ኑሮ በአውስትራሊያ
ለዳንኤል የአውስትራሊያ ኑሮ ጅመራ በረከቱ የወ/ሮ ክቤ ነው።
የወንድሙ የፓስተር ግሩም ባለቤት።
ወደ አውስትራሊያ እንዲመጣ አግባብ ያለው የማመልከቻ ቅፅ ሞልተው ላኩለት።
ተሳካ።
መጣ።
ዛሬም ድረስ ለወንድሙና ለባለቤቱ መልካም አሳቢነትና ቸርነት ውለታ እንደገባው ነው።
ሆኖም፤ የአዲስ ኑሮ ጅማሮው አልጋ በአልጋ አልነበረም።
ፈተና ነበረው፤ ከባይተዋርነት እስከ ሕይወት ግንባታ ሂደት።
ኑሮ ያለ ትግል አይገፋምና የሸሚዙን እጅጌ ሰብሰበ፤ ቀበቶውን አጠበቀ።
መኖሪያው አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ይኖሩበት ከነበረ ቀዬ ራቅ ያለ ነበርና ቀረብ ብሎ ተጎራበተ።
ከቤተክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጋር ተዋወቀ።
ምክራቸውን ለገሱት።
የሕይወት ተሞክሯቸውን አጋሩት።
ድጋፋቸውን ቸሩት።
ወጥቶ መግባት፤ ሥራ መሥራት ጀመረ።
በሥራው ላይ ለሰባት ዓመታት ፀንቶ ቆየ።
ኑሮን ተቋቋመበት።
ቤት ለመግዛት የበቃው ሥራ በጀመረ አንድ ዓመት ጊዜ ነው።
ትንሽ ትንፋሽ ሲያገኝ፤ ስለ ንግድ ሥራ ማሰላሰል ያዘ።
እምብዛም ሳይቆይ በሰንሻይን ክፍለ ከተማ የጎጆ ካፌና ሬስቶራንት ባለቤት ሆነ።
ቤቱ ተለመደ፤ ደንበኞች አፈራ።
የኢትዮጵያ ቡናና ባሕላዊ ምግብ አቀራራቡ ከእነ ጣዕሙ ተወዳጅ ሆነ።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ ተወስኖ አልቀረም።
ከቶውንም በ2025 አጋማሽ ሜልበርን ካሉ ካፌዎች ማጣሪያ አልፈው ለመጨረሻ ደረጃ ለሽልማት በዕጩነት ከቀረቡት ውስጥ ጎጆ ካፌ አንዱ ለመሆን በቃ።
የሀገሩን የኢትዮጵያ ስም በማስጠራቱ በእጅጉ የላቀ ክብርና ልዩ ስሜት አለው።
ኢትዮጵያ ለስደቱ ሰበብ ብትሆንም፤ ለትድግናም አብቅታዋለችና ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ማንነቱ ፀንቶ አለ።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ልዩ ሥፍራ እንዳላት አጥብቆ ያምናል።
ኢትዮጵያ ስታድግ፤ አፍሪካም ታድጋለች። ኢትዮጵያ ስትወድቅ፤ አፍሪካም ትወድቃለች።ዳንኤል አለማር
በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ጨለምተኛ አተያይ የለውም፤ ከቶውንም ብሩህ ተስፋ እንጂ።
ኢትዮጵያ በመንገዳገድ ላይ ያለች፤ ወደ ከፍታም ለመውጣት የምትጥርበት ጊዜ ላይ ናት። በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ አለኝ፤ ከኢትዮጵያ ብዙ እንደሚጠበቅ አውቃለሁ።ዳንኤል አለማር
ለዳንኤል ኢትዮጵያ አልፋና ኦሜጋው ናት።
በፖለቲካ ወጀብ ንጠት ኢትዮጵያዊነቱ አልተሸራረፈም፤ እንደ መንፈሳዊ ሕይወቱ ሁሉ በብሔራዊ ማንነቱም ፅኑዕ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከምንም በላይ አጉልቼ አያለሁ፤ ሀገሬን በጣም እወዳለሁ፤ እግዚአብሔር ሀገሬን ከፍታ ላይ አድርሶ ያሳየኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።ዳንኤል አለማር
መንፈሳዊ ሕይወት
በሜልበር የዘፀዓት ኢትዮጵያውያን ወንጌላውያን ቤተክርስቲያን ለታላቅ ሞገስ በቅቶ ለምረቃና የላቀ አገልግሎት እንዲበቃ ካስቻሉት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መካከል አንዱ ዳንኤል ነው።
የሕንፃ አስገንቢ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሆኖ የመንፈሳዊ ሕይወት ግለ ድርሻውን ተወጥቷል።
የዘፀዓት ቤተክርስቲያን ግንባታ ለእኔ ልዩ ክብር ነው።ዳንኤል አለማር
ሀገራዊ ቃል ኪዳን
ዳንኤል የትዳር ሕይወቱን ከሀገሩ ነጥሎ አላየም።
የሕይወቱ ማዕከል ለሆነችው ኬና ጉዲና የትዳር ጥያቄና የቃል ኪዳን ውሉ እንዲህ ነበር።
"ባለቤቴን ለዕጮኝነት፣ ለትዳር ስጠይቃት በመጀመሪያ ያልኳት አንድ ነገር ነው"
"ፈቃደኛ ከሆንሽና አብረን የምንኖር ከሆነ፤ እኔ ሀገሬ ላይ ነው መኖር የምፈልገው፤ እና የአንቺ ሃሳብ ምንድነው? ይህን ማወቅ አለብኝ አልኳት"
ምላሿ "እኔም ሀገሬን እወዳለሁ፤ መሔድ የምፈልገው ወደ ሀገሬ ነው ነበር ያለችኝ። ስምምነታችን የሚቀጥለው እንደ እዚህ ነው"
ዳንኤል፤ በሀገር ቤት ትልሞቹ ካሠፈራቸው ውስጥ በቀዳሚነት ተጠቃሹ ቢያንስ ለ10 ቤተሰብ ያህል የሥራ ዕድል መክፈት ነው።
የኬንያው ታዳጊ ወጣት ስደተኛ በአሁኑ ወቅት የአራት ልጆች አባት ነው።
በእዚሁ አጋጣሚ በቀጣዩ ሳምንት በሀገረ አውስትራሊያ ለሚከበረው ሕዝባዊ በዓል ከወዲሁ "መልካም የአባቶች ቀን!" ስንል ለአቶ ዳንኤል አማረና መላ ቤተሰቡ እንመኛለን።