በስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሲቪል ማህበራትን ተሳታፊነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል 176 ማህበራት በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ሕብረት ለምርጫ የተሰኘ ድርጅትን መስርተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
ኅብረቱ ገለልተኛ እና ከፓርቲ ፖለቲካ ነፃ የሆነ ድርጅት ሲሆን ምርጫው አካታችና ግልፅነት የተሞላበት መሆኑን ለማረጋገጥ የሚሰራ ድርጅት ነው። ዛሬ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በሰኔ 14፣ 2013 በተካሄደው ምርጫ ላይ ህብረቱ በሰበሰበው መረጃ ላይ የተመሰረተ ቅድመ ግኝትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው በምርጫ ቀን ለረጅም ሰዓታት በሰልፍ ላይ በመቆየት ድምፃቸውን የሰጡ ዜጎችን፣ የምርጫ ቦርድን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎቻቸውን፣ የፀጥታ ሀይሎችን እንዲሁም በምርጫው ሂደት ላይ የተሳተፉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አድንቋል።
ኅብረቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ባካሄደባቸው ሰባት ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች፤ ከ3000 በላይ የሚሆኑ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን እንዳሰለጠነ የገለፀው ህብረቱ ቋሚ ታዛቢዎች የታዘቧቸውን መረጃዎች በአዲስ አበባ ወደሚገኘው የሕብረቱ የመረጃ ማዕከል በጽሁፍ መልዕክት የላኩ ሲሆን፤ ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች ደግሞ በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ ከምርጫ ጋር የተገናኙ ሂደቶችን እንዲሁም የድምፅ አሰጣጥ ሂደትን ከአንድ ምርጫ ጣቢያ ወደሌላ በመዘዋወር መታዘባቸውን አብራርቷል።
ታዛቢዎቹ የምርጫ ጣቢያዎችን ዝግጅት፣ አከፋፈት፣ የድምፅ አሰጣጥ እና ቆጠራ እንዲሁም የድምፅ ቆጠራ ውጤት በሚለጠፍበት ጊዜ የነበሩ ሁኔታዎችን እንደታዘቡ አመልክቷል። ከቋሚ ታዛቢዎች በተጨማሪ ከ150 በላይ ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን በማሰማራት በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የተከሰቱ አሳሳቢ ኩነቶችን ለመረጃ ማዕከሉ እንዲልኩ እንዳስደረገና ከዚህም በመነሳት የህብረቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ከምርጫ አሠራር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የምርጫ ምልከታ ግኝቶች ዋና ዋና ነጥቦች ዛሬ ይፋ አድርጓል።