SKIP TO MAIN CONTENT

በአውስትራሊያ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ዋጋቸውን ያስመልሳሉን? | የነዳጅ ጉዳይ

Australia Explained – Fuel in Focus
አሽከርካሪዎች በዓመት 70 በመቶ ያህል የነዳጅና 40 በመቶ ያህል የመኪና ጥገና ወጪዎችን ይቆጥባሉ የሚል አመኔታ አለ። Source: Moment RF / Tashdique Mehtaj Ahmed/Getty Images

በአውስትራሊያ የነዳጅ ዋጋ አሁንም መረጋጋትን አላሳየም። በርካታ ሰዎችም የጉዞ ወጪያቸውን የሚቀንሱበትን አማራጭ እያፈላለጉ ነው። የኤሌክትሪክ መኪናዎች (EVs) በአውስትራሊያ መንገዶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዝተው ይታያሉ። ወደ ኤሌክትሪክ መኪና ለመዞር ካሰቡ፤ ሊያውቁ የሚገባዎትን እነሆን።


Published

Updated

By Zoe Thomaidou

Presented by Melissa Compagnoni, Kassahun Negewo

Source: SBS



Skip to podcast episode content

በአውስትራሊያ የነዳጅ ዋጋ አሁንም መረጋጋትን አላሳየም። በርካታ ሰዎችም የጉዞ ወጪያቸውን የሚቀንሱበትን አማራጭ እያፈላለጉ ነው። የኤሌክትሪክ መኪናዎች (EVs) በአውስትራሊያ መንገዶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዝተው ይታያሉ። ወደ ኤሌክትሪክ መኪና ለመዞር ካሰቡ፤ ሊያውቁ የሚገባዎትን እነሆን።


የኢንዱስትሪ ዳታ እንደሚያሳየው በወርሃ ኤፕሪል 2026 በአውስትራሊያ ከተሸጡት አዳዲስ ተሽከርካሪዎች መካከል ከስድስቱ አንዱ ገደማ የኤሌክትሪክ መኪና ነበር። ሽያጩ እየጨመረ ቢሆንም፣ እነዚህ መኪናዎች በዋጋ አቅም፣ በባትሪ መሙያ መሠረተ ልማት እና ከአውስትራሊያ የአነዳድ ሁኔታዎች ጋር ባላቸው ተስማሚነት ዙሪያ ጥያቄዎች አሁንም ይነሳሉ።

በአውስትራሊያ የኤሌክትሪክ መኪና ለመግዛት ምን ያህል ወጪን ይጠይቃል?

በአጠቃላይ ሲታይ፣ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ከቤንዚን ወይም ከነዳጅ መኪናዎች የበለጠ የመጀመሪያ ግዢ ወጪ ይጠይቃሉ። ሆኖም እየተበራከቱ በመጡ የገበያ ምርጫዎች እና እየጨመረ በመጣው ፍላጎት ምክንያት የዋጋ ቅናሽ እየታየ ነው።

በስዊንበርን ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ትራንስፖርትና ዘላቂነት ፕሮፌሰር ሑሴን ዲያ እንደሚሉት፣ አሁን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኙ ሞዴሎች በበርካታ ቁጥር ለገበያ ቀርበዋል።

“ከሦስት ወይም ከአራት ዓመታት በፊት ከ50,000 ዶላር በታች የሆነ ኤሌክትሪክ መኪና ማግኘት ከባድ ነበር። አሁን ግን በ30,000 ዶላር አካባቢ የሚገኙ መኪናዎች አሉ፤ በመንግሥት የሚሰጡ ማበረታቻዎች ሲጨመሩበት ደግሞ ከዚያም በርካሽ ዋጋ ሊገዙ ይችላሉ።” ብለዋል።

የሚኖሩበትን ክፍለ ሃገር ወይም ግዛት ማበረታቻዎች በመመልከትም ለተለያዩ የመንግሥት ድጋፎችና ማበረታቻዎች ብቁ ሊሆኑ ይችላሉ።

እንዲሁም ደመወዛቸውን በ"Salary Packaging" ስርዓት የሚያስተዳድሩ ሠራተኞች፣ በ"Novated Lease" አማካይነት በፍሪንጅ ቤኔፊትስ ታክስ (FBT) ላይ ቅናሽ ሊያገኙ ይችላሉ።

የሮያል አውቶሞቢል ክለብ ኦፍ ዌስተርን አውስትራሊያ የተሽከርካሪዎችና ነዳጅ ክፍል ኃላፊ አሌክስ ፎረስት፣

“ኖቬትድ ሊዝ ካለዎት በፍሪንጅ ቤኔፊትስ ታክስ ላይ ቅናሽ ያገኛሉ። ይህም ለምሳሌ በአምስት ዓመት የሊዝ ውል ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ሊያስቆጥብልዎ ይችላል” ብለዋል።

የኤሌክትሪክ መኪናን መጠቀም ከቤንዚን መኪና ይልቅ ርካሽ ነውን?

አዎን። በአጠቃላይ ሲታይ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መጠቀም ከቤንዚንና ከናፍጣ መኪናዎች ይልቅ ወጪ ቆጣቢ ነው።

ግምቶች እንደሚያሳዩት፣ ባለቤቶች በየዓመቱ የነዳጅ ወጪያቸውን እስከ 70 በመቶ፣ የጥገና ወጪያቸውን ደግሞ እስከ 40 በመቶ ሊቀንሱ ይችላሉ።

ፕሮፌሰር ዲያ እንደሚሉት፣ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ወጪና የጥገና ክፍያ በጊዜ ሂደት ትልቅ ቁጠባ ያስገኛል። ሆኖም መኪናቸውን በቤት ሳይሆን በሕዝባዊ መሙያ ጣቢያዎች ብቻ የሚሞሉ ሰዎች የሚያገኙት ቁጠባ ያነሰ ሊሆን ይችላል።

ኤሌክትሪክ በኪሎ ሜትር ሲሰላ ከቤንዚን በጣም ርካሽ ነው። በተጨማሪም፣ የኤሌክትሪክ መኪናዎች በመካኒካዊ አወቃቀራቸው ቀለል ያሉ በመሆናቸው የጥገና ወጪያቸውም ዝቅተኛ ነው።
ሁሴን ዲያ

የኤሌክትሪክ መኪናዎች በአንድ ሙሌት ምን ያህል ርቀት ይሄዳሉ?

ፕሮፌሰር ዲያ እንደሚገልጹት፣ ብዙ የመካከለኛ ደረጃ የኤሌክትሪክ መኪናዎች በአንድ ሙሉ ሙሌት ከ400 እስከ 500 ኪሎ ሜትር ሊጓዙ ይችላሉ። ነገር ግን፣ የረጅም ርቀት ጉዞዎች ቅድመ ዕቅድና ዝግጅትን ይፈልጋሉ።

“ችግሩ ከአንድ ክፍለ ሃገር ወደ ሌላ ሲጓዙ፣ በተለይም በገጠራማና ርቀት ባላቸው አካባቢዎች ነው። ፈጣን መሙያዎች የሌሉባቸው በሺዎች ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠሩ መስመሮች አሉ” ሲሉም አክለዋል።

የኤሌክትሪክ መኪናን በቤት ውስጥ መሙላት ይቻላል?

አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ መኪና ባለቤቶች መኪናቸውን በቤታቸው ባለው መደበኛ የኤሌክትሪክ ሶኬት በመጠቀም ይሞላሉ።

አሌክስ ፎረስት እንደሚሉት፣ ይህ በየቀኑ አጭር ርቀት ለሚጓዙ ሰዎች በቂ ሊሆን ይችላል።

“ከመንገድ ውጭ የመኪና ማቆሚያ ቦታ እና በጋራዥዎ ወይም በመኪና ማቆሚያ ጥላ ውስጥ የኤሌክትሪክ ሶኬት ካለ፣ በተሰጠው የመሙያ ኬብል መኪናዎን መሙላት ይችላሉ” ብለዋል።

በየቀኑ ብዙ ርቀት የሚጓዙ ሰዎች ደግሞ በቤታቸው ልዩ የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ቢገጥሙ ተጨማሪ ምቾት ሊያገኙ ይችላሉ።

በአፓርታማ የሚኖሩ ሰዎች ግና እንዲህ ዓይነት መሙያ ከመግጠማቸው በፊት ከሕንፃው አስተዳደር ፈቃድ ማግኘት ሊኖርባቸው ይችላል።

በየቀኑ ረጅም ርቀት የሚነዱ፣ በተደጋጋሚ የረጅም ጉዞ የሚያደርጉ እና ባትሪውን በብዛት የሚጠቀሙ ከሆነ፣ በዚህ ሁኔታ የቤት ውስጥ ልዩ መሙያ ትልቅ ጥቅም ያለው ይሆናል።
አሌክስ ፎረስት

ያገለገለ የኤሌክትሪክ መኪና ከመግዛትዎ በፊት ማወቅ የሚገባዎ ምንድን ነው?

በአውስትራሊያ ያገለገሉ የኤሌክትሪክ መኪኖች ገበያ አሁንም በአንፃራዊነት አዲስ ቢሆኑም፣ ተጠቃሚዎች በእነዚህ መኪናዎች ላይ የሚኖራቸው እምነት እየጨመረ ነው።

ባለሙያዎች ግዢ ከመፈጸምዎ በፊት የባትሪውን ዋስትና፣ የጥገና አማራጮችን እና ከሽያጭ በኋላ የሚሰጠውን ድጋፍ በጥንቃቄ እንዲመለከቱ ይመክራሉ።

አቶ ፎረስት እንደሚሉት፣ የመኪና ግምገማዎችን ማንበብ ብቻ ሳይሆን የባለቤቶችን ተሞክሮም መመልከት ያስፈልጋል።

“ጥሩ ጥናት ያድርጉ። የመኪና ግምገማዎችን ብቻ አይመልከቱ፤ ሰዎች መኪናውን ለጊዜው ከተጠቀሙበት በኋላ ያላቸው ልምድ ምን እንደሆነም ያጢኑ። ለሚከፍሉት ዋጋ በትክክል ምን እንደሚያገኙ እና መኪናው ፍላጎታችሁን የሚያሟላ መሆኑን ያረጋግጡ።” ሲሉም መክረዋል።

ስለ አዲሱ የአውስትራሊያ ሕይወትዎ ተጨማሪ ጠቃሚ መረጃና ፍንጮች ለማግኘት የአውስትራሊያ ስትገለጥ ፖድካስትን ይከተሉ አሊያም ደንበኛ ይሁኑ።   

ጥያቄዎች ወይም ርዕሰ ሃሳቦች ካለዎት? 

australiaexplained@sbs.com.au ኢሜይል ይላኩልን።


Latest podcast episodes

Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Stream now