ከሁለት አሠርት አመታት በላይ በትዳር ለኖሩት ወ/ሮ ለታይና አቶ ገ/እግዚ (ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ) ትዳራቸው በልጅ አለመባረኩ ህይወታቸውን አክብዶታል፡፡ ኑሮአቸውን ከመቐለ በስተደቡብ 60ኪ.ሜ እርቃ በምትገኘው ሳምሪ አቅራቢያ ያደረጉት እነዚህ ባለትዳሮት ኑሮዋቸውን በግብርና የሚገፉ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ የሆነባቸው ግና ጭንቀታችው የኑሮ ውጣውረድ ሳይሆን የዘወትር ፀሎትና ስለታቸው፤ ጎጆቸው በልጆች ጫጫታና ሩጫ እንዲደምቅላቸው ነበረ፡፡
ምንም እንኩዋን የወ/ሮ ለታይ እድሜ ወደ አርባዎቹ መጨረሻ እየገሰገሰ እርጅናም መጣሁ መጣሁ ቢልም በፈጣሪያቸው በነበራቸው መታመን አንድ ቀን የአብራካችንን ክፍያ እንስማለን የሚከው ምኞታቸው ለአንድ አፍታም ደብዝዞ አያውቅም፡፡ በትዳር መካከል የአብራክ ክፍያ ልጅ አለመኖር እንደትልቅ እንከን በሚቆጥር ማህበረሰብ ውስጥ እነዚህ ጥንዶች በታማኝነት መኖራቸው አንድም አንዳቸው ለሌላቸውያላቸውን ፍቅር በሌላ መልኩም አምላካቸው ላይ ያላቸውን መተማመን ያሳያል፡፡
ወ/ሮ ለታይ ነፍሰጡር መሆናቸውን ያወቁት የሆዳቸው መግፋት ካጤኑ በኃላ ጤና ተቋም ሄደው በደረጉት ምርመራ ነበር፡፡ በአቅራቢያቸው የሚገኙ የጤና ባለሞያዎች ከእድሜያቸው መግፋት ጋር ተያይዞ ሊኖሩ የሚችሉ ችግሮችን ከግምት በማስገባት የወሊድ ክትትላቸውን ከመኖሪያቸው 60 ኪ.ሜ በሚርቀው መቐለ ከተማ በሚገኘው በአይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንዲያደርጉ ይመከራሉ፡፡
በባለ ሙያዎቹ ምክር ወደ አይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያቀኑት ጥንዶቹ በተደረገላቸው ምርመራ ወ/ሮ ለታይ በአንድ ጊዜ ሶስት ልጆች እንደፀነሱ ሲነገራቸው ደስታቸውን በለቅሶና በምስጋና ለፈጣሪያቸው አደረሱ፡፡ “የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል” የሚለው ብሂል እነሱ ላይ ደርሶ ሲያዩት ያሳለፉት የትካዜና የባዶነት አመታት በደማቅና በተስፋ በተሞሉ የእርግዝና ወራት ተተኩ፤ ምስጋና ለእናቶችና ለህፃናት ህክምና ልዩ ትኩረት ለሰጠው የጠና ፖሊሲ፤ እሱን ተከትሎ ተግባራዊ ለሆነው የህክምና ትስስር (Referral System) እና ለአይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሃኪሞች ይሁንና ወ/ሮ ለታይ ሶስት ልጆችን በአንድ ጊዜ በሰላም ተገላገሉ፡፡
ሆኖም ወ/ሮ ለታይ ከቀናቸው በፊት (ከዘጠኝ ወር በፊት) የወለዱ በመሆኑ እንዲሁም ሁሉም ልጆቻቸው ከአንድ ኪሎ በታች ሆነው የተወለዱ በመሆኑ በሆስፒታሉ ሙቀት ክፍል ውስጥ (Neonatal intensive care unit NICU ) እንዲቆዩ ተደረጉ፡፡ በሆሲፒታሉ የህፃናት ስፔሻሊስት ሃኪሞች/ ነርሶች ያላሰለሰ ጥረት ለሁለት ወራት በክፍሉ ከታከሙ በኋላ የልጆቹ ጤናቸው ሁኔታ በጣም በመሻሻሉ ከነሙሉ ጤናቸው ወደቤታቸው ተሸኙ፡፡
ጥንዶቹም ሁለት ሆነው ወጥተው አምስት ሆነው ወደ መኖሪያ ቄያቸው ተመለሱ፡፡ከሁለቱ የለሆሳስ ንግግር በቀር ጭር ብሉ የነበረው ደሳሳ ጎጆአቸው በማያቋርጥ የጨቅላ ህፃናት ለቅሶና ጫጫታ ተሞላ፡፡ በአንድ ጊዜ የሶስት ህፃናት የማያቋርጥ ለቅሶ ከባድ እንደሆነ ማንም ሊገምተው ይችላል፡፡ ይሁንና ለነወ/ሮ ለታይ እንደ ትንግርት ነበረ፡፡
የወ/ሮ ለታይ የበዛ ትኩረት የልጆቻቸውን የእይታ ሁኔታ እንደጠበቁት አልሆን አላቸው እሳቸው ቀን ከሌት አይናቸው ለሶስቱም ልጆቻቸው መንቀል ቢያዳግታቸውም ህፃናቱ በተራችው ዓይናቸውን በደንብ እያዩቸው እየተከተሉቸው እንዳልሆነ ገባቸው፡፡ ሁኔታውን ሊጠይቋቸው ለመጡ ጎረቤትና ዘመድ ቢናገሩም ‘’እንዴ ተያቸው ገና ጨቅላ ህፃናት ናቸው’’ የሚል ምላሽ በማግኘታቸው ለጊዜው ‘’እፎይ’’ አሉ::
ይሁንና ይህ ንቁ የሆነ ምልከታቸው በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ሶስቱም ልጆቻቸው ጥቁሩ የዓይን ክፍል (ብርሃን ፊ) ነጭ ነገር እንደጣለባቸው አስተዋሉ፡፡ሁኔታው እንቅልፍ ቢነሳቸው በአቅራቢያቸው ወዳለ ጤና ጣቢያ ቢሄዱም ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ‘’የምሽት አልማዛቸው’’ ሁኔታ ያሳሰባቸው ወላጆች በሰላም ወዳገላገለቸው የአይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልይዘው ሄዱ፡፡ ወላጆቹ የልጆቻቸው የዓይን የችግሩ ግዝፈት የገባቸው የሆስፒታሉ ሃኪሞች ለተሻለ ህክምና ወደ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል (አዲስ አበባ) መሄድ እንዳለባቸው ሲነገራቸው ነው፡፡
እንደሙሉ ጨረቃ ፈክቶ የነበረው የነበረው ህይወታቸው በአንድ ጊዜ በስጋትና ጭንቀት ተወጠረ፡፡ አዲስ አበባ በምናችን እንሄዳለን? እዛስ ምን ይጠብቀናል? የልጆቻችንስ የዓይን ጤና መጨረሻ ምን ይሆናል? ፈጣሪስ ለምን አብዝቶ ፈተነን? የማያልቁ ጥያቄዎችና ጭንቀት…
የቤተሰቡን ጭንቀት የተረዳው ጎረቤትና ዘመድ አዘማድ በኢትዮጵያውያን የመረዳዳት ስሜት ቤተሰቡን በማገዙ ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል (አዲስ አበባ) አቀኑ፡፡..
እነዚህን የህይወት ውጣ ውረድ ፤የምኞት ፤የደስታ፤የጭንቀት ጊዚያትን ያሳለፉ ህይወታቸው በተስፋ፤ በደስታ፤በጭንቀት የተሞላባቸው የመጡበት የቦታ እርቀት፤ እድሜና የኑሮ ሁኔታ የደከመው፤ ሶስት ደሳስ የሚሉ ጨቅላ ህፃናትን ከሬዚደንት ሃኪሞች ጋር አብሬ አየሁኃቸው፡፡ የሶስቱንም ህፃናት ዓይን በጥልቀት መርምረን ችግሩን ለየን፡፡
አዘንኩ፤ በጣም አዘንኩ። እኔም ከሬዚደንት ሃኪሞች ፊትለፊት በማምሻ እድሜቸው በሶስት ልጆች በተባረኩ ጎልማሳ ወላጆች ፊት የመልካም የተስፋ ዜና ብስራትን የሚጠብቁት ዓይኖች እንዲሁም በተስፋ የህፃናት ዓይን ህክምና ላይ እንደሚሰራ ሃኪም ጥሩም መጥፎም ዜና ለወላጆች ስነግር ኖሬያለሁ፡፡
ዛሬ ከበደኝ ! ሰው መሆን አማረኝ ራሴን በእነሱ ጫማ ውስጥ መጨመር!እኔ ብሆን ምን ይሰማኛል? የሶስቱም የዓይን ብርሃን የሚቀበሉ ግርግዳ ከጨቅላነታቸው ጋር ተያይ በሚመጣ ችግር ተላቀዋል፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ መታከም አይችልም፡፡ ዘግይታችኋል፤ በመጨረሻ እድሜችሁ ያገኝችኃቸው ልጆች ሁሉም ዓይነ ስውር ሆነው ይኖራሉ! ለመናገር ከበደኝ ቁጭ አልኩና አወራኋቸው። ማናቸው? ስለኑሮአቸው እንደህመምተኛ ሳይሆን እንደጓደኛ (ቤተሰብ) አወራኋቸው፡፡ ከላይ የፃፍኩትን ታሪክ ነገሩኝ፡፡
ባለቅኔው ‘’ወንድ ልጅ እንዴት ያለቅሳል’’ ነበር ያለው? ወደ ውስጤ አነባሁ፡፡ የማይቀረውን መርዶ ባረዳኋቸው ወቅት የወላጆቹ በተለይ ወ/ሮ ለታይ ሀዘን ለቅሶ ዋይታ ስው ከሞተበት በላይ ነበር ፡፡
ይህ ከሆነ ሁለት አመት ሞላው፡፡ አሁን ለምን ፃፍኩት?
ገፊው ምክንያት “አንድ መልካም ያልሆነ ድርጊት ስታይ በእጅህ አስቁም ወይም ተናገር” በሚል ሃይማኖታዊ ምክር ምክንያት ነው፡፡
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በመዲናችን አዲስ አበባ በምክትል ከንቲባዋ የተመረቀው የእናቶችና ህፃናት ሆስፒል ነው፡፡ መንግስታችን ላለፉት አስር አመታት ገደማ የእናቶችና ህፃናት ህክምና ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በሺዎች የሚቆጠሩ የእናቶችና ህፃናትን ህይወት ለመታደግ ችሏል፡፡ ከፌደራል ጤና ሚኒስቴር አንስቶ ጤና ኬላ ድረስ ለዘርፉ በተሰጠው ትልቅ ትኩረት ትርጉም ያለው ለውጥ መጥቷል፡፡ የጨቅላ ህፃናት ሞት ከእጥፍ በላይ ቀንሷል፡፡ ይህ እጅግ በጣም የምኮራበት ተግባር ነው፡፡
ታሪካዊ ዳራ
የዓለማችን የጤና ታሪክ በምናጠናበት ወቅት የእናቶችና ህፃናትን የጤና አገልግሎት መሻሻል ጋር ተያይዞ በተለይም የጨቅላ ህፃናት ጤና አገልግሎት ከማሳለጥ ጋር በተገኛኘ ሆስፒታሎች የሙቀት ክፍል (Neonatal intensive care unit-NICU) ይገነባሉ፤ የጤና ባለሞያዎቹም በዘርፉ ይሰለጥናሉ፡፡ በመሆኑም ከቀናቸው በፊት የሚወለዱ ጨቅላ ህፃናት የክብደት መጠናቸው በጣም የቀነሰና ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ላሏቸው ህፃናት በሚደደረግላቸው እንክብካቤ በህይወት የመኖር ስፋ ይኖራቸዋል፡፡
ከ1920-30ዎቹ ባደጉት ሀገራት የተቀጣጠለው ይህ የአለም የጤና አብዮት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የእናቶችና ህፃናትን ህይወት ታድጎል፡፡ ይሁንና ይህንን የጤና አብዮት ተከትሎ በአውሮፓ እና ስሜን አሜሪካ መጀመርያ ክ1940-50 እ.አ.አ ቀጥሎም ከ1970-80 እ.አ.አ ሀገራቱ በየዓይነ ስውርነት ወረርሽኝ ተጥለቀለቁ፡፡ አለማችን ከፍተኛዉን የህፃናት የዓይነ ስውርነት አስተናገደች፡፡
በወርሃ ግንቦት 19650 እ.አ.አ የተወለደው ታዋቂው ጥቁር አሜሪካዊ ዘፋኝም Stevie Wonder የዚሁ በሽታ ተጠቂ ነበር፡፡ የጊዜዉ አዲስ በሽታ Retinopathy of Prematurity (ROP)- ከጨቅላነት ጋር በተያያዘ የብርሃን መቀበያ የደም ስሮች መቀንጨር የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡
ROP ( ከጨቅላ ህፃናት ጋር በተያያዘ የብርሃን ተቀባይ የደም ስሮች መቀንጨር)ምንድነው?
ብርሃን የሚቀበለው የዓይን ክፍል(Retina) ያሉ የደም ስሮች እድገታቸው በአግባቡ አጠናቀው መላውን ብርሃን ተቀባይ ክፍል ለመሸፈን ፅንሱ የ9 ወራት ቆይታውን በእናቱ ማህፅን መቆየት ይኖርበታል፡፡ በእናት ወደ ፅንሱ የሚተላለፉ ሆርሞኖችና ኦክስጂን በብርሀን ተቀባይ የደም ስሮች ለመፈጠር ወሳኝ ናቸው፡
በመሆኑም ከግዜያቸው ቀደም ብለው የሚወለዱ ጨቅላ ህፃናት ብርሀን ተቀባይ የደም ስሮቻቸው መላውን ብርሃን ተቀባይ የዓይን ክፍል(Retina) ሳይሸፍኑ ይቀራሉ፡፡ ጨቅላ ህፃናቱ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሙቀት (Neonatal intensive care unit NICU) ይቆያሉ፡፡ በጤና ባለሞያዎች ያላሰለሰ ክትትል፤ በሚሰጣቸው የኦክጂንና ሌሎች አስፈላጊ ህክምናዎች ህይወታቸውን ማትረፍ ይቻላል፡፡
ይሁንና በደም ስር ያልደረጀው ብርሀን ተቀባይ የዓይን ክፍል(Retina) ተፈጥሮያዊ ባልሆኑ አዳዲስ የደም ስሮች( New Vessels) ይወረራሉ፡፡ ተፈጥሮያዊ ባልሆኑ አዳዲስ የደም ስሮች( New Vessels) በቀላሉ ይደማሉ ችግሮቹ ታይተው በወቅቱ ካልታከሙ ብርሀን ተቀባይ የዓይን ክፍል(Retina) እንዲላቀቅ (Retinal Detachment) ሊዳርጉ በሂደትም ዓይነ ስውርነት ይዳርጋሉ፡፡
እንግዲህ ባጭሩ Retinopathy of Prematurity(ROP) ከጨቅላነት ጋር የተያያዘ የብርሃን መቀበያ የደም ስሮች መቀንጨር ማለት ይህ ነው፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት በሙቀት ክፍል (Neonatal intensive care unit) በሚሰጠው ክትትልና ህክምና ምስጋና ለጤና ባለሞያዎች ይሁንና እነዚህ ጨቅላ ህፃናት ህይወታቸው ለመታደግ ተችሏል፡፡ በዚህም መንግስትም የጤና ባለሞያዎችም ባደረጉት ጥረት የሚያኮራ ውጤት ተገኝቷል፡፡
ይሁንና Retinopathy of Prematurity (ROP) ከጨቅላነት ጋር የተያያዘ የብርሃን መቀበያ የደም ስሮች መቀንጨር በቂ እውቀት ግንዛቤ ስለሌለ አሁን አሁን Retinopathy of Prematurity (ROP) ምክንያት ህይወታቸው ተርፎ የዓይነ ብርሃናቸውን የሚያጡ ጨቅላ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ ነው ፡፡ ከ80 አመት በፊት የተፈጠረ ክስተትን ያልጠየቀ ሕዝብና መንግስት “3ኛውን የዓይነ ስውርነት ወረርሽኝ” ለማስተናገድ መንገዱን ተያይዘውታል፡፡
ከ80 አመት በፊት የተፈጠረ ክስተትን ያልጠየቀ ሕዝብና መንግስት “3ኛውን የዓይነ ስውርነት ወረርሽኝ” ለማስተናገድ መንገዱን ተያይዘውታል፡፡
የ ROP ከጨቅላ ህፃናት ጋር በተያያዘ የብርሃን ተቀበይ የደም ስሮች መቀንጨር) አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናችው?
- ከቀኑ ቀድሞ መወለድ ( በተለይ ከ 34 ሳምንት እርግዝና በፊት መወለድ
- የውልደት ክብደት መጠን ማነስ ( ከ2500 ግራም በታች መሆን
- ተያያዥ የጤና እከሎች የሳምባ በሽታ… ለዚህም ሲባል የኦክስጂን ህክምና መውሰድ
ሌሎችም ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው ፡፡
ምን ይደረግ ?
ያደጉ ሀገራት ክ1940-50 እ.አ.አ ቀጥሎም ከ1970-80 እ.አ.አ ካጋጠማቸው የህፃናት ዓይነ ስውርነት ማዕበል በኋላ በሙቀት ክፍሎቻቸው (Neonatal intensive care unit) ከሚሰጠው የጨቅላ ህክምና ጋር ተያይዞ የ ROP ልየታ (ROP Screening) አንዱ የህክምናው ክፍል አድርግዋል፡፡
ባደጉ ሃገራት ሙቀት ክፍል (Neonatal intensive care unit) ያላቸው የጤና ተቋማት የዓይን ምርመራን ግድ ያደርጋሉ፡፡ የነዚህ ጨቅላ ህፃናት ብርሃን የሚቀበለው የዓይን ክፍል ቀደም ብሎ የበሽታው ምልክት ከታየ በኋላ በሚደረጉ ህክምናዎች በቀላሉ በህፃናቱ ላይ የሚከሰቱ ዓይነ ስውርነት መከላከል ይቻላል፡፡
በሃገራችን አሁን ባለው ሁኔታ በጥቂት ተቋማት (ጥቁር አንበሳ፤ዳግማዊ ምኒሊክ እና የተወሰኑ የግል ተቋማት) በቀር ህክምናው እየተሠጠ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ እኔ በመራሁት ጥናት ጥቁር አንበሳ፤ዳ/ሚኒሊክ ሙቀት ክፍል(NICU) ተኝተው ህክምና ሲየገኙ ከነበሩ ጨቅላ ህፃናት መካከል 48 % (መጠኑ ቢለያይም) ROP ነበረባቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ችግሩ ያለባቸው በጊዜው በመታየታቸው ብርሃናቸውን መታደግ ተችሏል፡፡
በእኔ እይታ ባደገ /በሰለጠነ ሃገር /ማህበረሰብ ሴቶችና ህፃናት ከፍ ብለው ይታያሉ፡፡ በዚህም አኳያ በቅርቡ የተመረቀው የህፃናትና እናቶች ሆስፒታል የህፃናትና ሴቶችን ጤና ከፍ ከማድረግ አካያ የሚኖረው ድርሻ በጉልህ ሊታይ የሚችል ነው፡፡
ይሁንና ከሌሎች ሃገራት ተምረን የህፃናትን የሞት የመቀነስ ግቦች የህፃናት ዓይንን ታሳቢ ካለደረግን በቀጣዩ ትውልድ እንዲሁም በሃገር ላይም ትልቅ ችግር ማኖራችን አይቀርም፡፡ሁሉም የህፃናት የጤና ግቦች ፤ ጤናማ ውጤታማ አምራች ትውልድን አሻግረን ማየት አለብን፡፡ የወ/ሮ ለታይ አይነት አሳዛኝ ታሪክ ሁሉም ሊማርበት ይገባል፡፡
ክቡር ህይወትን አትርፎ የነፃነት ቀንዲል ለመሆነ የሰውነት ክፍል (እይታ) ግድ የለሽነት ተገቢ አይደለም፡፡ አዲሱን ሆስፒታል ጨምሮ የሙቀት ክፍል ያላቸው የጤና ተቋማት በሙሉ የህፃናት ዓይን ህክምና አገልግሎት አሰጣጡ አንዱ ክፍል ሊሆን ይገባል፡፡
እኔና ባልደረቦቼ አሁንም በየቀኑ የወ/ሮ ለታይ እይነት ታሪከ ያገጥመናል፡፡ የመወሰን ስልጣን ያለችሁ ሰዎች ምክራችንን ስሙ!!
እይታ የነፃነት ቀንዲል ነው፤ ሕይወት ሰጥተን ብርሀን አንንፈግ!!
Dr Sadik Taju Sherief a consultant Pediatrics and Strabismus Ophthalmologist at Menelik II Hospital and holds the rank of assistant professor at the School of Medicine, College of Health Sciences, Addis Ababa University. Following a Medical Doctorate degree from Jimma University, he completed residency training in Ophthalmology at Addis Ababa University. He then went to a subspecialty fellowship training in Pediatrics Ophthalmology and Strabismus at The Hospital for Sick Children’s, Toronto, Canada. Since returning to Ethiopia, his clinical practice and research have focused on pediatric glaucoma, cataract, retinoblastoma, retinopathy of prematurity, Strabismus and as well as other anterior segment abnormalities. Currently, he is also the chair of the department of ophthalmology, Addis Ababa University and Secretary General of Ophthalmological Society of Ethiopia.