የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የውጭ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ግጭቶች እየተካሔዱም ቢሆን የመንግሥት የሰላም ጥሪ አቋም ያልተለወጠ መሆኑንና ያም የሚያመለክተው የሰላም ኮሚቴው ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ፈቃደኝነት እንደሆነ አመላክተዋል።
አያይዘውም፤ የሰላም ንግግሩ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መካሔድ እንዳለበት መንግሥታቸው አቋም የያዘበት አንዱ አስባብ ምን እንደሁ ሲያስረዱ "ስለምን፤ በትግራይ ክልል ያሉ ኢትዮጵያውያን የሕወሓት ፖለቲካዊ ፍላጎት እሥረኞች ሆነው መቀጠል የለባቸውምና" ብለዋል።
ቃል አቀባይዋ "ምንም እንኳ በሕወሓት በኩል ለሰላም ሽራፊ ፍላጎት ባይኖርም፤ በመንግሥት በኩል የሰላም ጥሪው አሁንም ይቀጥላል" ሲሉ ገልጠዋል።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተዋናዮች ሕወሓት ለሰላም ንግግር እንዲቀመጥ በአደባባይ ሊጠይቁ እንደሚገባ የተናገሩት ቃል አቀባይ ቢልለኔ "የኢትዮጵያ መንግሥት በማንኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ሥፍራ በአፍሪካ ኅብረት መራሽ የሰላም ንግግር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ዳግም ያረጋግጣል" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም በአፅንዖት ገልጠዋል።
ተጨማሪ ያድምጡ

ደሴ ከተማ ላይ ሰዓት ዕላፊ ተጣለ
በሌላም በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ቃል አቀባይዋ ቢልለኔ ስዩም ጋዜጣዊ መግለጫ ቀደም ብሎ የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ፍላጎት እንደሌለው ጠቅሰው፤ መንግሥት ወደ ኤርትራ ጦር መላኩ አንዱ ማሳያ እንደሆነ በቲዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
በታካይነትም መንግሥት መቀሌ ላይ በሰነዘረው የድሮን ጥቃት ሶስት ቦምቦች መጣሉንና ከዒላማዎቹም መካከል አንዱ የመቀሌ ሆስፒታል እንደነበር ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ግና የሕወሓት ጦር አዛዥ ጄነራል ታደሰ ወረደ በፊናቸው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ሰላም የትግራይ ሕዝብ ማለፊያ ፍላጎት ነው" ሲሉ ለትግራይ ብዙኅን መገናኛ ተናግረዋል።
ሆኖም ጦራቸው የትግራይን ሕዝብ ደኅንነትና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲል አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንደሚወስድ አመላክተዋል።
አያይዘውም፤ የኢትዮጵያን መንግሥት ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ሊያመጣው የቻለው ጦራቸው በደቡባዊ ግንባር የወሰደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በማከልም፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ጋር በማበር በሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ ሽራሮ አቅጣጫ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመሰንዘር መተለሙን፣ እንዲሁም ከአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ጦር ጋር በመሆን ወደ ማዕከላዊ ትግራይ ለመዝለቅ በፊናርዋ በኩል ጥቃት መጀመሩን ገልጠዋል።
የግጭት አቅጣጫዎች
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ነሐሴ 25 ባወጣው መግለጫ ሕወሓት "በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ" ግጭት መክፈቱን አስታወቀ።
ሕወሓት በምሥራቅ አማራ ቆቦና አካባቢው የከፈተው ጦርነት እንዳሰበው ያልተሳካለት መሆኑን ያመላከተው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት "የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱበትን ጥቃቶች በጽናት እየተከላከለ፤ አሁንም ለሰላም አማራጮች የዘረጋቸውን እጆች ዛሬም ድረስ አላጠፈም" ሲል አክሏል።
ኦፌኮ
በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም በተቀሰቅሰው ጦርነትና ግሎ በመካሔድ ላይ ባለው የኦሮሚያ አካባቢ ግጭት ኃዘን የተሰማቸው መሆኑን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) መሪዎች አዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጠዋል።
አክለውም "ጦርነት የኢትዮጵያ ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ አይሆንም። ከጦርነቶቹ አገራችን ኢትዮጵያና ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ አንሆንም። እየተካሔዱ ላሉት ግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔ ለማስገኘት ሁላችንም ብርቱ ጥረቶችን ማድረግ ይገባናል" ሲሉ አሳስበዋል።
ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ላቅ ያሉ ጥረቶች እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።