Thirty Five years on still going strong - Ethiopian Sports Federation in North America

Source: Supplied
በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን ከተመሰረተ ሰላሳ አምስት አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአሜሪካ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያንን በእግር ኳስ ፤ በባህል ልውውጥ፤ በንግድ፤ በማህበራዊ ግንኙነቶች ፤ በኪነጥበብና መዝናኛ ሲያስተሳስርና አንድ ሲያደርግ የቆየ ፌደሬሽን ነው። ፌደሬሽኑ የሚያዘጋጀው አመታዊ በአል ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያን በናፍቆት የሚጠብቁትና አብዛኞቹም በየአመቱ የማይቀሩብት ዋነኛ መገናኛ ሆኗል። የዛሬ የውይይት መድረክ ፕሮግራማችን የትኩረት አቅጣጫም በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን ዙሪያ ነው። የውይይታችን ተሳታፊዎች አቶ መሰለ ክፍሌ ከቦስተን የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን መስራች አባል ገንዘብ ያዥና የቦርድ አባል፤ አቶ ያሬድ ነጋሽ ከሳኖዜ የወቅቱ ሴክሬታሪ እና የቦርድ አባል፤ እንዲሁም አቶ ዳዊት አጎናፍር የፌዴሬሽኑ የቀድሞ ፕሬዝደንትና የቦርድ አባል ናቸው። የፌደሬሽኑን አመሰራረት፤ ለህብረተሰቡ እያበረከት ያለውን አስተዋጻኦ ፤ያሳለፈውን ተግዳሮቶችና የወደፊት ትልሞቹን በተመለከተ ተወያይተናል። ምንም እንኳ ፌዴሬሽኑ ባለፉት ሰላሳ አምስት አመታት ስሙን ሊያስጠሩ የሚችሉ እና ተለይቶ የሚታወቅበትን ልዩ ተግባራት ያደረገ ቢሆንም በአንጻሩም የአፍሪካንም ሆነ የአለም ዋንጫ ግጥሚያዎችን ወከለው የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ማፍራት አለመችሉ ለወደፊት በስፋት ሊሰራባቸው ያቀደው አብይ ተግባራት እንደሆነ ይስማማሉ። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ የታየው የለውጥ ሂደት ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር በጋራ የሚሰራበትን አዲስ ምእራፍ ከፍቷል። በአገር አቅፍ ደረጃ የኳስ ብቃት ያላቸውን የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚያፈራ አካዳሚን ለማቋቋም ማቀዱን ተወያዮቹ ነግረውናል። የሴቶች ውክልና በቦርድ አባልነትም ሆነ ተጫዋችነት ደረጃ አሁንም ድረስ ዝቅተኛ መሆኑን ሁሉም የተስማሙበት ሀሳብ በመሆኑ በቀጣይም ፌደሬሽኑ በትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት መሆኑን አረጋግጠዋል።
Share




