"ለዛሬ መድረሻዬ ሆነኝ የምለው፤ በስደት ካምፕ የነበረኝና የሰንቅኩት ሕይወት ነው" ዳንኤል አለማር

Alemar FP.png

Daniel Alemar. Credit: SBS Amharic / D.Alemar

"የኃይለ ሥላሴ ቤተሰብ ነው እንዳትነኩት" - ዳንኤል አለማር፤ በግለ ታሪክ ወጉ ገና ለአካለ መጠን ሳይደርስ በለጋ ዕድሜው ከእናትና ወንድሞቹ ጋር እንደምን የትውልድ ሀገሩን ኢትዮጵያን ለቅቆ ለኬንያ የስደት ካምፕ እንደተዳረገና የኢትዮጵያ ስም እንደምን ከእሥር እንዳስለቀቀው ነቅሶ ያወጋል።


ትውልድና ዕድገት

ዳንኤል አለማር፤ ዕትብቱ ተቆርጦ የተቀበረው በሀገረ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ነው።

እግሮቹ ጠና፣ ቁመቱ ዘለግ ማለት እንደጀመረ ግና ውድ አያቱ ዘንድ ቡታጅራ ሔዶ አድጓል።

እዚያ አልቀረም።

ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ቡታጅራን ተሰናብቶ ወደ ናዝሬት / አዳማ አቅንቷል።

የናዝሬት ቆይታው ግና ከሁለት ዓመታት አላለፈም፤ አጭር ነበር።

የጉልምስናና የዐዋቂነት ዘመኑን በእጅጉ በሚያፈቅራት ሀገሩ ኢትዮጵያ ለማሳለፍ አልበቃም።

እ.አ.አ. በ1999 ቤተሰቦቹ ግድ አሰኚ በሆኑ ሁኔታዎች ክስተት ሳቢያ ወደ ኬንያ አመሩ።

ከእናትና ወንድሞቹ ጋር በታዳጊ ወጣትነት ዕድሜው የጎረቤት ሀገር ጥገኛ ሆነ።

በስደት ዓለም ፈተናዎችን መገዳደር፤ መልካም ዕድሎችን መጠባበቅ ጀመረ።

ከሥፍራ ወደ ሥፍራ ለመንቀሳቀስ የመኖሪያ ፈቃድ ወይም የስደተኛነት ማረጋገጫ ሰነድን ይዞ መገኘት ግድ ሆነ።

እንቅስቃሴው በሕግ ተገደበ።

የባዕድ ሀገር ጠለላ ጠያቂነት ውስን ነፃነት ልብ አለ።

ያለ ሕጋዊ የማንነት ማረጋገጫ ሰነድ ሲዘዋወር ዘብጥያ ወርዷል።

አንዴ አይደለም፤ በተደጋጋሚ።

በሁነቱ ቢከፋም፤ በስሎበታል።

የቀድሞዎቹ የኢሕዲሪ መንግሥት ባለስልጣናት ከከፍታ ዝቅታ ላይ ሆነው በዓይኑ በብረቱ ተመልክቷል።

በዕድሜ ከገፉ፤ በኑሮ ከበሰሉ አረጋውያን ሕይወት ቀያሽ ምክሮችን አግኝቶበታል።

ለፅኑዕ መንፈሳዊ ሕይወት ዕነፃም በቅቶበታል።

የዳንኤል የስደት ሕይወት በናይሮቢ ብቻ አላከተመም።

ካኩማ የስደተኞ መጠለያ ካምፕ ወስዶታል።
Refugee Camp.png
Daniel Alemar. Credit: D.Alemar
የካኩማን ከምድረ በዳነት ወደ ትንሽዬ ሕይወት ያላት የስደተኞች ከተማነት መለወጥ የዓይን እማኝ ሆኗል።

በተስፋና የኑሮ ትግል መካከል ያሉ ስደተኞች ፈተና አደንድኗቸው፤ ተስፋ ታግሎ የማሸነፍ ውስጣዊ ኃይልና ፅንዓትን አላብሷቸው ተመልክቷል።

ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ውስጥ ከንፉግነት ይልቅ ሰብዓዊነት የአብሮነት ሚዛንን ደፍቶ አይቷል።

የትስስቦሽና ድግግፎሽ ኑሮን ተጋርቷል።

መንፈሳዊ ሕይወት በጨለማ ውስጥ ብርሃን ፈንጥቆለት መፅናናትን አላብሶታል፤ ከ'እኔ' ይልቅ 'የእኛ'ን አስተውሎት ቸሮታል።

ያም የስደት ሕይወትን መሪር ፈተና ለመቋቋም፤ በኑሮ ትግል ውስጥ ስኬትን አማትሮ ለማየት፤ እስከ ዓለም ጫፍ ለመጓዝ የፅንዓት ስንቅ ሆኖታል።

ለቅቋት ቢሰደድም፤ የኢትዮጵያ ታላቅነት ትሩፋት በአስከፊ የእሥር ቆይታ እንኳ ታድጎታል፤ ሞገስን ተላብሶበታል።

የእሥር ሕይወት - 'የኃይለ ሥላሴ ቤተሰብ ነው እንዳትንኩት'

በአንደኛው የእሥር ጊዜው "ከየት ነህ?" ተብሎ ሲጠየቅ

"ከኢትዮጵያ" ነበር መልሱ።

ያኔ ነው፤ የመልካሚቱ ሀገር ስም ሲነሳ የሰሙ የራስ ተፈሪ ተከታዮች አፈፍ ብለው "የኃይለ ሥላሴ ቤተሰብ ነው እንዳትነኩት" ብለው ከእሥር እስኪወጣ ድረስ ዋስ - ጠበቃ የሆኑት።

ከእሥር አወጣጡም 'በስውር ኃይል' ድጋፍ የታጀበ ነበር።

ዘብጥያ በወረደ 10ኛ ቀኑ አንዲት ኬንያዊት የባለስልጣን ልጅ በሰዓት ዕላፊ ተይዛ ዳንኤል ካለበት እሥር ቤት ትገባለች።

የወንዶችና ሴቶች እሥር ቤቶቹ ጎን ለጎን ነበሩና ከየት እንደመጣና ለምን እንደታሠረ ጠየቀችው።

በስደተኛ መታወቂያ ችግር እንደሆነ ነገራት።

አፍታም ሳትቆይ ስሟ ተጠርቶ የእሥር ክፍሏን ለቅቃ ወጣች።

ዘግየት ብሎ የዳንኤል ስም ተጠራ።

'አቤት' አለ።

'ተንስ ተባለ' ተነሳ።

ወደ መውጫ በር እንዲሔድ አመላከቱት።

ኬንያዊቷን ሴት ያስለቀቀው ሰው ይጠብቀው ነበር።

ሰላምታ ተለዋወጡ።

የቤቱን አድራሻ ያውቅ እንደሁ ተጠየቀ።

ነገራቸው።

ላይመለስ ሔደ።

የኢትዮጵያ ታላቅነትና የቀድሞ መሪያዋ ውለታ ለስደተኛ ዳንኤል ተረፈ።

'ኢትዮጵያ ሆይ!" በሚያሰኝ ሁነት።

ወራት በዓመታት ተለወጡ።

ከአራት ዓመታት ዕላፊ ቆይታ በኋላ የዳንኤል የኬንያ ስደት ጊዜ አከተመ።

እናት ወደ አሜሪካ፣ አንድ ወንድም ወደ ካናዳ፣ ሌላኛው ወንድሙና ዳንኤል በቅደም ተከተል አውስትራሊያ ዘለቁ።

Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
"ለዛሬ መድረሻዬ ሆነኝ የምለው፤ በስደት ካምፕ የነበረኝና የሰንቅኩት ሕይወት ነው" ዳንኤል አለማር | SBS Amharic