የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች የትምህርት ክፍተትና የወደፊት እርምጃ

Australia Explained - Indigenous Education

First Nations-led education sees stronger engagement, outcomes and pathways for young people. Credit: courtneyk/Getty Images

ትምህርት ወደ መልካም ዕድል ማምሪያ ነው፤ ይሁንና ለረጅም ጊዜያት አውስትራሊያ ውስጥ የነባር ዜጎች ተማሪዎች ስኬት ላይ ለመድረስ ደንቃራዎች ገጥሟቸዋል። ተግዳሮቶች እንዳሉ አሉ፤ አዎንታዊ ለውጦች ግና እየተከሰቱ ነው። በእዚህ ክፍለ ዝግጅት የትኞቹ አካሔዶች እየሠሩ እንደሁ፣ ባሕላዊ ትምህርት ስላለው ረብ፣ የነባር ዜጎችና ምዕራባዊ ዕውቀቶች እንደምን ለሁሉም ተማሪዎች ትሩፋት ሊያስገኙ እንደሚችሉ፤ ከነባር ዜጎች የትምህርት ተጠባቢዎችና ተማሪዎች እናደምጣለን።


አንኳሮች
  • ነባር ዜጎች በሆኑና ባልሆኑቱ ተማሪዎች መካከል ያለው ክፍተት በዓመታት ጊዜያት ውስጥ ቢጠብብም፤ አሁን ድረስ እውን ሆኖ አለ።
  • ነባር ዜጎች - መር እና የባሕላዊ ትምህርት ተነሳሽነቶችን መደገፍ ለሁሉም ልጆች የተሻለ የትምህርት ውጤቶችን እንደሚያስገኙ የተወሰኑ ተጠባቢዎች ያምናሉ
  • አንዲት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ለቀለም ትምህርቷ ዳር መድረስ ውለታን ለመምህራን ድጋፍና በትምህርት ቤት አማካይነት ለባሕላዊ ግንኙነት መብቃት መቻል ትቸራለች
ከአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ በፊት፣ የነባር ዜጎች ባሕል ከምድር፣ ዕውቀትና ማኅበረሰብ ጋር የተቆራኘ የበለፀገ የትምህርት ሥርዓቶች የነበረው ነው። እኒህ ልማዶች ዛሬም ድረስ ጠቃሚ የሆኑ ግንዛቤዎችን እያስጨበጡ አሉ።

የትምህርት ውጤቶችን አስመልክቶ አሁንም ድረስ የፍትሐዊነት ጉድለት አለ። የነባር ዜጎች ተማሪዎች ትምህርት ገበታ ላይ የመገኘት ደረጃ ዝቅተኛ ነው፣ የንባብና ስሌት ደረጃዎችና የዩኒቨርሲቲ ውክልናዎች አይመጣጠኑም። ለእዚህም በታሪካዊና አሁንም በሂደት ላይ ያሉ እንደ መድልዖ፣ የባሕላዊ አካታችነት ማነስና የማኅበራዊ ምጣኔ ተጠቃሚ ለመሆን አለመብቃት አስባቦች ናቸው።

የትምህርት ክፍተትን አንስተን በምንነጋገርበት ወቅት የነባር ዜጎች ሕፃናት ምን ያህል መድልዖ እንደገጠማቸውም አንስቶ መወያየት እንደሚያሻ የባንጂ እና ኪጃ ሰው፤ የብሔራዊ አቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ትምህርት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሻሮን ዴቪስ ልብ ያሰኛሉ።  

“ገና ከመነሻው አንስቶ ድንጋጌዎችና ፖሊሲዎች ግልጥ ባለ ሁኔታ የነባር ዜጎች ልጆችን ከትምህርት ቤት እንዲርቁ አድርገዋል” ይላሉ።

ዴቪስ በቅርቡ በብሔራዊ ወጣት ዜጎች የትምህርት ቅንጅት የቀረበ ሪፖርት  ን አጣቅሰው ሲያመላክቱ፤

“በ20ኛው ክፍለ ዘመን አግላይ ፖሊሲዎች እንደተቀረፁ አመላክቷል… ነባር ዜጎች ያልሆኑቱ ቤተሰቦች እንደምን የነባር ዜጎች ልጆችን ከመማሪያ ክፍሎች ለቅቀው እንዲወጡ መጠየቅ እንደሚችሉ” በማለት ።
Sharon Davis.jpeg
Sharon Davis, CEO of NATSIEC Source: Supplied / Sharon Davis
በ 2008 የአውስትራሊያ መንግሥት፤ አውስትራሊያውያን ነባር ዜጎች ፀንተው የተቋቋሟቸውን ጉስቁልናዎች፤ በተለይም የሕፃናት በኃይል ከቤተሰቦቻቸው፣ ማኅበረሰባቸውና ቀዬአቸው ተነጠቀው መወሰድን አስመልክቶ ይፋዊ ይቅርታን አቅርቧል።

የይቅርታው አካል ሆኖም፤ ትምህርትን አክሎ ነባር ዜጎች በሆኑና ባልሆኑ አውስትራሊያውያን መካከል በዘርፈ ብዙ የሕይወት መስኮች ያሉትን ክፍተቶች ለማጥበብ ቃል ተገብቷል።

አሁን ቁልፍ ሆኖ ያለው ክፍተትን የማጥበብ ብሔራዊ ስምምነት ከነባር ዜጎችና ማኅበረሰባት ጋር የሚሠሩ መንግሥታት ማኅበረሰባት ኢ-ኩልነትን ለመወጣት ማኅበረሰብ-መር ዘርፍ ግንባታን የመሳሰሉትን ለመቅረፅ እንደምን የውዴታ ግዴታቸውን አብሮ በመሥራት መወጣት እንዳለባቸው የማሻሻያ ለውጥ እያካሔደ ነው።

ዴቪስ “የማኅበረሰባትን ፍላጎቶች ለሟሟላት የላቀ ዘላቂነት ያላቸው በአቦርጂናል ቁጥጥር ስር ያሉ ድርጅቶችመሆናቸውን እናውቃለን”  

“እናም፤ የእኛ ሰዎች ትምህርትን ሲመሩ፤ የተሻለ ተሳትፎ፣ መልካም ውጤትንና ለወጣቶቻችንም የፀኑ መንገዶችን እናይበታለን” ብለዋል።  

ባሕላዊ ትምህርት የወደፊት መራመጃ መንገድ ይሆናልን? 

በዎሎንጎግ ዩኒቨርሲቲ የነባር ዜጎች ማዕክል ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አንቶኒ ማክናይት የአዋባካል፣ ጋሚሮይ እና ዩኢን ሰው ናቸው።   

የነባር ዜጎችን የማስተማር ዘዴ በሥርዓተ ትምህርት፣ ፖሊሲና ትግበራ እንዲካተት ለበርካታ ዓመታት በማስተማርና በመመራመር አሳልፈዋል።

ዶ/ር ማክናይት ክፍተትን ማጥበብ ማለት ለነባር ዜጎች ምን ማለት እንደሁ ዳግም ቅርፅ ልናሲዘው ይገባል ባይ ናቸው።  

“ለእኔ፤ ሕብረ ቀለማቱ ካለን፤ የነባር ዜጎች ትምህርት፣ ምዕራባዊ ትምህርትና የነባር ዜጎች ተማሪ በመሃል ካሉን ሕብረ ቀለማቱ ይኖሩናል” ይላሉ።  

የክፍተትን ማጥበብ ተነሳሺነቶች ዓላማ፤ ተማሪዎችን ወደ ምዕራባውያኑ ትምህርት ማቅረብና ሕብራዊነቱን ማክሰም እንደሁ ልብ ይሰኛሉ።  

“እንዲያ ሲሆን፤ በሥርዓተ ትምህርታቸው ውስጥ መጠነ ሰፊ ክፍተት ይተዋል” 

“ለእኔ የነባር ዜጎች ሕፃናት ከመሃል፤ ከእዚያም ሁለቱ ዕውቀቶች መሃል ላይ ተጣማሪ ሲሆኑ ነው። ተማሪዎቻችን በሁለቱ ዕውቀቶች መካከል የመኖር ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል” ይላሉ። 
UOW INDIGENOUS LITERACY DAY
Dr McKnight has spent years teaching and researching how to embed Aboriginal pedagogy in curriculum, policy, and practice. Source: Supplied / MichaelDavidGray
ዶ/ር ማክናይት የምዕራቡን ትምህርትና የነባር ዜጎችን የዕውቀት ሥርዓቶች የሚያጣምር ትግበራን ተወዳጅ በማድረግ ሕፃናት ስለሚኖሩባት ምድርና እንደምንስ ክብካቤን ሊቸሯት እንደሚገባ መማር አለባቸው የሚል አመኔታ አላቸው።  

“የነባር ዜጎች ልጆች ብቻ ሳይሆኑ፤ ይህችን ሥፍራ መከባከብ ያለባቸው የነባር ዜጎች ልጆች ያልሆኑትም ጭምር መሆን አለባቸው… ያ ቁሳዊ አካል ነው የምንሻውን ሁሉ የሚቸረን፣ ሁላንችንም የምንራመደው አንዲት ምድር ላይ ነው፣ የምንጠጣው ተመሳሳይ ውኃ፣ የምተነፍሰውም ተመሳሳይ አየር ነው” ሲሉ አተያያቸውን አጋርተዋል።  

የእኩል ትምህርት ውጤቶች—ፍኖተ ካርታ በሂደት ላይ  

ክፍተትን የማጥበብ ብሔራዊ ስምምነት ወቅታዊ ዳታ መሠረት በነባር ዜጎችና ነባር ዜጎች ባልሆኑቱ መካከል ትምህርትን አስመልክቶ ያለው ክፍተት በዓመታት ውስጥ ቢጠብም አሁንም ድረስ ክፍተት አለ።  

ዴቪስ “ለምሳሌ ያህል፤ በአሁኑ ወቅት የነባር ዜጎች በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታ 59 በመቶ ላይ ያለ ሲሆን፤ ነባር ዜጎች ያልሆኑ ተማሪዎች ቆይታ 85 በመቶ ላይ ይገኛል”  

“እናም በውጤቶች ላይ እንዲያ ያሉ ክፍተቶችን ስንመለከት፤ ያ ሥርዓተ ትምህርቱ ምን ያህል የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ተማሪዎችን፣ ወጣቶችን፣ የግል ትምህርት ቀሳሚዎች በረባ ሁኔታ ያገለገለ ሳይሆን የተገላቢጦሽ የመሆኑ ነፀብራቅ ነው” በማለት ያስገነዝባሉ።  
Retori Lane.png
Retori Lane (L) with her mother, Jenadel Lane. Source: Supplied / Retori Lane
ባለፈው ዓመት፤ የጋሚላሮይዋ ወጣት ሴት ሬቶሪ ሌን፤ ከዳቦ ከፍተኛ ኮሌጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃለች።  

ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ 12ኛ ክፍል ካጠናቀቁ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የነባር ዜጎች ተማሪዎች ውስጥ አንዷ ናት።

ወ/ት ሌን፤ ድጋፍ የታከለበት የመማር ሂደቱ ሁኔታ ፍሬ እንዳስገኘላት ትናገራለች።

ድጋፍ ሰጪዎቿ የትምህርት ቤት ባልደረቦች፣ የነባር ዜጎች መምህራንንና በመላ ኒው ሳውዝ ዌይልስ እና ሰሜናዊ ግዛትፕሮግራሞችን በማካሔድ የነባር ዜጎች ተማሪዎች ከባሕላቸው ጋር ትስስሮሽ እንዲኖራቸውና በትምህርት ገበታቸው ላይም ስኬታማ እንዲሆኑ አጋዥ የሆነው የአውስትራሊያ አቦርጂናል ስፖርት ኮርፖሬሽንን (አአስኮ) ድርጅትን ያካተተ ነው።

“በተለይም ከትምህርት ቤት ባልደረቦች ትልቅ ድጋፍን አግኝቻለሁ”
“እንዲሁም ከአአስኮ ሠራተኞች። መጥተው ወደ ጥናት ይወስዱናል፤ እስከ ዘለቄታው ያግዙናል። እንዲሁም፤ መምህራኑም በማናቸውም ረገድ ሊያግዙን እዚያ አሉ” ብላለች።

የሬቶሪ እናት ጃናዴል፤ ልጃቸው የተመረቀችበትና ከቤተሰባቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ የመጀመሪያዋ የሆነችው መማሪያ የነበረው የዳቦ ከፍተኛ ኮሌጅ ምክትል ርዕሰ መምህርት ናቸው ።  

በልክ የተመጠነ ድጋፍና ባሕላዊ ጥንቃቄን የተላበሰ ሁኔታ ሁሉንም ተማሪዎች ምርጥ ትምህርት ቀሳሚዎች እንደሚያደርግ ያመላክታሉ።  

“እኔ የአቦርጂናል ተማሪዎች 12ኛ ክፍልን ማጠናቀቅን አስመልክቶ በስሜት የተመላሁ ነኝ፤ ስለምን፤ ትንሽዬ ድርሻዬን ለሰዎቼ አበረክትበታለሁና። ለእዚያም ነው አስተማሪ የሆንኩት"   

“ሲልም፤ ከትምህርት ቤት በኋላ ላለ ሕይወታቸው አያሌ በሮችን እንደሚከፍትላቸው ተስፋ አደርጋለሁ” 

ሪቶሪ በነባር ዜጎች ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪዋ ለማግኘት ተመዝግባለች።

“በትውልዶች ውስጥ ባክነው የቀሩ የነባር ዜጎች ልጆችን ለማስተማር ራሴን ለማብቃት እሞክራለሁ። እናም፤ ባሕል አንሠራርቶ ሕይወት እንዲኖረው የማድረግ ሂደት አጋዥ አካልም ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ”  ስትል ውጥኗን አመላክታለች።

ስለ አዲሱ የአውስትራሊያ ሕይወትዎ ተጨማሪ ጠቃሚ መረጃና ፍንጮች ለማግኘት የአውስትራሊያ ስትገለጥ ፖድካስትን ይከተሉ አሊያም ደንበኛ ይሁኑ።   


ጥያቄዎች ወይም ርዕሰ ሃሳቦች ካለዎት? 
australiaexplained@sbs.com.au ኢሜይል ይላኩልን።

Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service