የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በውይይት ለመፍታት እንዲያስችል ሶስት የቀድሞ አፍሪካ አገራት መሪዎችን ያቀፈ አንድ ልዩ ልዑካን ቡድን መሰየማቸውን የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ቢሮ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት ዮኣኪም ቺሳኖ - የቀድሞ የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት፣ ኤለን ጆንሰን-ሲርሊፍ የቀድሞ ላይቤሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንትና ኬጋሌማ ሞትላንቴ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ልዩ ልዑክ ሆነው ደቡብ አፍሪካ ተገኝተው ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ስላለው ግጭት ሁኔታ ለፕሬዚደንት ራማፎሳ ገለጣ አድርገዋል።
ፕሬዚደንት ራማፎሳ በበኩላቸው እንደ አፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነታቸውና የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ቤተሰብነታቸው ተቀስቅሶ ያለው ግጭት ጥልቅ ስጋት ያሳደረባቸው መሆኑንና በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚካሄድ ውይይት ከዕልባት ላይ እንዲደርስ ያላቸውን ብርቱ ፍላጎት ለፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ገልጠዋል።
አያይዘውም ለግጭቱ ዕልባት ማበጃ የሚያግዝ ሶስት የቀድሞ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን የአፍሪካ ሕብረት ልዩ የልዑካን ቡድን አባላት አድርገው መሰየማቸውንና በዚሁ መንፈስም በቀጣይ ቀናት ውስጥ ልዑካኑ እህት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ተናግረዋል።
የልዩ ልዑካኑ ቀዳሚ ተግባርም በግጭቱ ውስጥ ካሉ ወገኖች ጋር ሁሉ ግጭቶቹ የሚቆሙበትን፣ በአካታች ብሔራዊ ውይይት ለግጭቱ አስባብ የሆኑ ጉዳዮች ዕልባት የሚያገኙበት፣ ሰላምና መረጋጋትን ዳግም በኢትዮጵያ ማስፈን እንደሆነ የሕብረቱ ሊቀመንበር መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም፤ የሊቀመንበሩ ተነሳሽነት አፍሪካን ከግጭት ነፃ ለማድረግ "የጠመብንጃዎችን ላንቃ ፀጥ ማሰኘት" እና "አፍሪካዊ መፍትሔዎች ለአፍሪካዊ ችግሮች" ከሚለው የአፍሪካ ሕብረት ዓላማ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ይህንኑ ተነሳሽነት በመቀበል ለልዩ ልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን ያደነቁ መሆኑን አንስቷል።
በተያያዥነትም ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ አሁን ተከስቶ ላለው ግጭት ታሪካዊ መንስኤዎቹን ማስረዳታቸውንና ፕሬዚደንት ራማፎሳም የፕሬዚደንቷን ገለጣ በመልካም ጎኑ መቀበላቸውንም መግለጫው አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ አንዳለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ባወጣው ማስተባባያ "የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ቡድን ጋር ሊደራደር ነው በሚል የተሰራጨው ወሬ ሃሰት ነው" በማለት አስታውቆ ሆኖም "ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የሆኑትን የሲሪል ራማፎሳ ልዑካን ተቀብለው በግል ይወያያሉ" ብሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ በመቋጫነት "ድርድርን አስመልክቶ የፌዴራል መንግሥት ያለው አቋም ፈጽሞ ያልተለወጠ ነው" ሲል አስታውቋል።