ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓም በወዳጅነት አደባባይ የማስጀመሪያ ስነ ስርዓት የተከናወነ ሲሆን ለአጠቃቀም ቀላልና ሁሉንም ህብረተሰብ የሚያሳትፍ የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያና የመገበያያ ዘዴ መሆኑ ተገልጿል።
በአህጉሩ የመጀመሪያ የሆነውና ከተመሰረተ አንድ ከሩብ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው ቴሌኮሙ በተለይም የቴሌኮም የገንዘብ ክፍያ ዘዴን እስካሁን አለመጀመሩ ሲያስወቅሰው ነበር።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ በመርኃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት "የቴሌ ብር መጀመርን ሳበስር በታላቅ ኩራት ነው። ከዚህ በኋላ " ያንቀላፋው ግዙፍ ካምፓኒ " ከሚለው ቅፅል ስም እኛም አገራችንም በ ቴሌ ብር መጀመር አብቅቷል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በበኩላቸው በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ሁለት የውጭ ድርጅቶች ፈቃድ የሚሰጣቸው መሆኑን ገልፀው በቴሌ ፋይናንስ ዘርፍ ግን አገልግሎት አይሰጡም ብለዋል። ለዚህም ምክንያቱ "ቅድሚያ ለብሔራዊ ጥቅም በመሰጠቱ ይህንን ኢትዮቴሌኮም የሚከውነው እንዲሆን ታስቧል። በዚህ ዛሬ ይፋ ባደረግነው ቴሌ ብር አማካኝነት ከውጭ ካምፓኒዎቹ ልናገኝ እንችል የነበረው ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ በአጭር ጊዜ እንደሚያካክስ እምነት አለኝ" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ለአንድ ዓመት ብቻ ነው ይህንን የሞባይል ብር አገልግሎት ስርዓት በብቸኝነት እንዲሰጥ ዕድል የተሰጠው ፡ ከዚያ በኋላ ለሌሎችም የሚፈቀድ በመሆኑ ለውድድር ራሱን እንዲያዘጋጅም አሳስበዋል።
ይህ የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ገንዘብ ማንቀሳቀሻ ቴሌ ብርን ለመጀመር ሲባል ከብሔራዊ ባንክ የ አንድ መቶ ቢሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል እንደተፈቀደለት ተገልጿል። አጠቃላይ የተፈቀደ ካፒታሉም 400 መቶ ቢሊየን ብር ነው።

PM Abiy Ahmed (L) Source: Ethio-Telecom
ጥሬ ገንዘብ መያዝን አስቀርቶ ዲጂታል እንደሚያደርግ የተነገረለት ቴሌ ብር ተጠቃሚ ደንበኞች ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ ገንዘብ እንዲልኩ፣ እንዲቀበሉና ግዢ እንዲፈፅሙ ያስችላል፣ ካሽ ወይም ቼክ ሳያስፈልጋቸው ዘርፈ ብዙ ክፍያዎችን እንዲፈፅሙ ያደርጋል። በሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የትስስር መንገዶች ላይ ገንዘብ መላላክን፣ ለዕቃና አገልግሎቶች ግዢ የሚደረጉ ክፍያዎችን መፈፀም እንደሚያስችል ተገልጿል።
በዚህ ዘመናዊ አገልግሎት በመጠቀም ሸቀጣ ሸቀጦችን ማግኘት ይችላሉ። አገልግሎቶችን ከሱፐርማርኬቶች ፣ከ ፋርማሲና ዳጅ ማደያ በቀላሉ መገበያየትም ያስችላል ተብሏል። በተጨማሪም የትምህርት ቤት፣ የውሃ እና ኤሌክትሪክ እንዲሁም ሌሎች መሰል ክፍያዎችን በስልክ መክፈል ያስችላል። ከዳያስፖራዎች ገንዘብ ለመቀበል፣ ገንዘብ ለመቆጠብ፣ ብድር ለማግኘት እና የባንክ አካውንት ከቴሌብር ጋራ እንዲተሳሰር የሚፈቅድ መሆኑም ሌላ ጠቀሜታው እንደሆነ ይፋ ሆኗል።
ይህንን አዲሱን የኢትዮ ቴሌኮም ቴሌ ብር የበዙ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ይፋ የማድረጊያ ስነ ስርዓት ከፍተኛ የፌደራል ባለስጣናትና የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም የተለያዩ እንግዶች ታድመውበታል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ ከአዲስ አባባ ]