ውልደትና ዕድገት
በትረ ትጉኅን ኃይለልዑል ገብረሥላሴ ውልደታቸው በሲዳማ ክፍለ ሃገር፣ በቦረና አውራጃ፣ በሊበን ወረዳ፣ ነገሌ ቦረና ከተማ ነው።
የተገኙትም ከእናታቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ በቀለና ከአባታቸው መምህር ገብረሥላሴ እርገጤ ተካው አብራክ ነው።
ፊደል ቆጠራ
ዕድሜያቸው ለቀለም ትምህርት ቀሰማ ሲደርስ ቀድመው የዘለቁት ቄስ ትምህርት ቤት ነው።
ሀሁ ቆጠሩ።
መልዕክተ ዮሐንስ አጠናቀቁ።
ዳዊት ደገሙ።
ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ተዛወሩ።
የዛሬ ስያሜውን ልብ ባይሉም፤ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል የቀለም ትምህርታቸውን የቀሰሙት በወቅቱ የቤተ ክህነት አንደኛ ደረጃ በነበረውና ቆይቶም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የሶማሊያ ወረራን መክቶ ድል የነሳበትን አጎባ ሞገስ በማላበስ "የአጎባ ድል" የሚል ስያሜ ባገኘው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
ሕይወት በእንቅስቃሴ የተመላ ነውና ወላይታ ይኖሩ ወደነበሩት እህታቸው ዘንድ አመሩ። የአራተኛ ክፍል የቀለም ትምህርታቸውን እዚያ ተከታተሉ።
በሊጋባ በየነ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት።
ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ወላጆቻቸው መኖሪያ ተመለሱ።
አፄ ካሌብ ትምህርት ቤት ገቡ። ቀሪውን የአንደኛ ደረጃ፤ ሲልም የሁለተኛ መለስተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
ግና በዓለማዊው የቀለም ትምህርት ቀሰማ ውስን አልነበሩም።
መንፈሳዊ ጉዞና አገልግሎት
ከዓለማዊው ዘመነኛ ትምህርት ጎን ለጎን የቤተ ክህነት ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር። ያም አቶ ኃይለልዑልን ገና ኮበሌ ሳሉ ለድቁና አድርሷቸዋል፤ ሲልም ለሊቀ ዲያቆንነት።
በትምህርታቸውም በመንፈሳዊ አገልግሎታቸውም ገፉ።
መንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባሕር ማዶ አሻገራቸው፤ ለሀገረ አውስትራሊያ አበቃቸው።
የሊቀ ዲያቆን ኃይለልዑል የአውስትራሊያ ጉዞ አስባብ በሜልበርን - አውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች የቤተ ክርስቲያን ምሥረታ ዕሳቤ ነው።
እ.አ.አ በ1992 የምዕመናቱና ምዕመናኑ ዕሳቤ እውን ይሆን ዘንድ ተልዕኮ ይዘው፤ አደራ ተቀብለው ወደ አውስትራሊያ መጡ።
ነሐሴ 23 የመንፈሳዊ አገልግሎት በረከታቸውን አሃዱ ብለው አበረከቱ።
መንፈሳዊ አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረው ለፀሎት ማካሔጃነት በቸርነት በተገኘ አንድ የፈረንጅ የቤተ ክርስቲያን አዳራሽ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ያሟላ አይደለም።
መንበረ የተዘረጋለት፣ ቤተ መቅደስ ሞገስ ተላብሶ የቆመለትና ታቦት የክብር ልዕለ ሥፍራውን የያዘበት አልነበረም።
ስዕለ አድህኖ ተሰቅሎ፣ ሻማ በርቶ ፀሎት ይካሔዳል። መዝሙር ይዘመራል። በዚያ መልኩ ነበር የዕለተ እሑድ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ሲሰጥ የቆየው።
ግና በእዚያ ተወስኖ አልቀረም። ለደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ማሪቢኖንግ ክፍለ ከተማ የኪራይ ቤት ተገኘ። ክፍያውም በሳምንት 20 የአውስትራሊያ ዶላር ነበር።
ዘግየት ብሎ መቅደስ ተሠራ። መንበር ተዘረጋ።
የመድኃኒዓለም ቅዳሴም መስከረም 1 ቀን የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ ዕለት ተካሔደ።
ከአያሌ ውጣ ውረድና ድካም በኋላ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሜልበርን - አውስትራሊያ ስትቆም ከመሥራቾቹ አንዱ ሆኑ።
የታሪክ አካልነት ቋሚ አሻራቸውን አሳረፉ።
የአቶ ኃይለ ልዑል የሁለት ዓመታት አገልግሎት በደመወዝተኛነት አልነበረም። ክፍያ የላቸውም። የመጠለያ፣ ምግብና ሌሎች ማኅበራዊ ድጎማዎች ነበር የነበሯቸው።
በሳምንት ከ20 እስከ 30 ዶላር የኪስ ገንዘብ አላጡም።
በእዚያ ማኅበራዊ ልገሳ ግና ደስተኛ ነበሩ።
ሲልም፤ ብፁዕ ኒቆዲሞስ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጀመሪያ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ተልዕኮ ለሟሟላትና አገልግሎቷንም አስፍታ ለመቸር እንድትበቃ ሊቀ ጳጳሱ ወደ ደቡብ አውስትራሊያ፣ ኒው ሳውዝ ዌይልስ እና ኩዊንስላንድ ክፍለ ሃገራት አመሩ። ሊቀ ዲያቆን ኃይለልዑልም አብረዋቸው ተጓዙ።
በሶስቱም ክፍለ ሃገራት የአደራጅ ኮሚቴዎችን ሰይመው ወደ ሜልበርን ተመለሱ።
ዕውቀት የዓለም ብርሃን ናትና ወደ አልረካው የትምህርት ጥማታቸው መለስ አሉ።
**********************************************
በቀጣይ ክፍለ ዝግጅታችን በትረ ትጉሃን ኃይለልዑል ገብረሥላሴ የትምህርትና የሥራ ዓለም ተግዳሮቶችንና የከፍታ ገጠመኞቻቸውን ነቅሰው ያወጋሉ።





