125ኛው የአድዋ ድል በዓል ዛሬ እሑድ ፌብሪዋሪ 28 በዙም ዌብናር ታዳሚዎች ተዘክሯል።
በዕለቱ በተዘጋጀው ዝክረ መታሰቢያ ፕሮግራም መሠረት በደቡብ አውስትራሊያ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተወካይ አማካይነት የአጤ ምኒልክ የአድዋ ዘመቻ ክተት አዋጅ ተነቧል።
በመቀጠልም በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠባባቂ ጉዳይ አስፈጻሚ በርይሁን ደጉ በዓሉን በልዩ ሁኔታ ለመዘከር ተሳትፎ ያደረጉትን በሙሉ፤ በዕለቱ በክብር ተናጋሪ እንግዳነት የተጋበዙ ተናጋሪዎችን፤ ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተርንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት የታሪክ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ የቅርስና ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌውን በማመስገን ፕሮግራሙን አስጀምረዋል።
ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተርንም በበኩላቸው፤ ከአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላት የ125ኛውን ክብረ በዓል በጋራ ለመዘከር በመጋበዛቸው ክብር የተሰማቸው መሆኑን በመግለጽ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

Beryihun Degu. Source: SBS Amharic
በከብረ በዓሉ ላይ ባሰሙት ንግግር "የአድዋ ድል በአንድ ቀን ብቻ ተከብሮ የሚያልፍ አይደለም። አፍሪካውያን ሁሉ ሁሌም የሚያከብሩት ነው። ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው አያሌ በረከቶችዋ ውስጥ አንዱና ዋና የአድዋ ድል ነው። ዛሬ ሰንደቅ ዓላማችን በብዙ የአፍሪካ አገራት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የነፃነት ምልክት እስከሚሆን አባቶቻችን አድርሰውናል። በዚህም ልንኮራ ይገባናል። አድዋን እኛ ብቻ ሳንሆን የምናከብረው በበርካታ የአፍሪካ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ይህን እያከበሩ ናቸው" ብለዋል።
አያይዘውም "የዳግማዊ አድዋን ታሪክ የምንሠራበት ጊዜ አሁን ነው" በማለት "ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጎን እንድትቆሙ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ" ሲሉ ጥሪያቸውን ለማኅበረሰቡ አባላት አቅርበዋል።

Selamawit Dawit. Source: SBS Amharic
ሌላው የክብረ በዓሉ ተጋባዥ ተናጋሪ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት የታሪክ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ የቅርስና ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው "የአድዋ ድል፤ መንስኤ፣ ሂደትና ውጤት" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን አቅርበዋል።
በዝክረ መታሰቢያው ላይ አገር አዳሙ፣ ሰፋኒት መንግሥቱና ዲያቆን ምኒልክ ዓለሙ ለአድዋ ታላቅነት መዘከሪያ ያቀረቧቸው የስንኝ ቋጠሮዎች ልዩ ዝግጅቱን ሞገስ አላብሷል።

Asst Prof Abebaw Ayalew. Source: SBS Amharic
የታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ በዝግጅቱ የውይይት መድረክ ከታዳሚዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶበታል።
በገለጣቸውም ወቅት "ይህ ታላቅ ለ125ኛ ጊዜ ሲከበርና ሲዘከር የጦርነቱን መንስኤዎች፣ የኢትዮጵያውያንን የዲፕሎማሲ ትግል፣ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለነፃነት የከፈሉትን መስዋዕትነት፣ የድሉን ትሩፋቶችና ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳዎች ለዘመናችን ትውልድ በሚገባ ማስገንዘብ በእጅጉ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
በማጠቃለያቸውም "በውጭ አገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገር ቤት ላሉ ኢትዮጵያውያን አርአያ እንድትሆኑ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ" ብለዋል።