አደገኛና ፈጣን ተዛማች በሆነው የእንግሊዝ ቬሪያንት ቫይረስ ሳቢያ በመላው ቪክቶሪያ ከዛሬ ዓርብ ከምሽቱ 11:59pm ጀምሮ ለአምስት ቀናት ጸንቶ የሚቆይ የኮሮናቫይረስ ገደቦች ተጥለዋል።
ገደቦቹን የመጣል ውሳኔ የተላልፈው የቪክቶሪያ ካቢኔ ዛሬ ማለዳ ላይ ተሰይሞ ከመከረ በኋላ ነው።
ሜልበርን ውስጥ ለባሕር ማዶ ተመላሾች በተዘጋጀው ሆሊዴይ ኢን ሆቴል ወሸባ ገብተው ከነበሩት ውስጥ 13ቱ በቫይረሱ ተጠቅተዋል።
የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ቫይረሱ በእጅጉ በፍጥነት ተዛማች በመሆኑ የቪክቶሪያ ማኅበረሰብን ለብርቱ አደጋ ስለሚያጋልጥ ገደቦቹን የመጣል እርምጃ በጣሙን አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት ከዛሬ ዕኩለ ለሊት ጀምሮ ለአምስት ቀናት ጸንተው የሚቆዩትን ገደቦች ተከትሎ ከቤት ውስጥ መውጣት የሚቻለው ለአራት ጉዳዮች ይሆናል።
- ለገበያ
- ግድ ለሚል ሥራ
- ከቤት ውስጥ ሆኖ መቀጠል ለማይቻል አስፈላጊ የሆነ ትምህርትና
- በቀን ለሁለት ሰዓታት የአካል እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ይሆናል።
ሌሎች የተጣሉ ገደቦች፤
- ፈቃድ ላለው ሥራ ለመሠማራት ካልሆነ በስተቀር ከቤትዎ ከ5 ኪሎ ሜትሮች በላይ ርቀው መሔድ አይችሉም
- ቪክቶሪያ ውስጥ በየትኛውም ሥፍራ ጭምብል ማጥለቅ ግድ ነው
- ወደ ማንም ሰው ቤት ለጥየቃ መሄድ አይቻልም
- ምንም ዓይነት የአደባባይ ሕዝባዊ ስብሰባ ማድረግ አይፈቀድም
- ትምህርት ቤቶች ክፍል ውስጥ መገኘት ግድ ከሚላቸውና ወላጆቻቸው ሥራ ገበታ ላይ ለመገኘት አስፈላጊ ከሆኑ ሠራተኞች ልጆች በስተቀር የመማሪያ ክፍሎቻቸው ዝግ ይሆናሉ
- ሃይማኖታዊ ስብስብና ሥነ ሥርዓቶችን ተሰባስቦ ማካሄድ አይፈቀድም
- በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከ10 በላይ ለቀስተኞች መገኘት አይችሉም
- የመስተንግዶ ግልጋሎት ሰጪዎች ግልጋሎቶች በቁም ያዘዙትን ይዘው በሚሄዱ ደንበኞች መስተንግዶ ብቻ ይወሰናል
- የሙዋዕለ ሕጻናት ክብካቤና አጸደ ሕጻናት ማዕከላት ክፍት ሆነው ይቆያሉ
- የአካል ማጠንከሪያ፣ የመዋኛ ሥፍራዎች፣ የማኅበረሰብ ማዕከላት፣ የመዝናኛ ሥፍራዎችና ቤተ መጽሐፍት ዝግ ይሆናሉ።