የርቀት ትምህርት ተግዳሮቶችና ተሞክሮዎች በኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ተማሪዎችና ወላጆች ዘንድ

Community

Adamu Tefera (L), A music school teacher and her pupil seen on a laptop screen as the teacher holds a one-to-one online flute lesson (R). Source: A.Tefera and AAP

አቶ አዳሙ ተፈራ በመድብለ ባሕላዊ የወጣቶች ትምህርት መኮንን፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ የርቀት ትምህርት በልጆችና በወላጆች ላይ ስላሳደራቸው ተፅዕኖ ይናገራሉ።


የቤት ውስጥ ትምህርት ተግዳሮትና የገበየነው  ትምህርት

ኮቪድ ባለፉት ሁለት አመታት ኑሮን ፈታኝ አድርጎት ነበር። ከዚያም ውስጥ አንዱ የልጆች ከቤት መማር ነው። በዚሁ ርእስ ዙሪያ በዚሁ በSBS ፕሮግራም ላይ የተለያየ መልክእት አስተላልፌ ነበር። ይህ የማጠቃለያው ክፍል ነው።

እርግጥ ነው የልጆች ከቤት ትምህርታቸውን መማር አዲስ ነገር አይደለም። በተለያዩ አገሮች ውስጥ ለምሳሌ እንደእንግሊዝ ባሉ አገሮች ውስጥ ወላጆች የትምህርት ቤቱን የትምህርት አያያዝ በመጥላት፤ በልጆች ላይ በሚደርስ የአካልም ሆነ የስነልቦና ጥቃት ጋር በተያያዘ ልጆቻቸውን ከቤት ማስተማር የተለመደ ነው።

ከኮቪድ ጋር የተያያዘው የቤት ውስጥ ትምህርት ግን ከዚህ የተለየ ነው። የሆነው ድንገት ነው፤ ማቀድና መዘጋጀት የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም። ወላጆችም መምህራንም ለዚህ ሁኔታ ዝግጁ አልነበሩም።

ወላጆች ይህንን ሁኔታ እንዴት እንዳሳለፉት ምን እንደገጠማቸው? ምን እንዳደረጉ? ከሁኔታው ምን እንደተማሩ ወዘተ ጉዳይ ዙሪያ ከአስር ኢትዮጵያውያን ወላጆች ጋር ተወያይቼ ነበር። በዚህ አጋጣሚ ለጊዚያቸውና ለሰጡኝ ግልጽ መረጃ ሳላመሰግን አላልፍም። እነዚህ ተሳታፊ ወላጆች በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጆች ያላቸው እና ልጆቻቸውን በግልን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ናቸው።

ወላጆቹ ያነሷቸው ፍሬ ነገሮች ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ነበሩ፦

-       የልጆች የአእምሮ ጤናና አጠቃላይ ደህንነት

-       የተወሰኑ ወላጆች የልጆቻቸውን ትምህርት በማገዝ ረገድ የነበራቸው ውሱን ሚና

-       ወላጆች ሥራን ፣የልጆች ትምህርትንና ሌሎች የቤተሰብ ተግባርን በማቀናጀት ረገድ የገጠማቸው ጫና

-       የትምህርት ቤቶች ለልጆች በተናጥል ድጋፍ የመስጠት ውሱንነት

-       ልጆች በየእለቱ ማካናወን በሚገባቸው ተግባር ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አለማስቻል

-       የኢንተርኔት ደህንነት  ፤የልጆችን ሶሻል ሚዲያና ኢንተርኔት አጠቃቀማቸውን መቆጣጠር አለመቻል

-       ልጅች ከትምህርታቸው ጋር በተያያዘ የገጠማቸውን ጫናና ጭንቀት ለማካካስ እንዲቻል የመዝናኛና የማገዣ ፕሮግራም መፍጠር አለማቻል

-       እና በመጨረሻም ከዚህ ሁኔታ ምን ትምህርት አገኙ? በሚለው ዙሪያ ነበር።

ማንኛውም ወላጅ የተማረ ያልተማረ ሳይል የልጁን የትምህርት ሁኔታ ለማገዝ አቅም አለው። በተለያየ የአውስትራሊያ ጥናት መሰረት ወላጆቻቸው በትምህርታቸው ላይ ፍላጎት የሚያሳዬቸው፤ለስኬታቸው የሚጓጓላቸውና በቻሉት መጠን የሚደግፏቸው ልጆች ትምህርት ቤት በሚያሳዩት መልካም ባህሪ፤ሁሌም ት/ቤት በመገኘትና የቤት ሥራቸውን በማጠናቀቅ ስኬታማ ናቸው።

ባደረግነው ውይይት ላይ ወላጆች የሚከተለውን ሃሳብ አጋርተውኝ ነበር።

-       ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በተካሄደው የቤት ውስጥ ትምህርት የበለጠ ተግዳሮት የገጠማቸው ወላጆች ፤ልጆቻቸው በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የሚማሩት ናቸው። ትምህርቱን ፤ሥነስርአቱንና ሌሎችንም አሳልጦ መምራት አዳጋች እንደነበረ ተናግረዋል። ከተሳታፊዎቹ ወላጆች ውስጥ አንዱ ሲናገር« በዚህ በኮቪድ ውስጥ የእኔ የወላጅነት አቅም እጅግ የተፈተነበት ሰአት ነው።» ብሏል። ይኸው አባት በመቀጠልም «የእርቀት ትምህርት በፍጹም ለልጆች የሚሆን ነገር አይደለም።» ብሏል።

-       አብዛኞቹ የውይይቱ ተሳታፊ ወላጆች የተስማሙበት አንዱ ጉዳይ«ወደ ትምህርት ጉዳይ ሲመጣ ልጆችን ሥርአት ሊያሲዙ የሚችሉት በተለይም ትምህርት ቤቶች ከተማሪዎች የሚጠብቁባቸውን ሥራ ማከናወን እንዲችሉ የሚያደርጉት መምህራን ናቸው።

አንድ ወላጅ ሲናገር «የእኔ ተግዳሮት ዋናው ልጄ እንደጓደኛ አባት ነው የምታየኝ። በፍጹም በመምህርነት ቦታ ጠብቃኝ አታውቅም። ያ ሥራዬን አስቸጋሪ አድርጎታል።» ብሏል።

-       ሌላው ወላጅም ሲናገር «የቤት ውስጥ ትምህርት አንዱና ዋናው ችግር የመምህራን እራሳቸው ዝግጁ አለመሆን ነው።» ብሏል።

ሌላው ያነሱት ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ልጆችን ለማዝናናት የተደረገው ጥረት ነው።

ከቤት መዋል ሰፊ ጊዜ ስለሰጠ፤ ወላጆችም ሆነ ልጆች እንደልብ  እንዲገናኙ አብረው እንዲውሉ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ስለሆነም አንዳንድ አዳዲስ ሁኔታዎች ለመሞከር እድል ፈጥሯል። በተለያየ የኪነጥበብ፣ ስፓርታዊና ምግብ ማብሰል መርሃግብር ላይ ከማተኮራቸውም ሌላ በሙዚቃና ዳንስም እንዲሁ ልጆቻቸው እንዲያተኩሩ ማድረጋቸውን ወላጆች አንስተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንድ የሶስት ልጆች አባት ሲናገር«በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ልጆቼን ለማበረታታት፤ለማንቃትና ለማገዝ የጠረፔዛ ጫዋታ እውቀቴ ረድቶኛል።» ብሏል።

ሌላው ወላጅም ሲናገር «ልጆቻችን ከቤት ሲማሩ ዋናው ትኩረታችን የነበረው ትምህርት ማሳካታቸው ላይ ሳይሆን። የአእምሮና ሁለገብ ደህንነታቸው ላይ ማተኮር ነበር። ከቤት መማር ከትምህርት ቤት ከመማር ጋር ሲነጻጸር ምንም ማለት ስላይደለ ያለፈው ሁለት አመት በከንቱ ባክኗል።» ብሏል።

ይኸው ወላጅ ሲናገር «የልጆቻችንን ጭንቀትና ድብርት ለመቋቋም እንዲረዳን የእግር ጉዞ እናደርግ ነበር።እናታቸው ደግሞ ልዩ የሲኒማ ክፍል በማዘጋጀትና ፍራሽ በመዘርጋት የፓፕኮርን ፊልም ምሽት ታዘጋጅላቸው ነበር።»ብሏል።

የግል ትምህርት ቤትና የሕዝብ ት/ም ቤትን በተመለከተ

በኮቪድ ወቅት ልጆቿን በግልና ሕዝብ ት/ቤት የማስገባት  አጋጣሚ የነበራት እንድ እናት ስትናገር። «ልጆቼ በሕዝብ ት/ቤት በነበሩበት ወቅት ትምህርት ቤቱ ያለማሰለስ ቀጥተኛ ድጋፍ ይሰጣቸው ነበር። የእኔን እገዛ ያን ያህል አላስፈለጋቸውም ነበር። ወደ ግል ት/ቤት ሲዞሩ ግን እኔ ላይ ሥራ በዝቶብኝ ነበር። ትምህርታቸው በቀጥታ ማገዝ ነበረብኝ። ልጆቼ በግል ት/ቤት ሲማሩ ትምህርት ቤቱ የጽሁፍና አንዳንዴም የቪዲዬ መመሪያ ይልክላቸው ነበር። አንደኛ ደረጃ ያሉት ብዙም ስለማይገባቸው እኔው ማገዝ ነበረብኝ።እርግጥ ነው የግል ት/ቤቱ በሳምንት አንድጊዜ የማህበራዊ መገናኛና መዝናኛ ፕሮግራም ያዘጋጅ ነበር።» ብላለች።

ሌላው ልጆቹን የግል ትምህርት ቤት ያስተምር የነበረ ወላጅ ደግም «ልጆቼን ትምህርት ቤቱ ብዙም አያግዛቸውም። ለምንስ ያን ያህል ገንዘብ እንደምንከፍል አልገባኝም?» ሲሉ ጠይቋል»

እርግጥ ነው የወላጆች ገጠመኝና ልምምድ የተለያየ ነው።አብዛኞቹ ወላጆች የተለያየ ተግዳሮት እንደገጠማቸው ሲገልጡ ጥቂት ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው በግልም ሆነ በሕዝብ ትምህርት ቤት የተሰማሩት ሁኔታው የሰከነና ከችግር የጸዳ እንደነበረ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንድ ወላጅ ሲናገር«ሶስት ልጆች አሉኝ። አንዱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሲሆን ሁለቱ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። እኔ እድለኛ ነኝ ማለት እችላለሁ።ልጆቼ የሚያደርጉትን በቅጡ የሚያውቁና እጅግ ሥርአት ያላቸው ናቸው።ስለሆነም በቤት የሚያካሂዱትን ትምህርት በጥሩ ሁኔታ እያሳኩ ነው።»ብሏል።

አንድ ሁለት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ያሉት ወላጅ ደግሞ ከዚሁ ከቤት ትምህርት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ጭንቀትና ጫና የልጆች ባህሪ እንደተለወጠ ተናግሯል። እንዲህም ብሏል «ልጄ ላይ የባህሪ ለውጥ አይቼበታለሁ። ግልፍተኛ እየሆነ ከመምጣቱም ሌላ ለትምህርቱ  ጭራሽ ትኩረት አይሰጥም። ባንድ ኮምፒዩቶር ላይ ትምህርቱን እየተከታተለ በሌላ ላፕቶፕ ላይ ደግሞ የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ይከታተል ነበር።»ብሏል።

በመጨረሻም አንዳንድ ወላጆች ከቋንቋውና የትምህርቱን ሥርአት ካለመረዳት ጋር በተያያዘ ልጆቻቸውን ለማገዝ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።«ልጄ ከትምህርት ቤቷ የሚደርሳትን መመሪያን ሥራ ተረድቼ ላግዛት አልቻልኩም። ሥራዋን በወግ ለማደራጀት አልረዳሃትም።  በዚህም ትበሳጭ ነበር።ይህ ሁኔታ ተግባቦታችንን አሻክሮታል።» ብሏል።

በጥቅሉ ወላጆች የተለያየ ተግዳሮት ቢገጥማቸውም ከሁኔታው መልካም ነገር እንደገበዩም የተናገሩ ወላጆች ነበሩ። የልጆቻቸውን የትምህርት ሁኔታ በሚከታተሉበት ወቅት የማስተማር ሄደቱን በተወሰነ ደረጃ መረዳት እንደቻሉ፤ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መውሰድና መመለስ ስለሌለ ብዙ ጊዜ ማዳን እንደቻሉና የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል።

ልጆች ከቤት ከመማራቸው ጋር በተያያዘ ስለቀሰሙት ትምህርትም አንዳንድ ወላጆች አንስተው ነበር። አንድ ወላጅ «እኔና ባለቤቴ ወደፊት ልጆቻችን የቀለም ትምህርት ላይ ብቻ ሳይወሰኑ በተውኔት፤ሙዚቃ ስፓርትና የመሳሉት ላይ እንዲያተኩሩም እናበረታታቸዋለን። ያ ሲሆን የኮቪድ አይነት ሁኔታ ሲጋጥም ጽናትና ሁኔታን የመቋቋም አቅማቸው ይጎለብታል። ሁኔታዎችን ለራሳቸው በሚመች መንገድ ለመግራት ያስችላቸዋል።»ብሏል።

- አዳሙ ተፈራ


Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service