ጣሊያን እንድ አንድ ቅኝ ገዢ አገር፣ መጀመርያ ወደ ኤርትራ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ እግሯን እንድትዘረጋ የረዳት ድርጊት ተብሎ በታሪክ ባለ ሙያዎች ዘንድ ይወሳል።

ኢትዮጵያ ጣሊያንን ካሸነፈች ከአሥር ዓመት እንቅስቃሴ በኋላ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በ1952 ዓ/ም በፌዴረሽን እስካዋሃደችበት ጊዜ ድረስ ማለትም ለ83 ዓመታት አሰብ የኢትዮጵያ ወደብ አልነበረችም።

ከ1952 ዓ/ም እስከ 1993 ዓ/ም ለ41 ዓመታት፣ (ኤርትራ ነፃነቷን እስካገኘችበት እስከ 1993 ዓ/ም ድረስ) ደግሞ አሰብ የኢትዮጵያ ወደብና አካል ነበረች። ላለፉት 32 ዓመታት ደግሞ አሰብ የኤርትራ አካል ናት።

አንዳንድ የዋሆች የተለያዩ ታሪኮችና ትርክቶችን እየጠቀሱ፣ አሰብ የኢትዮጵያ ነበረች፣ ስለዚህ መልሰን መውሰድ አለብን ይላሉ። በዘመናዊ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ልምድ መሠረት፣ አንድ አገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ከሆነበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ በሱ የሚጠራውንና በተግባር በራሱ መንግሥት አስተዳደር ሥር የሆነውን ሕዝብና መሬት ሌላ ማንም አካል ሊነካበት አይችልም።

ፈረንጆች the principle of territorial integrity የሚሉት መሪህ ነው። ይህ መርህ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ውስጥ ግልጽና በማያሻማ መልኩ የተቀመጠ ነው።

ዛሬ አሰብ የኤርትራ አካል ስለሆነች፣ ከኤርትራ መንግሥት በጎ ፈቃድ ውጪ የማንም ሌላ አካል ልትሆን አትችልም።

መንግሥታት ግን በሕዝባቸው ፈቃድ በተለያዩ ምክንያቶች ለጎረቤት ወዳጅ አገራት የግዛታቸውን አንድ አካል ቆርጠው በስጦታ መልክ ሊሸልሙ ይችላሉ። የሶቪዬት ኅብረት መንግሥት ለምሳሌ፣ የሩሲያና የዩክሬን ሕዝቦች የወዳጅነት ስምምነት የተፈራረሙበትን 170ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ በ1954 ዓ/ም ክራይሚያን ከሩሲያ ቆርጦ ለዩክሬይን ሰጥቷል። በወቅቱ፣ ዩክሬይን ከሶቪዬት ኅብረት 15 ሬፑብሊኮች መካከል አንዷ ስለ ነበረች፣ የሩሲያ ሕዝብም የመንግሥታቸውን ድርጊት አልተቃወመም።

አንዳንዶች ወገኖቻችን ደግሞ፣ ወያኔ የሕዝብ መንግሥት ስላልነበረ ወይም ደግሞ በወቅቱ የሽግግር መንግሥት ስለነበረ፣ ለኤርትራ ነጻነት የመፍቀድ መብት አልነበረም፣ ሊኖረውም አይገባም ሲሉ ይስተዋላል። ውሃ የማያነሳ ሙግት ነው።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ማለትም ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አገራችንን ሲያስተዳድሩና የውጪ ፖሊሲዋን እንደ ፈለጋቸው ሲነድፉ የነበሩ መሪዎቿ በሙሉ በሕዝብ የተመረጡ አልነበሩም። ኤርትራ ደግሞ ነፃ የወጣችው በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በጎ ፈቃድ ሳይሆን በትግል አሸንፋ ስለ ሆነ፣ የሽግግሩ መንግሥት (ወያኔ) ያኔ ከአሸናፊው የኤርትራ ኃይል ጋር የመደራደር አቅም የነበረው አይመስለኝም።

ሲሆን ሲሆን፣ አቶ መለስ በጊዜው ማድረግ የነበረበትና፣ ለማንም ሊገባ በማይችል ምክንያት “አሰብ የኢትዮጵያ አይደለችም” በማለት ፈንታ፣ “ለጊዜው አቅም ስለሌለኝ ኤርትራ ወሰደችብኝ እንጂ አሰብ የኢትዮጵያ ናት፣ ዛሬ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር ይዤ የባሕር መውጫ አልባ አገር ሆኜ መቀጠል ፍትሓዊ አይደለም” ብሎ ለመላው የተባበሩት መንግሥት ድርጅት አባላት ስሞታውን በአደባባይ ቢያሳውቅና ስሞታውም ቢመዘገብ ኖሮ፣ ዛሬም ሆነ መጪው ትውልድ አጋጣሚ ፈቅዶለት ኤርትራን ወግቶ አሰብን ለመውሰድ ቢነሳሳ፣ ታሪካዊ ምክንያት ስላለው ከመላውም ባይሆን የብዙ አገሮችን ድጋፍ ሊያገኝ ይችል ነበር።

በዛሬ ሁኔታ ግን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፉ መድረክ ላይ በግልጽ “የኔ አይደለችም” ብሎ በአደባባይ አውጆ ያስረከባትን ግዛት (አሰብ)፣ ዛሬ በጉልበት ለመውሰድ መሞከር ሕገ ወጥነት ይሆናል።

ኤርትራ ደግሞ በ1993 ዓ/ም 182ኛ የተመድ አባል ሆና ድርጅቱችን ከተቀላቀለችበት ጊዜ ጀምሮ፣ ወደድንም ጠላንም ዛሬ ከሌሎች 193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ጋር እኩል ሙሉ አባል ሆና የምትኖር ሏዓላዊ አገር ናት። ይህቺን ሏዓላዊ አገር የተፈጠረችው በሕጋዊ መንገድ አልነበረም ማለት ወይም ግዛቷን በጉልበት ቆርሶ ለመውሰድ መሞከር ኢትዮጵያ ቃል ገብታ የፈረመችውን የተመድን ቻርተር የሚጥስ ዓለም ዓቀፋዊ ወንጀል መፈጸም ይሆናል።

አንዳንዶች ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራ መንግሥት የሰጣትን ዕውቅና ማንሳት አለባት የሚሉ አሉ። አዎ! ኢትዮጵያ አንድን አገር የማወቅና ዕውቅናም የመንሳት መብት አላት። ግን፣ በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ውስጥ እንኳን ዕውቅና መንሳት ይቅርና ጊዜያዊ የዲሚሎማሲ ግንኙነትን ማቋረጥ እንኳ እጅግ በጣም ጎጂ ስለ ሆነ፣ ኢትዮጵያ የፈለገው ይምጣ ብላ ለኤርትራ ሰጥታት የነበረውን ዕውቅና ብታነሳ፣ በኤርትራ ዓለም ዓቀፋዊ ግንኙነት ላይ አንዳችም ዓይነት ጫና ሊያሳድር አይችልም።

ሐ) ጦርነት መፍትሔ ሊሆን ይችላል ወይ?

ዘመናዊው የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት (በመንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት) በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተቋቋመ በኋላ፣ ከፊተኞቹ ግንኙነቶች ሁሉ የሚለየው የአባል አገራት ግዛትን አይነኬ (territorial integrity) በማድረጉና መንግሥታት አለመግባባቶቻቸውን በጉልበት ሳይሆን በውይይት እንዲፈቱ የሚል መሪህ በማወጁ ነው።

አንድ መንግሥት ግን የቻርተሩን መሪህ ከጣሰና ሌላ አገርን ከወረረ፣ የጸጥታው ምክር የአባል አገራትን ጦር አሰባስቦ በወራሪው አገር ላይ በማዝመት የተጣሰውን ሏዓላዊነት መልሶ ሊያስከብር ይችላል። ለምሳሌ በኮርያና በኮንጎ እንዳስዘመተው ዓይነት። በተረፈ ግን፣ አንዳንድ አገራት በተለይም ኃያላኑ የተመድ አባል አገራት ያለ ጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ በደካማ አገሮች ጉዳይ ጣልቃ ቢገቡም፣ የአንድ አገራዊ ሏዓላዊነት ግን በመርህ ደረጃ ሁሌም እንደ ተከበረ ነው።

የተመድ መርህ አስፈላጊነት አንዳለ ሆኖ አንዳንድ ኃያላን አገራት ግን “ብሔራዊ ጥቅሜ ተነክቷል” ብለው ከማሰብ፣ ደካማ አገሮችን ሲወርሩ እናያለን። ይሕ ሕገ ወጥነት ነው። ጉልበተኛ ስለ ሆኑ ብቻ ሏዓላዊ አገርን መውረራቸው፣ ድርጊታቸውን ሕጋዊ አያደርገውም። ኃይለኛ ሰው ደካማውን ሰው ሊገድል ይችላል። ድርጊቱ ግን ሕገ ወጥ ስለሆነ በግድያ ወንጀል ያስከስሳል።

በዘመናዊው የዓለም ዓቀፍ ግንኙነትም፣ ኃይለኛው አገር ደካማውን ሲወርር በሕገ ወጥነቱ በሌሎች አገራት ቢኮነንም፣ ወንጀለኛውን ኃያል አገር በተግባር ሊቀጣ የሚችልና ለተወራሪው አገር ፍትሕ የሚቆም፣ “ጥርስ ያለው” ዓለም አቀፋዊ የጦር ፍ/ቤት ስለሌለ፣ ድርጊቱ እየተኮነነም አልፎ አልፎ ከመተግበር አልቆመም።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቻርተሩ ነፍስ አባት ነን ብለው ራሳቸውን የሾሙ አምስቱ ኃያላን አገራት ራሳቸው የአገራትን ሏዓላዊነት እየጣሱ እንዳሻቸው “ብሔራዊ ጥቅማቸውን” ሲያስከብሩ ይገኛሉ። አሜሪካ በኢራቅ፣ በሶርያና በሊቢያ፣ ሩሲያ ደግሞ በዩክሬይን የፈጸሙትን ወረራ ማስታወሱ በቂ ይመስለኛል።

'ታዲያ ኢትዮጵያስ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ኤርትራን ብትወርር ምን ነውር አለበት?' ብሎ መጠየቅ አግባብ ያለው ይመስላል። አዎ! አቅም ካላት ልክ እንደ አሜሪካና ሩሲያ የተመድን መርህ ጥሳ ኤርትራን መውጋት፣ ምናልባትም ደግሞ ለማሸነፍ ትችላለች። ግን? ግን? ግን?

ጦርነትን ማሸነፍና ድልን ማጣጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

ጦርነትን አሸንፎ የአጭር ጊዜ ዓላማን ከግብ አድርሶ ወደ ኋላ መመለስ ይቻላል። ለምሳሌ በ1977 ዓ/ም የሶማልያ ወረራ ጊዜ፣ ኢትዮጵያ በሶቪዬት ኅብረትና በሌሎች ወዳጅ አገራት ድጋፍ ወራሪውን ኃይል አሸንፋ ከአገሯ አባርራ ሏዓላዊነቷን አስከብራለች። ዓላማው ወራሪውን ኃይል ድል አድርጎ ወደ አገሩ መመለስ ስለሆነ፣ የሶማሊያ ጦር ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ሕዝባችን እስከ ዛሬም ድረስ ድሉን ሙሉ በሙሉ እያጣጣመ ነው።

ጦርነትን ማሸነፍና ድልን ማጣጣም ማለት እንደዚህ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ኤርትራን በጦር ሜዳ አሸንፋ አሰብን የመያዝ ዕድል አገኘች እንበል። አሰብ በጉልበት የተወሰደበት የኤርትራ ሕዝብና መከላከያ ሠራዊቱ ደግሞ፣ “አሸንፈኸኝ አሰብን ስለ ወሰድክብኝ ደስ ብሎኛል” ብሎ እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም።

ለመዋጋት ለጊዜው ዓቅም ባይኖረውም ቀስ በቀስ መደራጀት ይጀምራል። ሕዝቡም ደግሞ ለወራሪው የኢትዮጵያ ሠራዊት ቢያንስ ቢያንስ በልቡ ጥፋትን መመኘቱን ይቀጥልበታል። ኢትዮጵያ እንግዲህ አሸናፊ ስለ ሆነች፣ የአሰብ ወደብን ጥቅም ላይ ለማዋል፣ ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ወይም ወዳጅ አገራት ተበድራ ግንባታውን ትጀምራለች። ለግንባታው ሥራ ደግሞ መቼም ኤርትራውያን “ስለማይታመኑ” የቀን ሠራተኞቹን ከኢትዮጵያ አምጥታ ጸጥታው አስተማማኝ ባልሆነ የጦርነት ቀጠና ውስጥ ማመላለስና ማኖር ሊኖርባት ነው። ሰላምና መረጋጋትን በአካባቢው ማስፈን ግድ ይላል ማለት ነው።

የአካባቢው ዓረብ አገራት ወገን ለይተው፣ በአንድ በኩል ሳውዲ ዓረቢያና ኳታር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅዋ ኤሚሬትስ ሆነው “ለአካባቢው ጸጥታ” ከመቆርቆር የተነሳ የአሰብን ወደብ ብቻ ሳይሆን ቀይ ባሕርን እንዳለ በደም ሊያጨቀዩት እየተፎካከሩ ነው። ስለዚህ፣ ኢትዮጵያ አሰብን በጉልበት ይዛ ለመቆየት፣ እነዚህን ሁሉ ወዳጅ ያልሆኑ አገራትን በዲፕሎማሲው ብቻ ሳይሆን በጦር ሜዳም ገጥማ ማሸነፍ አለባት ማለት ነው።

በቅርቡ በትግራይ ጦርነት ወቅት ብዙ መቶ ሺህ ወጣቶች አልቀው የወደቀው ኤኮኖሚያችንም ገና ሳያገግም፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ደግሞ ከሰሜኑ ጦርነት የተረፈው አምራች ኃይል ወጣቱ በየቀኑ የሚማገዱባት ኢትዮጵያ፣ ሌላ ዓለም ዓቀፋዊ ጦርነት ማካሄድ ትችላለች ብሎ መገመት ይከብዳል።

በኔ ግምት፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ፍላጎቱ እንጂ (wishful thinking) አሰብን በጉልበት ወስዳ ገንብታ ለልማት የሚያደርስ አቅም አላት ብሎ የሚገምት ካለ የፖሊቲካ የዋህ “አገር ወዳድ አርበኛ” ብቻ ይመስለኛል።

የክራይሚያና የአሰብ ጉዳይ ተመሳሳይ ነው?

የአሰብና የክራይሚያ ታሪካዊ አመጣጥና ዛሬ ያሉበት ሁኔታ ይመሳሰላል። በርግጥም ታሪካዊ ተመሳሳይነት አላቸው። ያን ያህልም ደግሞ ልዩነቶችም አሏቸው።

ክራይሚያ የሩሲያ መንግሥት ከቱርክ (ኦቶማን) ጋር ካደረገው የረጅም ጊዜ ጦርነት በኋላ በ1783 ዓ/ም የሩሲያ ግዛት አካልና የደቡብ የባሕር በሯ ሆነች።

በወቅቱ የከራይሚያ ኗሪዎች የእስልምና እምነት ተከታይ የነበሩ የታታር ሕዝቦች ሲሆኑ፣ በሂደት ክርስቲያኗ ሩሲያ የራሷን ብሔር ክርስቲያን ዜጎችን በክራይሚያ ስላሰፈረች የነባሩ ሕዝብ ቁጥር እየቀነሰ ሂደ። ይባስ ብሎ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመርያ ላይ፣ የክራይሚያ ታታሮች ሂትለርን ይደግፋሉ ብሎ ከማሰብ፣ ስታሊን ታታሮችንና ሌሎች አሥር የሩሲያ ብሔር ተወላጅ ያልሆኑትን የሶቪዬት ሕዝቦችን ወደ ሳይቤርያ ለጅምላ ግዞት ዳረጋቸው።

ሩሲያ ሂትለርን አሸንፋ አውሮፓን ከፋሺስት ነፃ ካረገች በኋላ፣ በአህጉሩ ከወሰደቻቸው የግዛት ሽግሽጎች አንዱ፣ ታታሮች ምንጊዜም ወደ ክራይሚያ እንዳይመለሱና በነሱ ፈንታ በግዛቱ ሙሉ የሩሲያንና ጥቂት የዩክሬይን ብሔር ተወላጆችን ማስፈሯ ነው።

ስታሊን ከሞተ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1954 ዓ/ም ማለትም ክራይሚያ ለ171 ዓመታት የሩሲያ ግዛት አካል ሆኖ ከኖረች በኋላ፣ የያኔው የሶቭዬት መሪ ክሩሼቭ (ራሱም የዩክሬይን ብሔር ተወላጅ ነበር)፣ የሩሲያና የዩክሬይን ሕዝቦች የወዳጅነት ስምምነት የፈረሙበትን ሶስት መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ክራይሚያን ከሩሲያ ቆርጦ ለዩክሬይን ሰጠ።

ያኔ ዩክሬይን ራሷ ከአሥራ አምስት የሶቪዬት ኅብረት ሬፑብሊኮች አንዷ ስለ ነበረች፣ ክራይሚያ በውስጥ አስተዳደር ዩክሬይን ሬፑብሊክ ሥር ትሁን እንጂ ያው የሶቪዬት ኅብረት አካል ነበረች። የክራይሚያ አስተዳደራዊ መዋቅሯ በዩክሬይን ሥር ቢሆንም፣ ሶቪዬት ኅብረትም ሆነች ኋላ ደግሞ የሶቪዬት ኅብረት ወራሿ የሩሲያ ፌዴሬሽን፣ እስከ 2014 ዓ/ም ድረስ ወደቡን ለተለያዩ ዓላማዎች መጠቀሟን ለአንድም ቀን አላቋረጠችም ነበር።

በ1991 ዓ/ም ሶስቱ የሶቭዬት ኅብረት ሬፑብሊክ ሕዝቦች መሪዎች፣ ማለትም ሩሲያ፣ ዩክሬይንና ቤላሩስ፣ ታኅሳስ 8 ቀን 1991 ዓ/ም ሶቪዬት ኅብረት እንድትፈርስ ሲወስኑ፣ ዩክሬይን ክራይሚያን እንደ ያዘች ነጻ አገር ሆና ወጣች። በወቅቱ የነበረው የሩሲያ መሪ ስለ ክራይሚያ በዩክሬይን ሥር መሆን ምንም አላሳሰበውም ነበር።

በዩክሬይንና ሩሲያ መካከል በተፈጸመው ልዩ ውል መሠረት ሩሲያ ክራይሚያን ለፈለገችው ዓላማ በሊዝ እንድትጠቀምበት እና ሩሲያ ደግሞ ጋዝና የነዳጅ ዘይት ለዩክሬይን በቅናሽ ዋጋ እንድታቀርብ ተስማምተው በወዳጅነታቸውን ቀጠሉበት። ማርች 18 ቀን 2014 ዓ/ም ላይ ግን ፑቲን ውሉን አፍርሶ፣ ያለ አንዳች ተኩስ የዩክሬይንን መከላከያ ሠራዊት አባርሮ፣ ክራይሚያን መልሶ የሩሲያ አካል አደረጋት።

እንዴት እንደዚህ በቀላሉ ክራይሚያን የሚያክል ግዛት ቆርጦ የሩሲያ አካል ለማድረግ ቻለ የሚለው ጥያቄ፣ ኢትዮጵያም ለተወሰነ ጊዜ የግዛቷ አካል የነበረውን አሰብን እንደዚሁ በጉልበት መውሰድ ትችላለች ወይም አለባት ለሚሉ ወገኖች ትምህርት ሰጪ ስለሚሆን፣ አንዳንድ ለፑቲን ስኬት አስተዋጽዖ ያደረጉትን ምክንያቶች (factors) መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።

1) ሩሲያ ከዓለም ኃይላን መንግሥታት ምናልባትም መከላከያን በተመለከተ ታላቋ የምድራችን ኃያል አገር ናት። ስለሆነም፣ የዩክሬይን መከላከያ ሠራዊት በምንም ተዓምር ሊገዳደረው ስለልቻለ፣ የነበረው ምርጫ ያለ ምንም ማንገራገር ግዛቱን ለሩሲያዎች ለቅቆ መውጣት ብቻ ነበር።

2) የሩሲያ ጦር ደግሞ ለዘመናት በክራይሚያና በጎረቤት ሴቫስቶፖል ወታደራዊ ቤዝ ሰፍሮ ስለ ነበር፣ ክራይሚያን ለመውረር ሩሲያ ከሩቅ ቦታ ወታደሮችን ማምጣት አልነበረባትም።

3) የክራይሚያ ሕዝብ ከ85% በላይ የሩሲያ ብሔር ተወላጅ ስለ ነበር፣ የሩሲያ አካል መሆንን የዘላለም ሕልማቸው ነበርና ሩሲያ ክራይሚያን ስትጠቀልል ወታደሮቹን በደስታ ነበር የተቀበሏቸው።

4) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በማርች 2014 ዓ/ም ባስተላለፈው የጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ 68/262፣ አሥራ አንድ አገራት ብቻ ሩሲያን ሲደግፉ አንድ መቶ አገራት ደግሞ የተቃወሙት ቢሆንም፣ ውሳኔው በሩሲያ ላይ አንዳችም ተጽዕኖ ሊያሳድር አልቻለም።

5) ሩሲያም ክራይሚያን የራሷ ባደረገች በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ ለመላው የክራይሚያ ኗሪዎች የሩሲያ ዜግነት፣ ፓስፖርት፣ የመንጃ ፈቃድና ሌሎች መታወቂያ ወረቀቶችን ወደ ሩሲያ ዶኩሜንቶች ቀይራ ያለ አንዳች ችግር ይኽው እስከ ዛሬ ባለቤትነቷን አስመስክራ ግዛቱን 27ኛ የሩሲያ ሪጂናል አስተዳደር በማድረግ ድሏን እያጣጣመች ትገኛለች። ኢትዮጵያ ግን እንደው በጦርነት አሸነፈች ብንል እንኳ፣ ድሉን የማጣጣም ዕድሏ ዜሮ ነው ማለት ይቻላል።

የክራይሚያ በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች በተለያዩ አገራት አካል መሆን፣ መጨረሻ ላይ ደግሞ ወደ ታሪካዊ ባለቤቷ ያለ አንዳች ችግር ተመልሳ መቀላቀሏ ከአሰብ ጉዳይ ጋር የሆነ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖርም፣ ከሚያመሳስላቸው ይልቅ የሚለያያቸው የሚያመዝን ይመስለኛል።

1) ኢትዮጵያ ከኤርትራ የተሻለ የመከላከያ ሠራዊት ሊኖራት ይችላል፣ ግን ኤርትራን ደግፈው ኢትዮጵያን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊወጉ የሚችሉ ብዙ አገራት አሉ። በክራይሚያ ምክንያት ዩክሬይንን ደግፎ ሩሲያን ሊወጋ የቃጣ ግን አንድም አገር አልነበረም።

2) ኢትዮጵያ ለአርባ ዓመት አንዳችም እንክብካቤ ያልተደረገለትን ወደብ፣ መጠነ ሰፊ የሆነ ካፒታል አፍስሳበት ወደቡን ለጠቀሜታ ማድረስ እጅግ በጣም አዳጋች ይሆናል። ሩሲያ ግን ወደቡን ከቱርኮች ከወሰደችበት ከ1783 ዓ/ም ጀምሮ ያለማቋረጥ ትጠቀምበት ስለ ነበር፣ አሁን እንደ አዲስ ማልማት አያስፈልጋትም ነበር።

3) ሩሲያ የክራይሚያ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት እንዳይደረግበት ወይም ውሳኔን “ድምጽን በድምጽ የመሻር” (ቬቶ) ሥልጣን ያላት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን ያ አቅም የላትም።

 4) ባለፉት ዓመታት በኅዳሴ ግድብ ምክንያትና በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያን ደግፈው የተመድ የጸጥታ ምክር ቤትን ውሳኔ በቬቶ ሲሽሩ የነበሩ ሩሲያና ቻይና፣ በአሰብ ጉዳይ ግን፣ ኢትዮጵያ በጦርነት ኤርትራን ድል አድርጋ አሰብን እንድትቆጣጠር የሚፈቅዱ አይመስለኝም።

ይህ ሁሉ ሲደመር፣ በዛሬው አገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ ኤርትራን አሸንፋ አሰብን ለመያዝ ብትችልም እንኳ ድሉን የማጣጣም ዕድሏ ግን እጅግ በጣም የመነመነ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።

መ) ኢትዮጵያ የባሕር በርን መልሳ ለማግኘት ምን ማድረግ አለባት?

አዎ! ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል። ግን እንዴት አድርጋ ነው የባሕር በሩን ልታገኝ የምትችለው?

ለኔ ብቸኛው መንገድ ከኤርትራ ጋር በመልካም ጉርብትና መንፈስ ተነጋግሮ “ሰጥቶ በመቀበል” መርህ ላይ የተመሠረተ አንዳች ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ ነው ባይ ነኝ።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ኢትዮጵያም ደግሞ እነዚያን የኤርትራን ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ ብዙ ስጦታዎች አሏት።

ሩሲያ ለዩክሬይን ጋዝና ዘይት በርካሽ ሰጥታ ወደቡን ለመጠቀም እንደ ቻለች ዓይነት ማለት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ሕዝብ ስለሆንን፣ በምድራችን ካሉት መንግሥታት መካከል ከኤርትራ መንግሥት ጋር መግባባቱ በጣም የሚቀልል ይመስለኛል። ቅንነቱ ካለ!

መደምደምያ

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ተስማማታ የአሰብን በር መጠቀም ብትጀምር፣ ከኢትዮጵያ ባላነሰ መልኩ ኤርትራም ተጠቃሚ ትሆናለች። ሰላሳ ዓመት ሙሉ አንዳችም ጥቅም ያልሠጠን ወደብ ዛሬ ኢትዮጵያ አልምታው መጠቀም ብትጀምር ኤርትራም እንደ ባለቤትነቷ፣ የወደቡ ተጠቃሚ ትሆናለች። በቀረጥ መልክ ከኢትዮጵያ በምታገኘው ገቢ የአገሯን ኤኮኖሚ ታሻሽላለች። ወጣቶቿ የሥራ ዕድል ያገኛሉ፣ ሌላም ሌላም።

ስለዚህ የኢትዮጵያ አሰብን መጠቀም ለኤርትራ መቶ በመቶ ጥቅም እንጂ አንዳችም ጉዳት አያደርስባትም። ይህ እንግዲህ ሁለቱ መንግሥታት መርዛማ ንግግራቸውን አቁመው፣ ጥያቄው በቅንነትና በሰላም የሚፈታበትን መንገድ ለመፈለግ ፈቃደኛ ከሆኑ ማለት ነው።

ኤርትራ ይህ ሁሉ ጥቅም ይቅርብኝ ብላ ኢትዮጵያ ለምታቀርብላት የወዳጅነት ጥያቄ በሯን ከዘጋች ደግሞ፣ ሙሉ መብቷ ነውና ኢትዮጵያ ይህንን የኤርትራን የሏዓላዊነት መብት ማክበር ግዴታዋ ነው። በጦርነት አሰብን ወስዶ ለኢትዮጵይ ጠቄሜታ ለማዋል መሞከር ዓለም ዓቀፋዊ ወንጀል ስለሆነ፣ ኢትዮጵያ በምንም መልኩ በዚያ የጦርነት ጎዳና ለመሄድ ሳይሆን፣ ለመሄድ ማሰብም የለባትም።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ያላት ተቀዳሚውና ሕጋዊው ምርጫ፣ ከኤርትራ ጋር ተስማምቶ አሰብን ማልማት ነው። ያ ካልተቻለ ደግሞ፣ ከጂቡቲ በተጨማሪ የሌሎች ጎረቤት አገራትን ወደብ ለመጠቀም መሞከር ነው። ይህም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይጠይቃል እንጂ የሚቻል ነው። ዋናው ነገር፣ የውጭ ወራሪ ኃይልን ወግቶ ግዛትን ለማስለቀቅ ካልሆነ በስተቀር፣ ጦርነት ምንጊዜም ቢሆን አውዳሚ ነውና በጭራሽ መታሰብ የለበትም።

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ያስተናግዳቸውና እያስተናገድናቸው ያሉት የእርስ በርስ ጦርነቶች ምንኛ አውዳሚ እንደሆኑ በደንብ የገባን ይመስለኛል። ስለዚህ የጦርነት አማራጩ ከኢትዮጵያ መንግሥት የመፍትሔ ሊስቶች ውስጥ ለዘላለሙ መፋቅ አለበት ብዬ አምናለሁ። ቮልቴር እንዳለው፣ “war is the greatest of all crimes, and yet there is no aggressor who does not color his crime with the pretext of justice.

አቶ መለስና ግብረ አበሮቹ የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰው በሕገ ወጥ መንገድ ለኤርትራ በመስጠታቸው ምክንያት ጉሮሮአችን መታነቁ ቢያንገበግበንም፣ ከሃዲዎቹን ለዘላለም እንዲኮነኑ ማድረግና መጪው ትውልድ ደግሞ ከዚህ የክህደት ሥራ ጥሩ ትምሕርት ቀስሞ፣ ለወደፊት አንዲት ስንዝር እንኳ የኢትዮጵያ መሬት ተቆርሳ ለሌላ አገር እንዳትሰጥና ሏዓላዊነቷ እንዳይደፈር ነቅተው የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው ብሎ ማሳሰብ እንጂ በሕገ ወጥ መንገድ የተወሰደብንን መሬት በጦርነት ለማስመለስ መሞከር አያስፈልግም።

ከላይ እንዳልኩትም ቅንነቱ ካለ፣ ሁለቱም መንግሥታት ሰላማዊ በሆነ መንገድ አሰብን ለሁለቱም እኩል የሚጠቅም ወደብ ማድረግ ይችላሉ። መልካም ንባብ!

******
ስዊድን፣ ጥቅምት 2025 ዓ/ም


*** ባይሳ ዋቅ-ወያ ቀደም ሲል በራሺያ ፌዴሬሽን - ሞስኮ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ ናቸው።

wakwoya2016@gmail.com


Share

Published

By Bayisa Wak-Woya
Source: SBS

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service