ቀጣይ ተልዕኮ ትምህርት፣ ሥራና ማኅበረሰባዊ አገልግሎት
በኩረ ትጉኅን ኃይለልዑል ገብረሥላሴ የመንፈሳዊ አገልግሎታቸው በረከት መሠረት እየያዘ ሲመጣ በጉዟቸው ተቋርጦ ወደ ነበረው የከፍተኛ ተቋም ትምህርታቸው አማተሩ።
ከምሕንድስና ወደ ነገረ መለኮት (ቲዮሎጂ) ጥናት ተሸጋገሩ።
ከዲከን ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቁ።
ለጥቀውም፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ልማት ከላትሮብ ዩኒቨርሲቲ ተቀበሉ።
ቆይተውም፤ ከሜልበርን ዩኒቨርሲቲ በሕዝባዊ ፖሊሲና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ አገኙ።
ከትምህርት ወደ ሥራ አመሩ።
በዲከን ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ አማካሪነት ለሁለት ዓመታት ሠሩ።
ተሸጋግረውም፤ በቪክቶሪያ መንግሥት የባሕር ማዶ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃና፣ ግምገማና የሙያ አማካሪነት ቀጠሉ።
ለሁለት አሠርት ዓመታት ያህልም በተለያዩ መምሪያዎች እስከ ገዲብ የሥራ ኃላፊነት ደረሱ።
አክለውም፤ በማኅበረሰባዊ የበጎ ፈቃደኛነት ሥራዎች ተሠማሩ።
ድርጅት አቆሙ።
ለአፍሪካውያን ማኅበረሰብ አባላት የልዩ ስልጠና ፕሮግራሞችን በመደፍ፤ በአመራር፣ የዳግም ሠፈራና የንግድ ሆርሻዎች ለበርካታ ሰልጣን የማኅበረሰብ አባላት ክህሎቶችን የማስጨበጥ አስተዋፅዖዎችን አበረከቱ።
በሀገር በቀል ማኅበረሰባዊ ዘርፎችም ለሰባት ዓመታት በዕድር ሰብሳቢነት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሁለገብ የሕንፃ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ዘለግ ላሉ ጊዜያት እያገለገሉ ይገኛሉ።
በተለያዩ የማኅበረሰባት ተቋማት ውስጥም በቦርድ አባልነት አገልግለዋል።
The Medal of the Order of Australia (OAM) የክብር ኒሻንን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን ተሸልመዋል።

በብፁዕ አቡነ ገብርኤልም ለመንፈሳዊ አገልግሎት በአሠርት ዓመታት ለሚቆጠሩ አስተዋፅዖዎቻቸው 'በኩረ ትጉኅን' ተብለው ተሰይመዋል።
በቅርቡም በሰሜናዊ ምዕራብ የፍልሰተኞች መታደጊያ ማዕከል (MRC) በሥራ አስፈፃሚነት እያገለገሉ ይገኛሉ።





