ክቡራን ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፣
ክቡራን የማኅበረሰብ መሪዎች፣
የሀገራችን ወዳጆችና አጋሮች፣
በአውስትራሊያ፣ በኒውዚላንድ፣ በፊጂ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒ እና በሶሎሞን ደሴቶች የምትኖሩ ክቡራን የኢትዮጵያ ዜጎችና የዲያስፖራ አባላት፣
በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የካንብራ ኤምባሲ ስም እና በራሴ ስም፣ እንኳን ለ130ኛው የአድዋ ድል በዓል በሰላምና በክብር አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
የአድዋ ድል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ የማይደበዝዝ የብሔራዊ ክብር፣ የነፃነትና የሉዓላዊነት ምልክት ነው።
አድዋ በጀግንነት የተገኘ የጦር ድል ብቻ ሳይሆን፣ በዘመኑ የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ብልሃት፣ በመንግሥታዊ አቅም እና በሕዝባዊ አንድነት የተጠናከረ ታላቅ ብሔራዊ ድል ነበር።
ይህም ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ዓለም አቀፍ አውድ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ያላትን ብቃት ያሳየ ነበር።
አድዋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝቦችና ለነፃነት ፈላጊ ሕዝቦች ሁሉ የክብር ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
ዛሬ ከአድዋ የምንወስደው ትምህርት ግልፅ ነው፤ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር፣ ሉዓላዊነታችንን በመጠበቅ እና ብሔራዊ ጥቅማችንን በተቀናጀ መንገድ በማጠናከር ወደ ዘላቂ ልማትና ብልጽግና መጓዝ ነው።
በዚህ አውድ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በማጎልበት ያሉብንን የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ለመቅረፍ፣ ብሔራዊ የልማት አጀንዳችንን ለማሳካት እና ከጎረቤት አገራት ጋር በመተባበር የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተግባር መሥራት ያስፈልጋል። በዚሁ መሰረት መንግሥታችንም በትጋት እየሠራ ይገኛል።
በተለይም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ጉዳይ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚፈታ የፍትሃዊነት እና የኢኮኖሚ ነፃነት ጥያቄ መሆኑን እንደገና እናረጋግጣለን።
ይህ ጉዳይ የአገራችን ሉዓላዊ መብትን በማክበር በማጠናከር ለሕዝባችን ዘላቂ እድገትና የኢኮኖሚ ነፃነት መሠረት የሚሆን ትክክለኛ ብሔራዊ አጀንዳ ነው።
የመንግሥታችንና የህዝባችን ጥያቄ የሆነው የባህር በር ጥያቄያችን ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላምና በመግባባት የሚፈታ መሆኑ የመንግስታችን ግልጽ አቋም ነው።
አድዋ በሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ተሳትፎ የተገኘ መሆኑ ዛሬ የምንገነባው የዴሞክራሲ ሥርዓት በሕዝብ ባለቤትነት ላይ እንዲመሠረት ጠንካራ መሠረትና ትምህርት ይሰጠናል።
ፍትሃዊና ተዓማኒ ምርጫን ማካሄድ፣ እያንዳንዱ ዜጋ በሕጋዊ መንገድ በምርጫ ካርዱ ብቻ የፖለቲካ ተሳትፎውን እንዲያረጋግጥ ማበረታታት የሁላችንም የብሔራዊ ግዴታ ነው። ለዚህም በየመስኩ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለዚህ እሳቤ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።
ይህንን አገራዊ ራዕይ ለማሳካት አሁናዊ ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊና ክልላዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት የሕዝብ አንድነትና አገራዊ ስሜት በመፍጠር ሉአላዊነታችን ለማስከበርና አገራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ በሐሰተኛ ትርክቶች ከመከፋፈል ይልቅ በጠንካራ ብሔራዊ አንድነት መቆም ይጠበቃል።
ልዩነታችንን እንደ ኃይል በመቀበል የጋራ ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስቀደም የአድዋን መንፈስ በተግባር ማስቀጠል ይገባናል።
ክቡራን ወገኖች፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ አትዮጵያውያን፣
እናንተ በውጭ የምትኖሩ የኢትዮጵያ ልጆች የሀገራችሁ አምባሳደሮች ናችሁ።
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ በኢንቨስትመንት፣ በእውቀት ልውውጥ እና በብሔራዊ ድጋፍ የምታበረክቱት አስተዋፅኦ ለኢትዮጵያ የወደፊት ጉዞ እጅግ ወሳኝ ነው።
በመሆኑም የጀመራችሁትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እና የልማት፣ የኢንቨስትመንት፣ የትምህርትና እውቀት፣ የቴክኖሎጂ፣ የረሚታንስ ተሳትፎአችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።
እንደ አድዋ ጀግኖቻችን በአንድነት እንቁም!
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም በጋራ እንጠብቅ!
አገራችንን ወደ ዘላቂ ልማትና ብልጽግና እንመራ።
እንኳን ለ130ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!
አመሰግናለሁ።





