ስደት
የቫሔ እናትና አባት ውልደትና ዕድገት በሀገረ ኢትዮጵያ ነው።
ቀድመው የኢትዮጵያን ምድር በስደት የረገጡትና አፈሯንም ዘግ ነው የጨበጡት ግና ከቱርክ
የአርመንያ ዘር ማጥፋት የተረፉቱ የወንድ አያቱ ናቸው።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን በቱርክ ስርወ መንግሥት መዳከም ቁጭት ተላብሶ፣ እሳት ለብሶ፤ እሳት ጎርሶ የገነነው "ቱርክ ለቱርካውያን" ዋልታ ረገጥ ብሔረተኝነት፤ ለአራት ክፍለ ዘመናት በስርወ መንግሥቱ ጭቆና ስር ለነበሩቱ አናሳ አርመንያውያን ጭፍጨፋ በር ከፈተ።
አሁንም ድረስ የሰለባዎቹ ቁጥር አወዛጋቢ ቢሆንም፤ ከ1915 እስከ 1923 ባሉቱ ዓመታት በቅደመ ጦርነት ከነበሩቱ ከ2 ሚሊየን አርመንያውያን ውስጥ ከ600,000 - 1.5 ሚሊየን አርመንያውያንን በኦቶማን መንግሥት መሪነት ለግድያ ዳረገ።
ከጅምላ ግድያውም ባሻገር ንብረታቸው ተገፍፎ ወደ ሶሪያ እንዲጋዙ ተደረገ።
ከተጋዢዎቹ አንዱ የቫሔ አያት (የአባቱ አባት) ነበሩ።
ዛሬ የዘር ሐረጋቸው ቫሔ እና እህቱ ድረስ ዘልቆ ይመዘዛል።

Vahe and his family roots. Credit: V.Talibian
እንደ እናትና አባቱ ሁሉ የቫሔም ዕትብት ተቆርጦ የተቀበረው በመዲናይቱ አዲስ አበባ፤ በሀገረ ኢትዮጵያ ነው።
ከአራት አሠርት ዓመት በፊት ከወላጆቹ አብራክ የተከፈለው ቫሔ ለፊደል ቆጠራ ሲደርስ የዘመናዊ ትምህርት ቀሰማን በአርመን ትምህርት ቤት ጀመረ።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ Sanford English Community School ገባ።
የክፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰም የነፃ ትምህርት ዕድል አገኘ።
ወደ ካናዳ ቫንኩቨር የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አመራ።
የመጀመሪያ ዲግሪውን በሥነ ሕይወት (Biology) አጠናቅቆ ተመረቀ።
ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
ከዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ወደ ሥራ ዓለም
አዲስ አበባ እንደተመለሰ የመጀመሪያ የጉልምስና ዘመን ሥራውን ዘመዶቹ ዘንድ ጀመረ።
ቫሔ ቫንኩቨር ሳለ ተማሪ ብቻ አልነበረም።
በላቲን አሜሪካ ዳንስ ዘይቤ ለዓለም አቀፍ መድረክ የበቃ ነበርና ዳንስ ማስተማርን በምሽት ሥራነት አክሎ ያዘ።
ሲልም፤ አጋጣሚ መርቶት ከመልካም ወዳጁ ድምፃዊት ቢጢቅ እምላዕሉ ጋር ባንድ መሠረቱ።
ከሌላኛው ሥራው ተሰናበተ።
የሙዚቃ ሰው ሆነ።
በቫሔ የሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ወራትና ዓመታት ተቆጠሩ።
አማርኛ፣ አርመንኛ እና እንግሊዚኛን ያካተተው የ2012 (እ.አ.አ) Mixology አልበሙ ወጣ።
ሲልም ነጠላ ሙሉ ዘፈኖቹ ተከታትለው ለሕዝብ ዓይንና ጆሮ ተዳረሱ።
ለምሽት ክለብ መደንከሪያነትም በቁ።
በእዚያም አላበቃ።
ቫሔ አርመን፣ ኢትዮጵያና የአፍሪካ አኅጉርን ወክሎ በ2015 የዩሮ-ቪዥን የዘፈን ውድድር ላይ ተገኘ።

Armenia's representatives in the 2015 Eurovision Song Contest. Including Vahe Talbian (Africa), five of the Armenian Genealogy super group participated from the diaspora community of different continents. Credit: EurovisionTV

Singers Zeritu Kebede (L), and Vahe Talbian (R). Credit: V.Talbian
የአርመንኛ ድንቅ ጥንታዊ የገበሬዎችን ዘፈን "Horovel" ከመሰንቆ ጋር አዋድዶ ኢትዮጵያዊና አርመንኛዊ ቃናን አላበሰ።
በሀገር ቤት አድናቆትን፤ በሀገረ አርመን 'አበጀህ! የተወጣለት ሸጋ ሥራ' ያሰኘ ክብርን አስገኘለት።
ከድምፃዊ፣ ሙዚቃ አቀናባሪና የዳንስ መምህር ቫሔ ቲልቢያን ጋር ያካሔድነው ቃለ ምልልስ በዚሁ አልተቋጨም።
*** በተከታዩ ክፍለ ዝግጅታችን ሰሞነኛ ከሆነው “ትዝታ” ዘጋቢ ፊልም እስከ አውስትራሊያ የ2025 ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር ዝግጅት ላይ ለመገኘት ልባዊ ፈቃደኝነቱን እስከገለጠበት ድረስ ያካተተውን ቃለ ምልልሱን ይዘን እንቀርባለን።