በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዲ ሃቂ ካምፓስ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት የድሮን አየር ጥቃት መድረሱን የሕወሓት ቃል አቀባይና የሰላም ልዑክ ቡድን አባል አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ።
ቃል አቀባዩ የአየር ጥቃት መድረሱን የገለጡት በቲዊተር ገፃቸው ሲሆን፤ በሰውና በንብረት ላይ ስለደረሱ አደጋዎች ግና የሰጡት መረጃ የለም።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩልም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ላይ ደረሰ የተባለውን የቃል አቀባዩን ገለጣ አስመልክቶ የማስተባበያም ሆነ የማረጋገጫ ቃል አልተሰጠም።
ሕወሓት መስከረም 1, 2015 ላወጣው የሰላም ድርድር ጥያቄም በመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ5ኛው የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ከልዑካን ቡድን አባላቶቻቸው ጋር ናይሮቢ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመቱን አስታክከው ከኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር የጎንዮሽ ንግግር አካሂደዋል።
ተመራጭ ፕሬዚደንት ሩቶ በቀጣዩ አንድ ሰዓት ውስጥ ቃለ መሐላ የሚፈፅሙ ይሆናል።