ላለፉት ሰባት ወራት ወሲባዊ ጥቃትና ረሃብ በጦር መሣሪያነት እንደዋሉ የገለጡት ሰልፈኞች፤ የአውስትራሊያ መንግሥት ብርቱ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
"ትግራይን ማስራብ ይቁም!" ሲሉም በመፈክሮቻቸው አስተጋብተዋል።
ከተቃውሞ ሰልፈኞቹ አንዷ የሆኑት ሳሮን ብርሃን "እንደ ማኅበረሰብ ማየት የምንሻው አውስትራሊያ በንቃትና በግልጽ ወጥታ ጦርነቱን እንድታወግዝና ኢትዮጵያን ተጠያቂ እንድታደርግ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በዕለቱ በሥፍራው የተገኙት የምክር ቤት አባል ፒተር ክሃሊል አውስትራሊያ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ የቪዛ ዕቀባ አለመጣሏን አንስተው "እንደ መካከለኛ ኃይልና ከዓለም አንዷ አንጋፋ ዲሞክራሲያዊት አገር እንደመሆኗ፤ አውስትራሊያ ተሳትፎ የማድረግና ግጭቶችን የመፍታት ኃላፊነት አለባት" ብለዋል።
በፓርላማ ግድግዳዎች ላይም ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ግጭት የሚያሳይ አንድ የምስል ኤግዚቪሽን ለዕይታ በቅቷል።
በ2012 ወደ አውስትራሊያ የመጣው የ18 ዓመቱ ክብሮም በላይ አጎቱንና ሰባት ዘመዶቹን ያጣ መሆኑን ጠቅሶ ተጨማሪ የቤተሰብ አባላትን እንዳያጣ ከፍ ባለ ጭንቀት ውስጥ ያለ መሆኑን ተናግራል።
አክሎም " በኖርኩባቸው 18 ዓመታት ውስጥ ያለፉት ሰባት ወራት በእጅጉ አዋኪ ነበሩ" ብሏል።

Kibrom Belay. Source: SBS
ኤግዚቪሽኑ ያተኮረው የትግራይ ውጊያ ከጀመረበት ወርኃ ኖቬምበር አንስቶ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለግጭቱ መነሻ ሕወሓት በፌዴራሉ የሰሜን ዕዝ ጦር ላይ ጥቃት በማድረሱ እንደሆነ ገልጧል።
በግጭቱ ጎልተው ከሚነሱት አንዱ የወሲባዊ አመፅ ጥቃት ሰለባ የሆነች ሴት ለዶቼ ዌሌ እንደገለጠችው "በእያንዳንዱ ቤት እየገቡ ወንዶቹን አስገድደው ያስወጣሉ። እኔም ቤቴ ውስጥ እንድቆይ ተደርጌያለሁ። ከዚያም አስገድደው ወሲባዊ ጥቃት ፈጸሙብኝ። ሶስት ወታደሮች ናቸው አስገድደው ወሲባዊ ጥቃት የፈጸሙብኝ" ብላለች።
በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር "የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች እኒህን ግፎች ፈጽመው የተገኙ ከሆነ ለፍትሕ ይቀርባሉ የሚል አመኔታ አለዎት?" ተብለው ከSBS ለቀረበላቸው ጥያቄ "በእርግጥም አመኔታ አለኝ። የኢትዮጵያ መንግሥት የማረሚያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ ነው፤ ቃልም ገብቷል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በትግራይ ማኅበረሰብ በኩል በሰባቱ የጦርነት ወራት ምግብ ለመሳሪያነት እንደዋለ ሲነገር፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ትግራይ ውስጥ ያለው የረሃብ ሁኔታ በዓለም ላይ ከየትኛውም ሥፍራ በበለጠ አያሌ ሰዎችን ለረሃብ መዳረጉን አስታውቋል።

Source: SBS
ይሁንና አምባሳደር ሙክታር ግና የመንግሥታቸውን አቋም በማንጸባረቅ "የኢትዮጵያ መንግሥት ረሃብን ለጦር መሣሪያነት አውሏል የሚለው ክስ ፍጹም ፖለቲካዊ ተነሳሽነት ያለውና ሙሉ በሙሉ መሠረተ ቢስ ነው" ሲሉ አሌ ብለውታል።
በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ትግራይን መልሶ ለማቋቋም እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጠዋል።