የብሔራዊ አቦርጂናልና ደሴተኞች ቀን ኩነት ኮሚቴ (NAIDOC) በአውስትራሊያ የዘመን ቀመር ውስጥ ሁነኛ ሳምንት ነው። በተለይም በመላ አገሪቱ ላሉ ለበርካታ የነባር ዜጎች ማኅበረሰባት አስፈላጊ ነው። ነባር ዜጎች ባሕላቸውንና ውርሰ ቅርሳቸውን የሚያከብሩበት፣ ታሪካቸውን የሚዘክሩበት፣ ማኅበረሰባቸውን ሕብር የሚያላብሱበትና ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ጋርም የሚጋሩት ነው። የናይዶክ ሳምንት በየዓመቱ የሚከበረው ከመጀመሪያው እስከ ሁለተኛው ወርኃ ጁላይ እሑዶች ነው።
ሆኖም በኮቨድ-19 ሳቢያ የናይዶክ መማክርት ጉባኤ የማኅበረሰባቱንና አረጋውያኑን ከኮቨድ-19 ተጋላጭነት ለመታደግ የዓመታዊ ክብረ በዓሉን አዲስ ቀን አስታወቀ።
ከኖቬምበር 8 - 15 ይፋዊ የ2020 ክብረ በዓል ሳምንት ሆነ።
የናይዶክ ሳምንት ኩነቶች በመላ አገሪቱ የሚከበሩ ሲሆን በአብዛኛውም በሙዚቃ ዝግጅቶች፣ የሥነ ጥበብ ትዕይንቶች፣ ባሕላዊ ሆርሻዎች፣ በንግግሮችና የሕጻናት የጨዋታ እንቅስቃሴዎች የታጀበ ነው።
የናይዶክ መሪ ቃል
በየዓመቱ የናይዶክ ሳምንት የሚያተኩርበት የተለየ መሪ ቃል በናይዶክ ኮሚቴ ይመረጣል። ቀደም ሲል ተመርጠው የነበሩት መሪ ቃሎች የቃል ኪዳን ውል፣ መንፈሳዊ ቀዬዎች፣ ባሕላዊ ማንሰራራት መድን ነው፣ የድንኳን ኤምባሲ፣ ወደ አገር ቤት አምጧቸው፣ የይርካላ ባራክ ፊርማ ስብስብ፣ ቤተሰቦች፣ ነጭ አውስትራሊያ የጥቁር ታሪክ አላት፣ ከበሬታ፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና ሌሎች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ ጉዳዮችን የሚያንጸባርቁ ነበሩ።
ለመሪ ቃሉ የሚሆን ፖስተር የሚመረጠው አገር አቀፍ ውድድር ተካሂዶ ሲሆን የዚህ ዓመቱ መሪ ቃል "Always Was, Always Will Be" ሆኖ ተመርጧል።
የዚህ ዓመት ፖስተር ውድድር አሸናፊ በመሆን የተመረጠው የኑንጋርና ሳኢባይ ደሴቱ ሰው ታይሮውን ዋይጋና ነው።

'Shape of Land' by Tyrown Waigana is the winning design in the 2020 National NAIDOC poster design awards. Source: Supplied
የናይዶክ የአዳራሽ ግብዣና ሽልማቶች
ምንም እንኳ ኩነቱ አገር አቀፍ ቢሆንም በየዓመቱ የናይዶክ ሳምንት የአዳራሽ ግብዣና ሽልማቶች የሚከናወንበት አስተናጋጅ ከተማ በፈረቃ ይለዋወጣል። የዚህ ዓመት አስተናጋጅ ከተማም ኤሊስ ስፕሪንግስ ናት።
የናይዶክ ሽልማቶች ስድስት የሽልማት ዘርፎች አሉት፤
- የዕድሜ ልክ ስኬት ሽልማት
- የዓመቱ ሰው
- የዓመቱ ሴት አረጋዊት
- የዓመቱ ወንድ አረጋዊ
- ክብካቤ ለአገር ሽልማት
- የዓመቱ ወጣት
- የዓመቱ አርቲስት
- የዓመቱ ምሁር
- የዓመቱ ሰልጣኝ
የናይዶክ ታሪክ
የናይዶክ ቅድመ መነሻ በአብዛኛው በ1950ዎቹ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ሆኖም በበርካታ አንቂዎች ዘንድ ለዓመታዊው ኩነት ከበሬታ ተፅዕኖ አድራሹ የ1938ቱ የኃዘን ቀን ተደርጎ ሰፊ ድጋፍና ዕውቅና ይቸራል።
በ1940ና 1954 አሁን የአውስትራሊያ ቀን የነባር ዜጎች ቀን ተብሎ ከሚታወቀው እሑድ በፊት የኃዘን ቀን በሚል በተቃውሞ ታስቦ ነበር። ይሁንና በ1955 ከተቃውሞነቱ ይልቅ ወደ ክብረ በዓልነት በወርኃ ጁላይ የመጀመሪያው እሑድ ዞረ። በየዓመቱ ጃኑዋሪ 26 የሚከበረው የአውስትራሊያ ቀን ዛሬም ድረስ በበርካቶች ዘንድ የኃዘን ቀን፣ የወረራ ቀንና የመድን ቀን ተብሎ ይታሰባል።
በቀጣዩ ዓመት 1956 ወርኃ ጁላይ ሁለተኛው እሑድ ለነባር ዜጎች የመታሰቢያ ቀን ሆኖ ለናይዶክ (ያኔ ናዶክ) ሳምንትነት ቁልፍ ቀን ሆኖ እስካሁን ዘለቀ።
ናዶክ እስከ 1974 ድረስ ተዋቅሮ የነበረው በነባር ዜጎችና ነባር ዜጎች ባልሆኑ አውስትራሊያውያን ነበር። በመጀመሪያው ዓመት ኮሚቴ ይመራ የነበረው ሙሉ በሙሉ በነባር ዜጎች የነበረ ሲሆን ኩነቱም ለአንድ ሙሉ ሳምንት እንዲዘልቅ የተወሰነው ያኔ ነበር። የናይዶክ ሳምንት የሚለው ቃል መደበኛ ሆኖ ዕውቅና እስካገኘ 1989 ድረስም ይጠራ የነበረው ናዶክ በሚል ነበር።
ምንም እንኳ የናይዶክ ሳምንት የአሠርት ዓመታት ታሪክ ቢኖረውም በተወሰኑት ዘንድ እስካሁንም ድረስ የጋለ መከራከሪያ ነጥብ ሆኖ አለ። አንዳንድ የአካባቢ አስተዳደሮች ወይም የመንግሥት ኤጀንሲዎች የነባር ዜጎችን ሰንደቅ ዓላማ ወይም ለነባር ዜጎች አገር ዕውቅና አለመቸር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያልተለመደ ዜና አይደለም።
ባለፉት አሠርት ዓመታት ውስጥ የናይዶክ ሳምንት በአገር አቀፍ ቀንነት ዕውቅና እንዲቸረው ጥሪዎች ቢቀርቡም እስካሁን ዕውን አልሆነም።