ሰላም!
የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት ዕንቁጣጣሽ ለሚያከብሩ ሁሉ የሞቀ ሰላምታዬን አቀርባለሁ።
የአውስትራሊያ ንቁና በማደግ ላይ ያለው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላት የበለፀገ ታሪክ፣ ቋንቋና ባሕልን ወደ አገራችን አምጥተዋል።
በምድር ላይ በእጅጉ ስኬታማ መድብለ ባሕላዊት በሆነችው አገር የዘንድሮውን የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የምናከብረውም እኒህ ስጦታዎች ለአውስትራሊያ ያበረከቱትን አስተዋፅዖን ይዘን ነው።
ባለፈው ዓመት፣ ኮቪድ -19 በመላ ሕይወታችን ላይ ጥላውን አጥልቶብናል። በእኒህ አዋኪ ጊዜያትም አያሌ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ብርቱ የእጦትና መለየት ስቃይ እንደተሰማቸው አውቃለሁ።
በጋራ በመሆንም አንዳችሁ አንዳችሁን በፍቅርና በቸርነት ረድታችኋል፤ ደግፋችኋል።
በታላቅ ፈተናና ለውጥ ፊት ጥንካሬያችን እኒህ የወዳጅነትና የቤተሰብ ትስስሮሾች ናቸው።
አውስትራሊያ ውስጥ ዕንቁጣጣሽ የሚውለው የፀደይ አዲስ ሕይወት ክስተት በሚጀምርበት ፀሐያማና ብሩኅ ቀናት ነው። ብርቱ ተግዳሮት ሁላችንም ላይ ተደቅኖብን ባለበት ወቅት፤ የዕንቁጣጣሽ ክብረ በዓል አዲሱ የፀደይ ወቅት የሚያመጣውን የተስፋ መንፈስ በተመሳሳዩ ይጋራል።
ይህ ተስፋም ዳግም በጋራ የምንሰባሰብበትን ጊዜ አማትረን እንድንመለከት ያደርገናል።
ምንም እንኳ የእናንት ክብረ በዓል ዳግም ቢስተጓጎልም፤ የእኔ ተስፋ አዲሱ ዓመት የሰላምና የአንድነት ዘመን እንደሚሆን ነው።
መልካም አዲስ ዓመት!
የተከበሩ ስኮት ሞሪሰን የምክር ቤት አባል
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር
ሴፕቴምበር 2021