አንኳሮች
- የቦርድ አስፈላጊነት
- የቦርድ አላስፈላጊነት
- አማራጭ ተቋማዊ አወቃቀር
ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ቦርድ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። ማኅበሩ የእራሱ ጽሕፈት ቤት እንኳ የለውም፤ በጥገኝነት ያለ ነው። ነገር ግን ሕገ ደንቡ ላይ እስካለ ድረስ የመቀበል ግዴታ አለብን። እስካልተለወጠ ድረስ አመራሩም ከቦርዱ ተግባብቶ መሥራት አለበት።ደራሲ ታክሎ ተሾመ፤ የቀድሞው በታዝማኒያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ፕሬዚደንት
እኔ የቦርድ አባል ሆኜ እንዳየሁት፤ ቦርዱ ለማኅበረሰባችን የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚሠራ ነው - ነው የምለው። የቦርዱ አለመኖር አመራር ላይ ላሉ ሰዎች እንደፈለጉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። መተዳደሪያ ደንቡ ላይ እስካለ ድረስ ቦርዱን መቀበል አለብን። የቦርዱ መኖር በጣሙን ጥሩ ነው።አቶ አሕመድ ዳውድ፤ የቀድሞው በቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ቦርድና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል (ዕገዳ ላይ)
የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በጣም ትንሽ፣ ትርፍ አልባ የማኅበረሰብ ድርጅት ነው። ቢሮክራሲን ከማብዛት በስተቀር ቦርድ የሚያስፈጥር ነገር ይኖራል ብዬ አልገምትም። ከሥራ አስፈፃሚ ጋር የሚያጋጭ ከሆነ ለዘላለም ችግር ውስጥ እየገባን ነው የምንኖረው፤ አሁን ያለው መተዳደሪያ ደንብ እስካልተቀየረ ድረስ ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል።ዶ/ር ቢቾክ ዋን፤ በቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ መምህር
ለኢትዮጵያውያን ማኅብረሰብ ማኅበር በቪክቶሪያ ቦርድ ያስፈልጋል ብዬ አልልም። አንድን ቦርድ - ቦርድ የሚሰኙ መመዘኛዎችን ሳያሟላ የተፈጠረ ነው። ነገር ግን ቦርዱን ተቀብለው የተመረጡ ከሆኑ ሕገ ደንቡ የሚለውን መፈፀም አለባቸው። ቦርዱ የችግሮች መንስዔ ነው፤ ውጤትም አያመጣም፤ ለወደፊትም ችግር የሚፈጥር ነው።አቶ ዓለማየሁ በዛብህ፤ የቀድሞው በቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ዋና ፀሐፊ
ቦርዱ ከተመሠረተ ጀምሮ ግልፅ አቋም ነው ያለኝ፤ ቦርድ አስፈላጊ አይደለም። ማኅበሩ በበጎ ፈቃደኝነት ቢሮ ውስጥ የሚቀመጥ ሠራተኛ የሌለው ነው፤ ከፋይናንስም አንፃር የሚታወቅ ነው፤ አባላት የሉትም። ለሥራ አስፈፃሚ የሚመረጥ ሰው በሌለበት ሁኔታ የምን ቦርድ ነው የሚቋቋመው? እንዲህ ያለውን ቦርድ ወታደር የሌለው የጄኔራሎች ስብስብ ማለት ይቀላል።ደራሲ አዳሙ ተፈራ፤ የቀድሞው በቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ፕሬዚደንት