የዘውድ ምክር ቤቱ ፕሬዚደንት አያይዘውም "የልዑል አለማየሁን ህልፈተ-ሕይወት አስመልክቶ ለተደረገው ዝክርና ጸሎተ- ፍትሃት፣ የኢትዮጵያን ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ። ለግማሽ ምዕት ዓመት ግድም፣ የዐጼ ቴዎድሮስ ቀጥተኛ ተወላጆችና ቤተስቦች ይሄንን ዕድል እስከዛሬ ድረስ ያላገኙ በመሆናቸው ቤተሰባዊ ሸክምና ሃዘናቸውን አቅልሎላቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለብዙ ዓመታት ያዘሉት ግዙፍ ታሪካዊ ሸክምና ጫና ቀላል አልነበረም። እግዚአብሔር የልዑል ዓለማየሁን ጸሎተ-ፍትሃትና የመታሰቢያ ዝክረ-በዓል ቤተሰቡ እንዲያይ ስለፈቀደ ምንም ነገር ለማይሳነው አምላካችን ክብረትና ምስጋና ይግባው። ለአጼ ቴዎድሮስ ቤተሰብና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አለን" ሲሉ በምስጋና የታጀበ ደስታቸውን ገልጠዋል።

ከኢትዮጵያውያኑም ባሻገር ለእንግሊዝ ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ ባቀረቡት ምስጋናም "መቼስ፣ በአንድ እጅ እንደማይጨበጨበው ሁሉ፣ እስካሁንም ድረስ፣ ላልተቋረጠው ለጋስነታቸው ለንጉሥ ቻርልስ 3ኛ ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን። ዲን ዊንድዘርና ዊንድዘር ካስል ውስጥ ለሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንም እንደዚሁም በዘውድ ምክር ቤታችን ስም ሆኜ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።

በመጨረሻም የዘውድ ምክር ቤቱ "የልዑል አለማየሁ ሕልፈተ-ሕይወትና የመታሰቢያ ዝክረ-በዓል ለወደፊቱም ድልድይ በመሆን፣ ታሪካችን፣ ባሕልና ዕሴቶቻችን ሕዝብን ከሕዝብ ለማቀራረብ፣ እንዲሁም ለሰው ልጆች ተስፋ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ምሕረትና አንድነት እንድናውለው ያብቃን። ኃያሉ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይጠብቅልን" ሲል መግለጫውን አጠናቅቋል።

