ወላጆቻቸው በሞት የተለዩዋቸው ዕድሜያቸው ገና ፲ ዓመት ሳይሞላ ነበር። የወላጆቻቸውን ሙቀትና ፍቅር ባይጠግቡም፤ የወገን ፍቅር ግና አልተለያቸውም። ዐቅፎ-ደግፎ ፓሪስ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፊት ሆነው ለዓለም አለም አቀፍ ሞዴልነት እንዲበቁ አስችሏቸዋል።
የፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስም የ‘Miss Black Europe’ የቁንጅና ዘውድ ደፍታላቸዋለች። ያም ለመጀመሪያዋ ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያዊት ሞዴልነት ማማ አብቅቷቸዋል።

በሞዴልነቱ ዓለምም በአውሮፓና አሜሪካ የመጽሔት ሽፋኖችና የቴለቪዥን መስኮቶች ደምቀውበታል። የኢትዮጵያን ውበት የተላበሰ ገጽታም ለዓለም አንጸባርቀውበታል።
ከታላላቆቹ የማስዋቢያ የንግድ ኩባንያዎች ውስጥ ለ Dior, Cartier, እና Girlee ሞዴል ሆነው ሰርተዋል።

ፓሪስ የጧት እንጀራቸው ብትሆንም፤ ፍቅር ላይ ወድቀው፤ ጋብቻ በመመስረታቸው ሳቢያ ወደ አገረ አሜሪካ ሸክፈው ገቡ። ዳላስን የመኖሪያ ከተማቸው አደረጉ።
ዳላስም የሐረርወርቅን በስሟ “Dallas” በሚል ስያሜ በተሠራ ዝነኛ ተከታታይ የቴለቪዥን ድራማ ላይ የመጀመሪያዋ ጥቁር ተዋናይት አድርጋ አስተወነቻቸቸው።
የሞዴልነት ዓለም የተወሰኑ ሰዎች እንደሚያስቡት ጊዜያዊ ፍቅር የገነነበት ሳይሆን፤ በልባዊና ዘላቂ ፍቅር የተመላ ስለመሆኑ ራሳቸውንና ሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸውን ዋቤ ይነቅሳሉ።
የክፍል አንድ ትረካቸው የሚያጠነጥነውም በእኒህ ጉዳዮች ዙሪያ ነው።






