የጆይ ኦቲዝም ማዕከል መስራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ዘሚ የኑስ፣ በኮቪድ 19 ቫይረስ ተይዘው በፅኑ ህሙማን መከታተያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን፣ “በፀሎት አስቡኝ” የሚል መልዕክትን ከቀናቶች በፊት አስተላልፈው ነበር።
አንደኛው ወንድ ልጃቸው የኦቲዝም ተጠቂ (የአዕምሮ እድገት እክል ያለበት ) መሆኑን ተከትሎ ስለችግሩ በጥልቀት እንዲረዱና ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች መፍትሔ ለማስገኘት በብዙ የደከሙ ሰው ነበሩ።
የኦቲዝም ታማሚ ልጃቸው ጆጆን ለማሳደግ የተጋፈጡትን ከባድ ሕይወት በአደባባይ በመናገርና ለዘመናት ከህመሙ ጋር ተያይዞ የነበረውን አጉል እምነትና ዝምታ በመስበር ለብዙ ወገኖች ደራሽ የሆኑት ፋና ወጊዋ ወ/ሮ ዘሚ የኑስ፣ በኮሮ ቫይረስ የተነሳ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የኒያ ፋውንዴሽን ጆይ የኦቲዝም ማዕከል በአሁኑ ወቅት ከ 80 በላይ የኦቲስቲክ ልጆችን ያቀፈ ሲሆን፣ ከተቋቋመ ከ19 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
ዛሬ ከቀኑ 6:00 ሰዓት ጀምሮ ሳር ቤት አካባቢ በሚገኘው ኒያ ፋውንዴሽን ዘሚ የክብር አሸኛኘት እንደሚደረግና ስርዓተ ቀብራቸው እንደሚፈፀም ተገልጿል።
[ ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ ]