ውልደትና ዕድገት
የሩት ይርጋዓለም ውልደት ቄራ ሠፈር - አዲስ አበባ ነው።
ለወላጆቿ አቶ ይርጋዓለም ወልደ ሥላሴ እና ወ/ሮ ወደርየለሽ ወንድማገኘሁ ሶስት ሴት ልጆች ውስጥ ማሳረጊያዋ እሷ ናት።
ለቀለም ትምህርት እንደበቃችም ሶሊያና፣ Sunny Side እና አደይ አበባ ትምህርት ቤቶች ገብታ ዕውቀትን ቀስማለች። ሲልም፤ የከፍተኛ ተቋም ትምህርቷን ወደ National Avation College ዘልቃ በገበያ አስተዳደር አጠናቅቃ ተመርቃለች።
ከትምህርት ቤት ወደ ሞዴል ሕይወት
የሩት የሞዴልነት ትንቢት የተነገረው ገና ለጋ ወጣት ሳለች ነው።
እነ ሩት ቤት ይመጡ በነበሩ ዘመድ አዝማድና ጎረቤቶች ዓይኖች የገባው ትክለ ሰውነቷና የተመዘዘ ቁመናዋ መስህባዊ ኃይል 'ከዓይን ያውጣሽ' አሰኝቶ መድረክ ላይ ግዘፍ ነስታ ሞገስ እንደምትላበስ ቀልባቸው ነገራቸው።
ተነበዩ።
አልተሳሳቱም።
'የተንባዮቹ' ቃል አየር ላይ በንኖ፤ ምድር ውስጥ ተቀብሮ አልቀረም።
በለጋይቱ ሩት አዕምሮና ልብ ውስጥ ግና አሻራውን ማሳደሩ እውነት ነው።
በእዚያም አላበቃ፤ ኢትዮጵያዊቷ ዓለም አቀፍ ልዕለ ሞዴል ሊያ ከበደ ታከለችበት።

Liya Kebede wearing Anne Klein Spring 2004 during Mercedes-Benz Fashion Week Spring 2004 - Anne Klein - Runway at Bryant Park in New York City, New York, United States. Credit: Dimitrios Kambouris/WireImage
ውስጣዊ የመድረክ ዘውድ የመድፋት ስሜቷ ግሎ ተቀጣጠለ።
ጣረች።
ሩቅ አሳቢ፤ ቅርብ አዳሪ ሳትሆን ቀረች።
የሞዴልነት ሙያዋ ሀገር ውስጥ በ Miss Addis Ababa ተሟሸ።
Miss Wubit Ethiopia, Miss International Ethiopia እያለ ቀጠለ።
ስምና ዕውቅና ተከተለ።
በርካታ ሽልማቶች በእጆችዋ ተጨበጡ።
መድረክ ላይ መግዘፍና ሞገስ መላበስን ተላመደችው።
በቅርቡም ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሔደው የ Miss World Ethiopia ውድድር ላይ ቀረበች።
በለስ ቀናት።
አሸነፈች!
ያም ለፊሊፒንስ 2025 ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር መጓጓዣ ሠረገላ ሆነላት።
ከአንድም ሁለት ሽልማቶችን አገኝች።
ትንቢቱ ሰመረ።
የሩት ሕልም ዕውን ሆነ።
ይህ የሆነው ግና በፅጌረዳ ስጋጃ ላይ ተረማምዳ አልነበረም።
ተግዳሮቶች ከውበት መድረክ በስተጀርባ
ሩት፤ በሀገረ ኢትዮጵያ የሞዴልነት ሙያ ከቅንጦትና አሉታዊ ነገሮች ጋር ተያይዞ መታየቱ ያሳስባታል።
ሰዎች፤ የሞዴልነት ሙያ እንደ ስፖርትና ሌሎች ኩነቶች ሁሉ አኩሪና ሀገር አስጠሪ መሆኑን እንዲገነዘቡላት ትሻለች።
የአስተሳሰብ ለውጥ ከሌለ ለሙያው ግዝፈትና ፈጣን ዕድገት ብርቱ ተግዳሮቶች እንደሚሆኑ ልብ ታሰኛለች።
የቁንጅና ውድድር በቁንጅና ብቻ የተወሰነ አይደለም። ማኅበረሰባትና ኢንዱስትሪዎችንም ለማገናኘት እንደ ድልድይ የሚጠቅም ነው። ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን የምናነሳባቸው፤ ያልተሰሙ ድምፆችን የምናስተጋባበት ነው"ልዕለ ሞዴል ሩት ይርጋዓለም
ስፖንሰር የሚሆኑ ኩባንያዎችንና አጋር ኤጄንሲዎችን የማግኘት ክብደትን በመንቀስም ተባባሪና ተጠቃሚም እንዲሆኑ ታበረታታለች።
እንዲያም ሆኖ ግና ተስፈኛ ናት።
የኢትዮጵያ የሞዴልነት ኢንዱስትሪ በትንሹም ቢሆን ወደፊት መራመድ ጀምሯል። ጥሩ ዕውቅናንም እያገኘን ነው።ልዕለ ሞዴል ሩት ይርጋዓለም
ትልሞች
- በሥነ ምግባር የታንፁ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ በቂ ግንዛቤዎችን የጨበጡ፤ አዳዲስ ወጣቶችን ለማፍራት ወጥናለች።Credit: YeabCreative
- የእቴጌ ጣይቱን ስያሜ የተላበሰ ማሰልጠኛ ማዕከል አቁማ፤ የሆርሻ መሰናዶዋን አጠናቅቃ ለጅማሮው ቀን ቆጠራ ላይ ትገኛለች።