አንኳሮች
- ከካዛንቺስ እስከ ሜልበርን
- የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ጅማሮና ሂደት
- የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለአውስትራሊያውያን የማስተዋወቅ እንስቃሴዎችና ስኬቶች
ዳንኤል አጥላው፤ ከአዲስ አበባ ካዛንቺስ ተንስቶ የኪቦርዱን ወስዶ-መላሽ ድምፅ በሜልበርን መድረኮች ላይ ለማናኘት የበቃው በጽጌረዳ ፍራሽ ላይ ተረማምዶ አልነበረም።
ወላጆቹ እንደ ወቅቱ በርካታ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ከሙዚቃ ይልቅ ወደ ቀለም ትምህርቱ አተኩሮ 'አንቱ' የተሰኘ ልጅ እንዲወጣላቸው ይሹ ነበርና ከመነሻው ድጋፋቸው ነፍገውት ነበር።
ተስፋ ቆርጦ ከሙዚቃው ይልቅ ወደ ቀለሙ እንዲመለስ የአውቶቡስ መሳፈሪያ ሳንቲሞችን አልሰጥ ብለውታል። ዳንኤልም በእግሩ እየተጓዘ ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመላልሷል።
የሕይወት ነዳጁ የሙዚቃ ፍቅሩ ነበር። እናም በየቀኑ ከአንበሳ አውቶቡስ ጋር ባለ ጎማና እግረኛ ሆነው የሻጉራ እየተያዩ አያሌ ቀናት አስቆጠሩ።
ዳንኤል በሙዚቃ ትምህርቱ ተሰጥዖው፣ ትጋቱና ፈጥኖ ቀሳሚነቱ ተሰናስለው ውጤቱ ያማረ ለመሆን በቃ።
የቤተሰቡንም ልብ አሸንፎ ይሁንታቸውን ተቸረ።
ሲልም፤ በብሔራዊ ቲአትር መድረከኛነት ብቻም ሳይወሰን ለዘመናዊ ሙዚቃ ክፍል ኃላፊነትም በቃ።
የሕይወት ጉዞው እትብቱ በተቀበረባት መዲናይቱ አዲስ አበባ አልተወሰነም።
የሕይወት ኮከቡ ወደ አውስትራሊያ መርታ፤ በጢያራ ውቅያኖስን አሻግራ ለሜልበርን ነዋሪነት አበቃችው።
'ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ' እንዲባል፤ ባሕር ማዶኛ በመሆኑ የኪቦርዱ ልሳን አልተዘጋም።
ከቶውንም አገርኛ ቅላፄው የአገረ አውስትራሊያን ጆሮ ለመሳብ ቻለ።

ዳንኤል፤ ሿሚ ሳያስፈልገው በጥረቱ ራሱን በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ሙዚቃ 'አምባሳደር' አደረገ።
ከአውስትራሊያውያን የጥበብ ሰዎች ጋር ተስማምቶ ስመጥር ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ሰዎችን በሜልበርን ታላላቅ የሙዚቃ መድረኮች ላይ ግዘፍ አስነሳ።
ማኅሙድ አሕመድ፣ ዓሊ ቢራ፣ ዓለማየሁ እሸቴ እና እንዳልካቸው የኔይሁን (2PAC) በፈረቃ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለአውስትራሊያውያን እነሆኝ አሉ።

ሰሞኑንም ከኖቬምበር 9 - 14 / ከጥቅምት 30 - ኅዳር 5 በሶስት የተለያዩ የሜልበርን መድረኮች የምዕራባውያኑንና የኢትዮጵያን ረቂቅ ሙዚቃዎች አዋድዶ ለማቅረብ ስንዱ ሆኖ ያለው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋም ታካይ ሆኗል።














