አቶ ካሣሁን በቅድሚያ ለተሰጠኝ ዕድል በጣም አመሰግናለሁ!
በመቀጠልም በራሴና ካንቤራ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቼ ስም በመላው አውስትራሊያ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2018 አዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
አዲሱን ዓመት የምናከብረው የኢትዮጵያ ማንሠራራት ዕውን የሆነበት ጊዜ መሆኑን እያስታወስን ነው።
በሁሉም ዘርፎች የኢትዮጵያ ዕድገትና ብልፅግና የበለጠ የምንፀናበት ዓመት ነው።
ዘንድሮ በርካታ ፈተናዎችን በፅናት ተሻግረን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የምናስመርቅበት ዓመት እንደሆነ የሚታወቅ ነው።
ከአድዋ ጀምሮ እስከ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድረስ የኢትዮጵያ ታላላቅ ድሎች የጋራ ጥረት፣ የመስዋዕትነት እና የጋራ ራዕይ ውጤቶች ናቸው።
የአንድነታችን ህያው ምስክር መሆኑን ያስታውሰናል።
ለዚህ እውነት በአውስትራሊያ እና በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ታሪካችሁ ይመሰክራል።
ለኢትዮጵያ ያላችሁን ፍቅር፣ በሃገራችን የልማት ሂደት ውስጥ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በማኅበረሰብ ድጋፍ፣ በቦንድ ግዢ ተሳትፎና ጥረት፣ ከተለያዩ ቋንቋዎች እስከ የተለያዩ ምግቦች፣ አልባሳት፣ ዜማዎች እና ወጎች፣ ዘፈኖችና ጭፈራዎች፣ በባሕል፣ በሃይማኖቶች፣ በማንነት እና በታሪክ የተዋበን ሕዝቦች ባለቤት መሆናችንን በተለያዩ መድረኮች በማስተዋወቅ የምታደርጉት ሥራዎቻችሁ የሕዝባችሁ ወኪልና አምባሳደሮች መሆናችሁን ያረጋግጣል።
የኢትዮጵያ ውብና ማራኪ ዕሴቶች በአውስትራሊያ በእናንተ ተግባር እና ስኬት ይናገራሉ።
ለእዚህ ሀገር ሕብረ-ብሔራዊነት ሕብረ-ባሕላዊነት ያላችሁ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነው።
በማኅበራዊ አገልግሎት፣ በጤና፣ በትምህርትና ምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እና በሌሎችም መስኮች ለአውስትራሊያ የምታበረክቱት ድርሻ የሚበረታታ ነው።
አንድነታችሁ እየጠነከረ እና ተሳትፎአችሁ እየበዛ ሲሄድ፣ በአውስትራሊያ ሕዝብና መንግሥት የመደመጥ እና ተፅዕኖ የመፍጠር ሁኔታ እየጨመረ መሄዱ ግልጽ ነው።
በመሆኑም አዲሱን ዓመት ስናከብር የአንድነት መንፈስን በማጠናከር በልዩነቷ የምትኮራ፣ በአንድነቷ የጠነከረች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የጀመራችሁትን መልካም ሥራዎችን አጠናክራችሁ የምትቀጥሉበት ዓመት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።
በዚህ አጋጣሚ በዓሉን በግልና በጋራ ስታከብሩ ለሁለትዮሽ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም ፍሰት ዕድገት በምንችለው አቅም እንድንረባረብ፣ በቀጣይነትም የሀገራዊ ምክክር መድረኮች ላይ በንቃት እንድንሳተፍ ጥሪ አቀርባለሁ።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሀገራዊ እና ዳያስፖራ ቀዳሚ ጉዳዮች ላይ ያለንን አጋርነት ለማጠናከር፣ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት፣ አገልግሎት ለመስጠት፣ ተደራሽነቱን ለማስፋት፣ ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ሰላም፣ እንድነት፣ ዘላቂ ልማትና ብልፅግና የሚበጅ ማንኛውም ድጋፎች ለማሳለጥ ቁርጠኛ መሆናችንን ለመግለጽ እወዳለሁ።
በመጨረሻም፤ አዲሱ ዓመት በሀገራችን ዕድገት ሰላም እና ብልፅግና አዎንታዊ አስተዋፅኦ የምናደርግበት ዘመን እንዲሆንልን እየተመኘሁ፣ በድጋሚ አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የተስፋ እና የብልፅግና እንዲያደርግልን ምኞቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።
አመሰግናለሁ!