የኔ ታሪክ፤ "ባልሰልጠነ ዘመን የሰለጠነ ሃሳብ ሰጥተውን ያለፉ አባቶቻችን ዕዳ አለብን" ሰብለወርቅ ታደሰ

My Story: Seblewerk Tadesse

Seblewerk Tadesse Source: Courtesy of ST

የዛሬ “የኔ ታሪክ፤ ከኢትዮጵያ እስከ አውስትራሊያ” እንግዳችን ወ/ሮ ሰብለወርቅ ታደሰ ናቸው። የግለ-ታሪክ ትረካቸው መነሻ የትውልድ ሠፈራቸው የሆነችው ቤልኤይር ናት። የኢትዮጵያ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ ነው የምትገኘው።


ትምህርት ባለ ሁለት ወገን ስለት ያለው ነውና በግለሰብ አዕምሮ ውስጥ ሰርፆ ዓለምን በአዎንታዊና አሉታዊ ገፁ ይቀርፃል፤ ይለውጣል።

ትንሿ ሰብለ እግሮቿ ወደ ቀበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ካመሩበትና ጉብሏ ሰብለ በኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአዕምሮ ጉልምስና ከደረሰችበት ጊዜ አንስቶ ውስጣዊ ቅርጽና ይዘታቸው የታነፀው በአዎንታዊነት ነው።

በዘመነ ጉልምስናም የሰብለወርቅ ዕሳቤ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ የግብይት አስተዳደር ዲግሪ ምልከታ ብቻ አልተወሰነም። ገፍቶ-ዘልቆ የአካዳሚ ነፃነት ዋጋን ለመረዳት፣ በሃሣብ የበላይነት ለማመን፣ ላለመስማማት የመስማማትን አቅምን በማዳበር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ በሰላማዊ መንገድ እንጂ በአመፅ መከሰት የለበትም የሚሉ አተያዮቻቸውን አዳብሯል።

ያም የዲሞክራሲ መሠረት ለሆነው ለማኅበራዊ ፍትሕ ጥያቄ አንጋቢነት አነሳስቷቸዋል። ከቃለ - ነቢብ ወደ ግብርም አሸጋግሯቸዋል። በ2004 የቀስተ ደመና ፓርቲን በወጣቶች ሊግ አደራሽነትና ሲልም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የድርሻቸውን ተወጥተዋል።

ቀስተደመና የቅንጅት ፓርቲ አካል ሲሆንም፤ በ’97ቱ ምርጫ በአዲስ አበባ አራዳና አዲስ ከተማ አደራጅተዋል።

My Story: Seblewerk Tadesse
Source: Courtesy of PD

ይሁንና የ’97ቱ ምርጫ ቅንጅትን ለሩቅ አሳቢ - ቅርብ አዳሪነት በመዳረጉ፤ እሳቸውን ጨምሮ የአመራር አካላቱ ዘብጥያ ወርደዋል። ከ18 ወራት ፈታኝ የእሥር ሕይወት በኋላ ግና ለስደት ሕይወት ግድ ተሰኝተዋል።

የፍቅሯ ግለት እስከ ዛሬም ውስጣቸው ግሎ ያለችውን የውድ አገራቸውን ኢትዮጵያ ድንበር ተሻግረው ወደ ኬንያ ገቡ። ጥቂት ቆይቶም ኡጋንዳ ዘለቁ። ኡጋንዳ ሳሉ ቀናትና ሳምንታት በወራት እየተቆጠሩ ሳለ፤ ስደተኛነታቸው በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን በኩል ዕውቅና ተቸሮት ነበርና የአውስትራሊያ ዳግም ሠፈራ ቪዛ ተቸራቸው።

እርግጥ ነው፤ አገረ አውስትራሊያ ውስጥም ሆነው ለፍትሕ ድምፃቸውን ከማሰማት ቸል አላሉም።

My Story: Seblewerk Tadesse
Seblewerk Tadesse Source: Courtesy of ST

አፍታም ሳይቆዩ ወደ ማኅበራዊ ሥራ ግልጋሎት ተሰማርተው ለቤት ውስጥ አመፅ ሰለባነት የተዳረጉ ኢትዮጵያውያንና አውስትራሊያውያን ሁኔታ ግና ሕሊናቸውን ሞግቷል።

ሆኖም ችግር አግናኝ ሳይሆኑ፤ ከቶውንም የመፍትሔ አካል ለመሆን በደቡብ ማኅበረሰብ የፕሮጄክት ሥራ አስኪያጅነታቸው ለቤት ውስጥ አመፅ ጥቃት ተጎጂዎች እገዛ በማድረጉ ዘርፍ አስተዋፅዖዎችን እያበረከቱ ይገኛሉ። ያም አንዱ ከማኅበረሰባዊ ግልጋሎቶች የሚመነጭ የመንፈስ እርካታ ማግኛና ዕሴቶቻቸውን መተግበሪያ ሆኗቸዋል።

የኩዊንስላንድ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር አመራር አካል በመሆንም ንቁ ተሣትፎ አበርክተዋል።

በግል ሕይወታቸው አውስትራሊያ ከማለፊያ የሕይወት ጓደኛ ጋር አጣምራ በሁለት ልጆች እናትነታቸውን የአብራካቸውን ፍሬ እንዲያዩ አብቅታቸዋለች።

My Story: Seblewerk Tadesse
Seblewerk Tadesse with her children Source: Courtesy of ST

Share

Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now