1. መግቢያ
ኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ልታከብር ጥቂት ቀናት ይቀራታል። ይህ የዘመን መለወጫ አብዛኛው የዓለማችን ሀገራት ከተቀበሉት የግሪጎሪያኑ ዘመን መለወጫ ልዩነት አለው። ልዩነቱ በዓመት ቆጠራውና በሰዓት አደረጃጀቱም ጭምር ነው።
የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከአብዛኛው ዓለማችን ከሚጠቀምበት የግሪጎሪያን አቆጣጠር ከመስከረም 1 እስከ ታህሳስ 20/21 ድረስ በሰባት ዓመት፣ ከታህሳስ 20/21 እስከ መስከረም 1 በስምንት ዓመት ይለያል።
የግሪጎሪያኑን አቆጣጠር በሚከተሉ ዘንድ ቀን የሚጀምረው ከግማሽ ለሊት ሲሆን፣ የኢትዮጵያውያኑ ደግሞ ከንጋት ላይ ነው።
ለመሆኑ ይህ ልዩነት ከምን መጣ የሚለው በየጊዜው በተወሰነ ደረጃ ማብራሪያ ቢሰጥበትም አብዛኛው ማብራሪያ አጥጋቢ ካለመሆኑም በላይ ከእምነት ጋር እየተጋመደ በቀላሉ ለመረዳት አስቸጋሪ ሲሆን ይስተዋላል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በመፅሀፍ መልክ ሰፋ አድርገን ያቀረብን ቢሆንም፣ መፅሀፉ አሜሪካ በመታተሙና በኢትዮጵያ በስፋት ባለመሰራጨቱ ለአሁን ዘመን መለወጫ በተወሰነ ደረጃ የማስታወቂያ ያህል ማንሳቱ ተገቢ መሰለን።
2. የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር
በኢትዮጵያ አቆጣጠር አንድ ዓመት 365 ቀናት ሲኖሩት በአራት ዓመት አንዴ 366 ይሆናል። ይህ 366 ቀናት የሚይዘው ዓመት በእንግሊዝኛው ሊፕ ዓመት ይባላል። የኢትዮጵያው አቆጣጠር በተለይ በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ዘንድ እነዚህ አራት ዓመታት በወንጌሎች ስምም ይጠራሉ።
እነዚህም እንደቅደምተከተላቸው ዘመነ ዮሀንስ፣ ዘመነ ማቲዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ እና ዘመነ ሉቃስ ናቸው።
ዘመነ ሉቃስ ዓመቱ 366 ቀናት የሚይዝበት ሊፕ ዓመት ነው። ይህን በመከተል፣ አዲስ ዓመት ሲለወጥ እንደየዓመቱ አመጣጥ፣ እንኳን ከዘመነ ዮሀንስ ወደ ዘመነ ማቲዎስ፣ ከዘመነ ማቲዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ፣ ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ፣ ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሀንስ በሰላም አሸጋገራችሁ የሚለውን መስማት የተለመደ ነው።
ይህ በእራሱ ሲታይ የኢትዮጵያው ዘመን አቆጣጠር በቀጥታ ከክርስትና እምነት በተለይ ከኦርቶዶክስ ሀይማኖት ጋር የተያያዘ ያስመስለዋል።
በተጨማሪም የግሪጎርያኑም ሆነ የኢትዮጵያው አቆጣጠር ዘመኑን ‘ኢራ’ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ እና ድኅረ ልደተ ክርስቶስ ብሎ መክፈሉ በራሱ በተለይ ለተራው ሕዝብ የዓመቱ መጀመሪያ/ዘመን መለወጫ ቀኑም በቀጥታ ከእምነቱ/ከክርስትና እምነት ጋር የሚገናኝ መስሎ እንዲታየው ያደረገው ይመስላል። ይህ አመለካከት የቤተክርስትያን ሰባኪዎችንም ይጨምራል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያውም ሆነ የግሪጎሪያኑ አዲስ ዓመት ከክርስትና እምነት ጋር የሚያያይዘው ነገር አለ ወይ የሚለውን በቅድሚያ ለመመልስ እንሞክራለን።
የኢትዮጵያው አቆጣጠር ጥብቅ ዝምድናው ከግብፁ አቆጣጠር ነው።
የግብፁ አቆጣጠር 30 ቀናት ያላቸው 12 ወራትና አምስት ቀን በሊፕ ዓምት ደግሞ 6 ቀናት ያለው ጳጉሜን አለቸው። ይህ አቆጣጠር የተጀመረበት ዘመን በማያወላውል መልኩ ባይታወቅም ቢያንስ ከመጀመሪያው ስርወመንግሥት ጀምሮ ስራ ላይ ውሎ እንደነበር ማስረጃዎች አሉ። ይህም ቢያንስ የአምስት ሺህ ዘመን ባለቤት ያደርጋዋል።
የግብፁ አቆጣጠር ከመነሻው ዓመት 365 ቀናት የያዘ ነበር። አቆጣጠሩ ከወቅቱ እየሸሸ በመምጣቱ ወደኋላ ላይ በአራት ዓመት አንድ ቀን በመጨመር ዓመት ልክ በአሁኑ ግዜ የኢትዮጵያው አቆጣጠር ያለውን አይነት ቀመር ለመያዝ በቃ።
ይህ ጭማሪ የተደረገው ከክርስቶስ ልደት በፊት (ከቅድመ ጋራ አቆጣጠር) 300 ዓመት አካባቢ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሆነው ከሁለት ምዕተ ዓመት በኋላ በሮማው ንጉሠ ነገሥት አጉስተስ ትዕዛዝ በ23 ቅጋአ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ለውጡን ለመቀበል የግብፅ ቀሳውስት አሻፈረኝ በማለታቸው ነበር። ማስተካከያ የተደረገበት የግብፅ አቆጣጠር የእስክንድሪያ አቆጣጠር በመባልም በስፋት ይታወቃል።
የጥንቱም ሆነ የሊፕ ዓመት ማስተካከያ ከተደረገበት በኋላ ያለው የግብፅ አቆጣጠር ዓመት የሚጀምርበት ቶት በተባለው ወር የመጀመሪያ ቀን ነው። ይህ ወር ካለምንም ልዩነት ከኢትዮጵያው መስከረም ጋር አንድ ነው። ሌሎቹ በግብፅ አቆጣጠር ያሉት ወራትም መሳ ለመሳ ከኢትዮጵያው ወራት ይገጥማሉ። ይህ አንድነት በሁለቱም አቆጣጠሮች ያለውን የዘመን መለወጫን ቀንንም ይጨምራል።
የግሪጎርያን አቆጣጠር በመሰረቱ የጁሊያን አቆጣጠር ነው።
ወራቱ ከእነስማቸው፣ ሊፕ ዓመት የሚጨመርበት ወር፣ እንዲሁም ዓመት የሚጀምርበት ባጠቃላይ አንድ ነው። ልዩነቱ በሊፕ ዓመት ላይ በተደረገ ማስተካከያ ምክንያት የመጣ ነው። የዘመን አቆጣጠሩ ግሪጎሪያን መባሉ በጁሊያን አቆጣጠር ዓመቱ ከወቅቱ እየራቀ በመምጣቱ የካቶሊክ ጳጳስ የነበሩት ግሪጎሪ ስምንተኛው ማስተካከያ በ1582 (እንደ ግሪጎሪያን አቆጣጠር/እግአ) በማድረጋቸው ነው።
ይህን ያስተዋሉት ፋሲካ በኒቂያው ስብሰባ ‘ኮንፈረንስ’ (325 ጋአ፣ እግአ) ከቨርናል/ማርች ኢኪኖክስ በኋላ ውሎ ስለነበር ነው። ይህ ቨርናል ወይም ማርች ኢኪኖክስ የሚባለው የሚያርፈው ማርች 20/21 ነበር። ቨርናል ኢኪኖክስ በግሪጎሪ ስምነተኛ ዘመን ማርች 20/21 አላረፈም።
ስለዚህም ይህን ለማስተካከል 10 ቀን ከመጨመራቸውም በላይ ወደፊት ይህ ችግር እንዳይመጣ ክፍለዘመናት ሲደፍኑ ለ400 የማይካፈሉት ሊፕ ዓመት እንዳይሆኑ አደረጉ። ማለትም ሊፕ ዓመት ሁልግዜ የሚውለው አለምንም ክፍልፋይ ለአራት የሚካፈለው ዓመት ላይ ሲሆን፣ ይህ ዓመት ግን ክፍለዘመን መድፈኛ ከሆነ ለአራት ብቻ ሳይሆን ለአራት መቶም አለምንም ቀሪ ክፍልፋይ መካፈል አለበት።
ለምሳሌ፣ 2000 ሊፕ ዓመት ሲሆን፣ 2100፣ 2200፣ እና 2300 አይደሉም። በክፍለዘመን ደረጃ ተመልሶ ሊፕ ዓመት የሚሆነው 2400 ነው። በዚህ ስሌት መሰረት ዓመት በአማካይ 365.2425 ቀናት ይኖሩታል። ይህ ለፀሀይ ዓመት ከጁሊያን አቆጣጠር ይልቅ የቀረበ ነው። የጁሊያን አቆጣጠር ልክ እንደኢትዮጵያዊው አቆጣጠር ዓመት በአማካይ 365.25 ቀናት ሲኖሩት፣ ፀሀይ መሬትን ለመዞር የሚፈጅባት ግዜ ደግሞ በአማካይ 365.2422 ነው።
የጁሊያን አቆጣጠር የመጣው ከሮማን አቆጣጠር ነው።
ጁሊየስ ቄሳር የሮማ ንጉሠ ነገሥት እንደሆነ ዝብርቅርቅ የነበረውን የሮማን አቆጣጠር በማስተካከል በግብፁ መሰረት አንድ ዓመት 365 ቀናትና በሊፕ ዓመት ደግሞ 366 ቀን እንዲኖረው አደረገ። ከጁሊየስ ቄሳር ማስተካከያ በፊት የሮማን አቆጣጠር ዓመት የሚጀምረው ከማርች ነበረ። ጁሊየስ ቄሳር ማስተካከያውን ያደረገው በጀንዋሪ አንድ በመሆኑ የዓመት መጀመሪያው ከሱ በኋላ በዚሁ ቀን ሆነ።
ይህ ሰው በዘመን አቆጣጠሩ ላይ ላደረገው አስተዋፅኦ ኩውንቲስ የተባለው ወር በስሙ ተሰየመለት። ጁላይ የሚለው የመጣው ከዚሁ የሮማን ንጉሥ ስም ነው። ኩንቲስ ማለት አምስት ወይም አምስተኛ ማለት ነው። ይህም በድሮው የሮማን አቆጣጠር ጁላይ አምስተኛ ወር ስለነበረ ነው። ዛሬ ላይ እነሴፕቲምበር (9ኛው ወር)፣ ኦክቶበር (10ኛው ወር)፣ ኖቮምበር (11ኛው ወር)፣ እና ዲሴምበር (12ኛው ወር) መነሻ ትርጉማቸው ሰባት/ሰባተኛ፣ ስምንት/ስምንተኛ፣ ዘጠኝ/ዘጠንኛ እና አስር/አስረኛ እንደቅደምተከተላቸው ማለት ናቸው። ለዚህ ምክንያቱ በጥንታዊ ሮም፣ ከላይ እንደገለፅንው፣ ዓመቱ የሚጀምረው በማርች ላይ ስለነበረ ነው።
ጁሊየስ ቄሳር የነገሠው ከክርስቶስ መወለድ በፊት ነው። የሞተውም/የተገደለውም በ44 ቅጋአ (እግአ) ነው። የእነዚህ ሁለት አቆጣጠሮችን የዘመን መለወጫ ከክርስትና እምነት ጋር ማገናኘት ካለም በኋላ ላይ የመጣ መሆን አለበት። ከመነሻቸው ክርስትና ከመፈጠሩ በፊት የነበሩ ከክርስትና ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ናቸው።
የኢትዮጵያው አቆጣጠርም ሆነ የግሪጎሪያን አቆጣጠር ከክርስትና እምንት ጋር የሚያይዛቸው ዘመንን ለጋራ መለኪያ ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላ እያሉ መክፈላቸው ነው። ዘመኑ ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላ ይባል እንጂ ቅመራው ገብርኤል ለማርያም እንደምትፀንስ ያበሰረበት ቀን ነው ከሚለው በመነሳት ነው።
የኢትዮጵያዊም ሆነ የግሪጎሪያን አቆጣጠር ዘመን መለወጫ ከክርስትና እምነት ጋር የሚያገናኛቸው የለም ማለት ነው።
በዚህ ረገድ በኦርቶዶክስም ሆነ በካቶሊክ ቤተክርስትያኖች ቀኑ ልዩነት አልነበረውም። ይኸውም ማርች 25 ነው። የዚህ ብስራት ቀን በሁሉም አንድ ተደርጎ ቢወሰድም፣ ዓመቱ ላይ ግን ልዩነት አለ።
ይህ ልዩነት ነው የ7/8 ዓመት በኢትዮጵያውና በግሪጎሪያኑ ዘመን አቆጣጠሮች መሀከል ያመጣው።
ለዚህ ሁለቱም አቆጣጠሮች የተከተሉት ቅመራዎች የተለያየ በመሆኑ ነው። በሁለቱም አቆጣጠሮች ዓለም ተፈጠረች ብለው የሚስያቡበት ቀን እሁድ ዕለት ሲሆን በእድሜ ደረጃም ልዩነት የለውም። ልዩነቱ በግሪጎሪያኑ 5500 ቅጋአ ሲሆን፣ በኢትዮጵያው ደግሞ 5993 ቅጋአ ነው። ይህ ከፊል ዓመቱ ሰባት፣ ሌላው ከፊል ዓመት ስምንት ዓመት ልዩነት የመጣው የዘመን መለወጫ ቀኑ የሚያርፍበት ወራት በመለያየቱ ነው።
የግሪጎርያን አቆጣጠር የሚከተለው ዲዮኒሱስ ኤክስጉስ ያወጣውን ስሌት ነው። ይህ ሰው ዘመን የሚጀምርበት ከክርስቶስ መወለድ/መፀነስ ጋር መሆን አለበት በሚል በ525 ጋአ “የራሱን ቀመር” አበጀና ከዚያን ግዜ ጀምሮ ያለውን አኖ ዶሚኒ ‘ዓመተ እግዚእ’ የሚል ስያሜ ሰጠው። ዲዮኒሱስ ኤክስጉስ ቀመሩን ምንጭ ሳይጠቅስ የወሰደው ከሱ ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው ፓኖዳሩስ ከተባለ ሊቅ ነው (ለዝርዝሩ ግርማ፣ 2016፡49ን ይመልከቱ)።
የዲዮኒሱስ/ፓኖዳሩስ ቀመር አኒያኑስ ከተባለው በፓኖዳሩስ ዘመነ ከነበረው የእስክንድርያ ሊቅ ካስቀመጠው ቀመር የስምንት ዓመት ልዩነት ነበረው። የኢትዮጵያው አቆጠጠር የወሰደው አኒያኑስ ያወጣውን ቀመር ነው። ሲግበርት ኡሊሽ በኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፔድያ (2003፡733) ላይ የኢትዮጵያ አቆጣጠር የተከተለው የፓኖዳሩስን ስሌት ነው ያለው ስህተት ነው። ግርማን (2016፡149)ን ይመልከቱ።
የግሪጎሪያን/የጁሊያን አቆጣጠር የተከተለው የዲዮኒሱስ/ፓኖዳሩስ ስሌትም ሆነ የኢትዮጵያው አቆጣጠር የተከተለው የአኒያኑስ ስሌት ክርስቶስ ስጋ ለብሷል ከሚባልበት ግምት ጋር በኋላ ጥናቶች እንዳስተዋሉት መጠነኛ ልዩነት አላቸው።
በአብዛኛው የቤተክርስትያንና የጥንታዊ ታሪክ ሊቃውንት ዘንድ በአሁኑ ግዜ የሚታመንበት የእየሱስ መፀነስን ገብሬል ለማርያም ያበሰረበት ዓመት ከ6ኛው እስከ 4ኛው ቅጋአ (እግአ) ባለው ግዜ ውስጥ መሆን አለበት የሚለው ነው። ዝርዝሩ ሰፊ ስለሆነ እዚያ ውስጥ እዚህ አንገባም። በስፋት ለማወቅ ለፈልገ ግርማ (2016)ን እና በእዚያ የተጠቀሱ ስራዎችን ይመልክቱ።
የኢትዮጵያው አቆጣጠር አንዳንዴ የጁሊያን ካላንደር በማለት ሲገለፅ ቢስተዋልም፣ ከጁሊያን አቆጣጠር ጋር የሚያገናኘው በየአራት ዓመቱ አንድ ቀን መጨመራቸው እንደሆነና ይልቁንም ጥብቅ ዝምድናው ከግብፁ የእስክንድሪያ አቆጣጠር በመባልም ከሚታወቀው ጋር እንደሆነ ገልፀናል። የኢትዮጵያው አቆጣጠር ከግብፁ ጋር የሚያገናኘው በቀን አከፋፈልም ነው። በሁለቱም አቆጣጠሮች ቀን የሚጀምረው ከንጋት ላይ ሲሆን ምሽት ደግሞ ከቀኑ 12 ሰዓት በኋላ ነው።
3. የቀናት፣ የሳምንትና የወራት አደረጃጀት
ግዜን በማስላት ረገድ የምንጠቀምባቸው ከሞላ ጎደል ከተፈጥሮ ጋር የተያያዙ ናቸው። ቀን መሬት በራሷ ዛቢያ ላይ ከምታደርገው መሽከርከር፣ ማለትም ከቀንና ጨለማ መፈራረቅ ጋር ይገናኛል። ዓመት ከሞላ ጎደል ከወቅቶች መፈራረቅ ወይም መሬት ፀሀይን ለመዞር ከሚፈጅባት ግዜ ጋር፣ እንዲሁም ወር ወይም ለዚህ መነሻ የሆነው ፅንሰሀሳብ በአብዛኛው ዓለማችን ባሉ እና በነበሩ አቆጣጠሮች ከጨረቃ መውጣትና መግባት ጋር ይያዛል።
ወር የሚለው የአማርኛ ቃል በራሱ ጥንታዊ ምንጩ ጨረቃ ማለት ነው። ይህ ቃል በሁሉም ሴሚቲክ ቋንቋዎች ማለት ይቻላል በዚህ ፍቺው ይገኛል። ለምሳሌ፣ ከእነዚህ ቋንቋዎች ቀደምቱ በፅሁፍ ሰፍሮ በሚገኘው በአካዲያን √ወረኀ ሲሆን በጥንታዊ ደቡብ አረቢያን ቋንቋዎች ደግሞ √ወረሐ ነው። ጥንታዊ ልዕለ ስሩ *ወረሐ/ኀ ነው። ቃሉ አሁንም ከወርነት በተጨማሪ ጨረቃ የሚለውንም ይዞ የሚገኝባቸው ቋንቋዎች አሉ። ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለምሳሌ፣ በትግርኛ ወርሒ እና በግዕዝ ወርኀ ጨረቃም ወርም ማለት ናቸው። በበርካታ የአለማችን ቋንቋዎችም ያለው ተመሳሳይ ሁኔታ ነው። ለምሳሌ፣ በእንግሊዝኛ መንዝ ‘ወር’ እና ሙን ‘ጨረቃ’ ምንጫቸው አንድ ስርወቃል ነው።
ወር የሚለው የአማርኛ ቃል በራሱ ጥንታዊ ምንጩ ጨረቃ ማለት ነው።
በግዜ ፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ከላይ ከገለፅናቸው ለየት የሚለው የሳምንት እና የሰዓት ጉዳይ ነው። የሰዓት፣ የደቂቃም ሆነ የሰከንድ ክፍልፋዮች በይሁንታ የተደረጉ ናቸው። ሳምንትም ከሞላ ጎደል በአብዛኛው አለማችን ክፍል ከተፈጥሮ ክስተት ጋር የተገናኘ አልነበረም። በጥንታዊ የግብፅ አቆጣጠር ሳምንት 10 ቀናት ሲኖሩት፣ ወራቱ በሶስት ሳምንት የተደራጁ ነበር።
ይኸው አይነት አደረጃጀት የፈረንሳይ አብዮት ባወጣው አዲሱ አቆጣጠር ተግባራዊ ሆኖ ነበር። ሰዓትም መቶ ደቂቃ ነበረው። በጥንታዊ ግዕዝ ሳምንት ስምንት ቀናት የያዘ እንደነበር አንዳንድ መረጃዎች አሉ።
ሳምንት የሚለው ቃል እራሱ ከስምንት ጋር የተያያዘ ይመስላል። በአብዛኛው የአለማችን ህብረተሰብ ሳምንት አብዛኛውን ግዜ አራት ወይም አምስት ቀናት በያዙ ከገበያ ቀናት አንፃር የተደራጀ ነበር። አሁንም የዚህ አይነት ሳምንት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አሁንም አሉ። በኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የሲዳማውን ባህላዊ አቆጣጠር መጥቀስ ይቻላል።
ከላይ ከቀረበው ትንሽ ከተፈጥሮ ክስተት ጋር ይያያዝ የነበረው የጥንታዊ ባቢሎንያን የሳምንት አደረጃጀት ነው። ጥንታዊ ባቢሎንያን ዓመታቸው በጨረቃ ወራት ላይ የተመሰረተ ከመሆኑም በላይ፣ ጨረቃ ስትወጣ የወሩ አንደኛው ቀን ሲሆን፣ ግማሽ ጨረቃ የምትሆንበት ሰባተኛው ቀን፣ የወር አጋማሽ በአማካይ 14 ቀን ጨረቃ ሙሉ የምትሆንበት፣ እንዲሁም ከእዚያ የሚቀጥለው ሰባት ቀን ጨረቃ ተመልሳ ግማሽ የምትሆንበት እና ከእዚያ ጨረቃ እስከምትጠልቅበት ያለው አራተኛ ሳምንት ነው።
የየሳምንቱ መጨረሻ ቀናት መጥፎ ቀን በመባል ይከበራሉ። ሙሉ ጨረቃ የምትሆንበት 14ኛው ቀን በተለየ መልኩ ይከበራል። ቀኑም ሻባቱ ይባላል።
የእብራይስጡ ሻባት ከዚህ ከባቢሎንያን ሻባቱ የተወሰደ እንደሆነ ይገመታል። የባቢሎንያን እራሱ ከሱሜሪያን ሳ-ባት በጥሬ ትርጉሙ የመሀል-እረፍት ከሚለው የተወሰደ ነው። ከዚህ ተመሳሳይ ቃል ሠመደተ /śmdt/ የሚል በጥንታዊ ግብፅም በጨረቃ አቆጣጠር ላይ ለተመሰረተው ወር ልክ እንደባቢሎንያኑ የወሩ አጋማሽን ወይም ሙሉ ጨረቃን የሚመለከት አለ። ፓርከር (1550:11 – 12)ን እና ግርማ (2016)ን ይመልከቱ።
በአጠቃላይ በጥንታዊ ባቢሎንያን አንድ ወር አራት ሳምንት ሲኖረው፣ አብዛኛው ሳምንት ደግሞ ሰባት ቀናትን ይይዛል። የዚህም ምክንያት የጨረቃ ዑደት በአማካይ 29.53059 ቀናት ነውና አንዳንድ ሳምንታት ከሰባት ቀን በላይ መዝለቃቸው ግድ ስለሚል ነው።
በአሁኑ ግዜ በአለማችን የምናየው በሰባት ቀናት ላይ የተደራጀው ሳምንት የመጣው ከአብራሀም እምነት ተፅዕኖ የተነሳ ነው።
ቀናቱም በቁጥር ወይም ከእምነቱ ጋር በተያያዙ ቃላት በበርካታ ቋንቋዎች የተሰየሙ ናቸው። ለምሳሌ እሁድ ማለት አንድ፣ ሰኞ ማለት ሁለት፣ ማክሰኞ ማለት (ማግስተ ሰኞ)፣ ረቡዕ ማለት አራት፣ ሀሙስ ማለት አምስት፣ አርብ ማለት (መሸ፣ ገባ)፣ የሰንበት ዋዜማ መሆኑን ለማመልከት፣ ቅዳሜ (ቀዳሚት ሰንበት) ነው።
እነዚህን ሙሉ በሙሉ በቁጥር ያደራጁም አሉ። ከዚህም ውጭ ሰኞን የስራ የመጀመሪያ ቀን አድርጎ ከመውሰድ ከሱ አንድ ብሎ መጀመር አለ። ይህ ዓይነቱ አሰያየም ለምሳሌ፣ በስላቪክ፣ በባልቲክ ቋንቋዎች፣ እና በሌሎች ትንሽ በማይባሉ የዓለማችን ቋንቋዎች አለ። ሩቅ ሳንሄድ በኦሮምኛም ለማክሰኞ ለመፎ ወይም ሆጃ ለመፎ ሁለተኛ ወይም ሁለተኛ ስራ [ቀን] የሚል እናገኛለን።
4. መደምደሚያ
በአንዳንድ ስራዎች የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከመነሻውም ከክርስትና ጋር ከመገናኘት አልፎ የእምነቱ ማሳያ ተደርጎ ሲቀርብ ይስተዋላል። በየዘመን መለወጫው ትንታኔ አቅራቢዎች ሆነው የሚቀርቡትም የቤተክርስትያን ሰዎች በመሆናቸው ይህ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ አስተዋፅዖ አድርጓል ማለት ይቻላል።
በዚህ መጣጥፍ የኢትዮጵያውያን የሲቪል አቆጣጠር አስመልክቶ ከእምነት/ከሀይማኖት ጋር ያለውን ግንኙነት በተወሰነ ደርጃ ለመመርመር ተሞክሯል። ሆኖም የዘመን አቆጣጠርና ሀይማኖት በአለማችን ላይ ያለውን ዝምድናና ልዩነት በስፋት አልተሄደበትም። ለዚህ በተወሰነ ደረጃ ለማወቅ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ያወጣነውን መፅሀፍና በዚያ የተጠቀሱ ስራዎችን እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የተፃፉ ሌሎች በቀላሉ የሚገኙ በርካታ ስራዎችን መመልከት ይቻላል።
የክርስትናው እምነት በዘመን አቆጣጠር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፈው በሳምንት አደረጃጀት ላይ ነው። ዛሬ በዓለማችን በሰባት ቀናት ላይ ያልተደራጀ ሳምንት ያለውን አቆጣጠር የሚከተል ሀገር ማግኘት ይከብዳል። ከዚህም በተጨማሪ የዘመን ‘ኢራ መነሻ’ ስሌቱ ትክክል ሆነም አልሆነም ከክርስትናው እምነት ጋር እንደሚያያዝ ከማንም የተሰወረ አይደለም።
ምንም እንኳ ለግሪጎሪያኑ እና ለኢትዮጵያዊውም ዘመን ‘ኢራ’ መሰረቱ የክርስቶስ መፀነስ ‘ኤንካርኔሽን’ ወይም ክርስትያኖች ገብርኤል ለማርያም እንደምትፀንስ መልዕክት ነገረ ብለው ከሚያምኑበት ቀን የሚነሳ ቢሆንም፣ በሁለቱም አቆጣጠሮች የዘመኑ መነሻ ከክርስቶስ መፀነስም ሆነ ልደት ጋር ልዩነት እንዳለው ገልፀናል።
ይህ ልዩነት ስላለ በአሁኑ ግዜ ማስተካከያ ማድረግ አለብኝ ብሎ የተነሳ ሀገር ግን እስከምናውቀው ድረስ የለም። ቆጠራ ስምምነት በመሆኑ መሰረት የጣለን አቆጣጠር መለወጥ ቀላል አይደለም። ለዚህም ነው በተለያዩ ግዜያት የተነሱ ሌሎች አቆጣጠሮች ብዙም ሳይቆዩ የከሰሙት።
በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያና ምናልባት ከሳውዲ አረቢያ በስተቀር የዓለማችን ሀገሮች የግሪጎሪያኑን አቆጣጠር ከወሰዱ በኋላ ዘመኑንም የተቀበሉት፣ ሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች ስለሆኑ አይደለም።
በእርግጥ በተወሰነ ደረጃ ከእምነቱ ለመራቅ ዘመኑን ‘ኢራ’ ጋራ አቆጣጠርና ቅድመ ጋራ አቆጣጠር በማለት በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል ይስተዋላል። ይህ በተባበሩት መንግሥታትም ተወሰዷል። ለዚህ በፈረንሳይ አብዮት ወቅት የተነሳውን አቆጣጠር መጥቀስ ይቻላል። በሶቭየትም ተመሳሳይ ሙከራ ነበር።
ዘመንን በዓመት እና በወራት አስልቶ ትክክለኛው የወቅት መፈራረቅ ማግኘት ቴክኖሎጂው ባላደገበት ዘመን ቀላል እንዳልነበረ ለማወቅ በዓለማችን ትላልቅ ስልጣኔ የነበራቸው ሀገራት ሳይቀሩ ይህ ነው የሚባል አቆጣጠር አለመኖሩ ምስክር ይመስለናል። በዚህ ረገድ የጥንታዊ ግብፆችና የባቢሎንያንን አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል።
ጥንታዊ ግብፆች ህይወታቸው ልክ እንደአሁኑም በአባይ ላይ የተመሰረተ ስለነበር የአባይ ሙላት በዓመት ዞሮ የሚመጣበትን አስልቶ ማግኘት ነበረባቸው። ይህን ለማድረግ ለረጅም ዓመት ቀን እየቆጠሩ አስልተው ለፀሀይ/ትሮፒካል ዓመት እጅግ የቀረበ አቆጣጠር አቅርበውልናል።
እንደዚሁም ጥንታዊ ባቢሎንያን በስነክዋክብት እና ሂሳብ ታላቅ እመርታቸው በዘመን አቆጣጠርም ላይ ታይቷል። ባቢሎንያን ዓመታቸውን የሚቆጥሩት በጨረቃ ወራት ነበር። አንድ ዓመት የሚሉትም 12 የጨረቃ ወራትን ነበር። 12 የጨረቃ ወራት ደግሞ ከትሮፒካል ዓመት በ11/12 ቀናት ያጥራል።
ጨረቃ ለመሬት እንደሚኖራት ቅርበትና ርቀት መሬትን ለመዞር የሚፈጅባት ግዜ የሚለያይ ሲሆን አጭሩ ወር 29.26 ቀናት፣ ረጅሙ ደግሞ 29.80 ቀናት ነው። ይህም በጨረቃ አቆጣጠር ዓመት 254 ቀናት አካባቢ ይይዛል።
ይህን የተረዱት ባቢሎንያን የጨረቃ ዓመት በ19 ዓመት 7 ወራት ወደኋላ ከትሮፒካል/የፀሀይ ዓመት መሸሹን አሰሉ። ይህን አስልተው 7ቱን ወራት በ3ኛ፣ 6ኛ፣ 8ኛ፣ 11ኛ፣ 14ኛ፣ 17ኛ፣ እና 19ኛ ዓመት ላይ በመበተን ሳጋ ያስገቡ ነበር።
ይህ የ19 ዐመት ዑደት በግዕዝ ዓውደ አበቅቴ የሚባለው ነው። ይህ አሰራር አሁንም በእስራኤሎች አቆጣጠር ላይ አለ።
እስራኤሎች አቆጣጠራቸው ብቻ ሳይሆን በርካታ ጥንታዊ ባህላቸው የባቢሎንያን ተፅዕኖ አለበት። ይህ ስሌት ፋሲካና ሌሎች ተንቀሳቃሽ በዐላትን ለማስላት ያገለግላል። በእርግጥ የፋሲካ ስሌት ከዚህም በላይ ትንሽ የተወሳሰበ ነው። ስሌቱ 28 የፀሀይ ዐመትን እና 19 የጨረቃ ዓመትን/አበቅቴን በመያዝ የሚሰላ ሲሆን ይህም በ532 (=28 X 19) ዓመት ዑደት የተቀመረ ነው።
ይህ ዑደት ታላቁ ዑደተ ፋሲካ ‘ግሬት ፓስካል ሳይክል’ ወይም በግዕዝ አውደ ቀመር ይባላል። ፓስካ ማለት ፋሲካ ነው። ሁለቱም ምንጫቸው አንድ ነው።
በዚህ አጭር መጣጥፍ ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ ስለዘመን አቆጣጠር ለማቅረብ ሞክረናል። የዘመን አቆጣጠር ውስጡ በደንብ ገብተን እንመርምረው ካልን ትንሽ ውስብስብ ነው። የጥሞና ንባብ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የትምህርት ዘርፎች በተለይ በስነክዋክብትና ሂሳብ ላይ ጥሩ ግንዛቤን ይጠያቃል።
የፀሀይ ዓመትን ከአውተመን ኢኪኖክስ እስከ አውተመን ኢኪኖክስ፣ ከቨርናል ኢኪኖክስ እስከ ከቨርናል ኢኪኖክስ፣ ከሰመር ሶሊቲስ እስከ ሰመር ሶሊቲስ፣ እንዲሁም ከዊንተር ሶሊቲስ እስከ ዊንተር ሶሊቲስ ያለውን ዙር በመየት ማስላት ይቻላል።
ሆኖም በእነዚህ ላይ በጣም አናሳ ይሁን እንጂ መጠነኛ ልዩነት መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ ከአንዱ በመነሳት የሚደረገው ስሌት ሁሌም እኩል ነው ማለት አይቻልም።
መልካም አዲስ ዓመት!
ግርማ አውግቸው ደመቀ፣ የምርምር ፕሮፌሰር
ኢኒስቲቲዩት ኦፍ ሴሚቲክ ስተዲስ፣
ፕሪንስተን፣ ኒው ጀርሲ
&
አፍሪካ ዎርልድ ፕረስ/ዘ ሬድ ሲ ፕርስ፣
ትሪንተን፣ ኒው ጀርሲ