"'ሕይወት አጭር ናት' አባባል አይደለም፤ እውነት ነው። ካንሰር እንዳለብኝ ሲነገረኝ ሕይወት አጭር መሆኗን አስተምሮኛል" ደራሲ ሚስጥረ አደራው

Author Mistre Aderaw II.png

Author Mistre Aderaw. Credit: M.Aderaw

ተስጥኦና እውቀት፡ የመፅሀፍ አስተያየት ሚስጥረ አደራው። 2017። እኔ። አዲስ አበባ፡ ማንኩሳ ማተሚያ ቤት። ገፅ ብዛት፡ 184። ግርማ አውግቸው ደመቀ


መግቢያ

ወዳጄ ኤልያስ አወቀ ሰሞኑን “እኔ” ስለተሰኘ መፅሀፍ አጫወተኝ። ብዙውን ግዜ የምናወራው ስለመፅሀፍ ወይም በትምህርት ዙሪያ ስላለ ጉዳይ በመሆኑ፣ በዚህኛው ላይ አስተያየቱን ያጋራኝ እኔም እንዳነበው በመጋበዝ ነበር።

ለደራሲዋ ምስጋና ይግባትና መፅሀፉን ልካልኝ ለማንበብ በቃሁ።

በዚህ አጭር መጣጥፍ አስተያየቴ የሚያተኩረው በመፅሀፉ ላይ ቢሆንም፣ ከመፅሀፉ ይዘትና አቀራረብ በተጓዳኝ ከደራሲዋ ጋ እየተዋሀደ የሚቀርብበት አጋጣሚም አለ።

ይህም በሁለት ምክንያት ነው።

አንደኛው፣ የመፅሀፉ ይዘት በራሱ ደራሲዋ ላይ የሚያጠነጥን በመሆኑ ነው።

ሁለተኛው፣ ቋንቋው፣ የሀሳብ ትንታኔው፣ ፍልስፍናው፣ የስነልቦና ጥየቃው እና በአጠቃላይ አቀራረቡ ደራሲዋ በይዘቱ ከነገረችን በላይ ስለራሷ የሚናገርም ሆኖ ስላገኘሁት ነው።

 የመፅሀፉ ይዘት

“እኔ” የልቦለድ ስራ አይደለም። በደራሲዋ በራሷ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሁን እንጂ፣ ግለታሪክም ‘አውቶባዮግራፊ’ አይደለም። የግል ማስታወሻ በእንግሊዝኛው ‘ሚሟር’ ከሚባለው ክፍል ‘ጀነር’ የሚመደብም አይደለም። ይህን አስመልክታ በገፅ 13 ላይ እንዲህ አስፍራለች፤ “ይህ ጽሑፍ ድርሰት አይደለም፤ የምክር መጽሐፍም አይደለም፤ ያለተነገረና [ስህተት ያልተነገረና] ያልተደሰኮረበት ሐሳብም ይዞ አልመጣም። ይህን ጽሑፍ ባንድ ቃል ግለጭው ብባል፣ ‘ስሜት’ ነው” (ገፅ 13)።

ደራሲዋ ስለደረሰባት ውስጣዊ ቀውስ የሄደችበት መንገድንና ያለፈችበትን ጉዞ በሚያስገርም ብስለት የሚተርክ መፅሀፍ ነው።

“በዚህ ጽሑፍ ለዘመናት ያሰቃየኝን ሕመም ለማከም ሞክሬያለሁ። በመንፈስ ሕመሜ የተነሳ ከወደኩበት አዘቅት በቃላት መሰላል ከፍ ለማለት ጥሬያለሁ። ከምንም በላይ በዚህ ጽሑፍ ቃላቶችን ሸምኜ፤ እድሜዬን ሙሉ ተራቁቶ የነበረውን እኔነቴን ሸማ አልብሻለሁ። ይህ ጽሑፍ እንደ ዋሽንት ከባዶነቴ የተነሳ የማወጣው ዜማዬ ነው” (ገፅ 13)።

ፀሀፊዋ በግልፅ እንዳስቀመጠችው የመፅሀፉ ዓላማ ተደራሲን ያለመ ሳይሆን፣ ደራሲዋ የነበረችበትን “የእኔነት” ስነልቦናዊ ጥያቄ የጠየቀችበትና መልሱን ለመሻት ያለፈችበትን መንገድ ከውስጧ በፅሁፍ ለማውጣት የሞከረችበት ነው።

ይህን ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በሚከተለውም በግልፅ አስፍራለች፤ “ይህ ጽሑፍ የራሴን ሕመም ለማከም የቀመምኩት መድኃኔት፤ ከወደቅኩበት ስፍራ እራሴን ከፍ ለማድረግ የሠራሁት መሰላል፤ የተራቆተ ስሜቴን ለማልበስ የሸማመንኩት ሸማ ነው” (ገፅ 13)። ለምን ይህን ማድረግ እንደፈለገች በሚከተለው መልኩ ትገልፀዋለች፤

“እስከዛሬ አይቶ እንዳለየ በመሆን ሳልፈው የኖርኩት ያለፈ ማንነቴ፣ ከፊት ለፊቴ ቆሞ ‘እዪኝ፣ ተመልከቺኝ፣ ልብ በዪኝ … ካልረዳሽኝ ወደየትም አላራምድሽም …’ በሚል ሁለመናዬን እየተናንቀ መንገድ ዘጋብኝ። ምንም ምርጫ ስላልነበረኝ እርምጃዬን በመግታት ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።

 “እንደምንም አቅሜን አሰባስቤ ራሴን ለመመልከትና ስሸሸው የኖርኩትን ማንነት ለመጋፈጥ ተገደድኩ። ለጥቂት ቀናቶች በዚህ ስሜት ውስጥ ከዋኘሁ በኋላ፣ ምናልባት መልስ ባገኝ ብዬ ለምን አሁን እንዲህ ሊሰማኝ እንደቻለ ለማወቅ ውስጤን መመርመር ጀመርኩ።

“ይህ ነው እንግዲህ የዚህ ፅሑፍ መጠንሰሻ ሀሳብ። ወደኋላ ተመልሼ የተቦጫጨቁና የነተቡ ትዝታዎቼን በብዕር ለመስፋትና አንድ ምስል ለማግኘት ስል የሚሰሙኝን ስሜቶች በሙሉ በወረቀት ላይ ለማስፈር ወደድኩ “ (ገፅ 30)።

 ጥያቄዎቿ ተራ ሳይሆኑ ጥልቅ ፍልስፍናዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። ለመልሳቸው ፍለጋ ረጅም ርቀት ተጉዛለች። የፍልስፍናና የስነልቦና ጠበብቶች በቀጥታ በጉዳዮቹ ላይ ከሰጡት ማብራሪያ ልቃ በመጓዝ የታላቅ ገጣሚዎችን እና ፀሀፊዎችን ስራዎች በጥልቀት በመመርመር ትንታኔ አቅርባለች። እዚህ ላይ ነው ይዘቱ ከተራ ስሜት መግለጫ በላይ ጥልቅ የፍልስፍናና የስነልቦና ስራ ሆኖ የሚወጣው።

ደራሲዋ ለዚህ መፅሀፍ ብላ ሳይሆን፣ ባጠቃላይ በህይወቷ ኑሮንና ስብዕናን የተመለከቱ ስራዎች እንደሚስቧት ግልፅ አድርጋ አስቀምጣለች፤

“ኑሮንና ስብዕናን የተመለከቱ ሐሳቦች፣ ንግግሮችና መፅሐፎች ይማርኩኛል። ምንም እንኳን ከልጅነቴም ጀምሬ ነገሮችን ማሰላሰል፣ ጽሑፎችን ማንበብና አንዳንድ ሐሳቦችን መሞነጫጨር እወድ የነበረ ቢሆንም፣ ይበልጥ ራስን ወደሚያመለክቱ ሥራዎች የተሳብኩት ከዓመታት በፊት በሰማሁት አንድ የባሕር ማዶ ጽሑፍ ሲሆን፣ ይህም ኸርል ናይቲንጌል የተሰኘው አሜሪካዊው የሬድዮ ሰው ‘ታላቁ ምስጢር’ ብሎ ያሰፈረውን ጽሑፍ በሬድዮ ሲተረክ ከሰማሁ በኋላ ነበር” (ገፅ 31)።

ደራሲዋ ከሀገሯ ባህል በተጨማሪ የሌላ ሀገር ባህል ማየቷ በንባብ ካገኘችው ጋር ተዳምሮ ስለህይወት ላላት ግንዛቤ እና ትርጓሜ አስተዋፅኦ እንዳደረገ መረዳት ይቻላል። መፅሀፉ በይዘቱ የደራሲዋን ስሜት ከመግለፅ ባሻገር በአንባቢው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ታላቅ እንደሆነ መገመት ይቻላል። እኔስ ምን ያህል አንብቤያለሁ፣ ያነበብኩትንስ በምን ያህል ተገንዝቤያለሁ፣ እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እንዲጠይቅ የሚያደርግ ሀይል አለው።

መፅሀፉ በይዘቱ ከራስ ስሜት መገለጫነት አልፎ ሌላውን ሊኮረኩር፣ አንባቢ እራስን እንዲየጠቅ፣ እንዲያነብ፣ ያነበበውን በጥልቀት እንዲመረምር የሚያስገድድ ሀይል እንዲኖረው ያስቻለው የደራሲዋ የህይወት ልምድ ከጥልቅ ንባቧ ጋር ተዳምሮ ይመስለኛል።

ይዘቱ በራሱ የስነፅሁፍ ደራሲዎችን ብቻ ሳይሆን በትምህርት አለም የተሰማሩ ተመራማሪዎችን የፅሁፍን፣ የንባብን፣ እና የመጠየቅን ባህል ደረጃ/መመዘኛ ከፍ ያደረገባቸው ይመስለኛል።

የመፅሀፉ አቀራረብ

መፅሀፉ በርካታ አጫጭር ክፍሎች አሉት። እነዚህ ክፍሎች ከማጠራቸው የተነሳ ምዕራፍ ለማለት ቢከብዱም፣ እያንዳንዳቸው እንደ አጭር ልቦለድ እራሳቸውን ችለው የቆሙ በመሆናቸው እንደ ምዕራፍ መቁጠሩ አግባብ ይመስለኛል። ክፍሎቹ/ምዕራፎቹ በራሳቸው ምሉዕ በመሆናቸው ለተነባቢነቱ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል ማለት ስህተት አይሆንም።

የመፅሀፉ የሀሳብ ፍሰትና የቋንቋ ምጥቀት በጥቂት በሳል ደራሲዎች ስራ የሚታይ ነው። ደራሲዋ በመደበኛው ትምህርት መግፋቷም፣ ለዚህ የራሱን አስተዋፅኦ ያደረገ ይመስላል። የሌላ ሰው ሀሳቦች በተገቢው መልክ ተጠቅሰዋል። አንባቢን እንዳያደናቅፉ ከሌላ ቋናቋ የተጠቀሱ ግጥሞች እና አባባሎች በጥሩ ሁኔታ ወደአማርኛ ተመልሰውም ቀርበዋል።

ግጥምን መተርጎም ቀላል ባይሆንም፣ ከውጭ ቋንቋ ወደአማርኛ የተመለሱት፣ ከመነሻው በአማርኛ ታስበው የተፃፉ ያህል ሆነው ይሰማሉ። ይህ የሚታየው በጣም በበሰሉ የስነፅሁፍ ተሰጥኦ ባላቸው ተርጓሚዎች ዘንድ ብቻ ነው።

 አጠቃላይ አስተያየት

መፅሀፉ ተነባቢ ቢሆንም፣ ጥቃቅን የስርዐተ ነጥብ፣ የድግግሞሽ፣ እና የፊደል ግድፈቶች አሉበት። ለዳግም ህትመት ያግዛል በሚል የተወሰኑትን ለደራሲዋ በግል መልዕክት አጋርቻታለሁ። ለደራሲዋ ያጋራኋቸውን ከታች አቅርቤያቸዋለሁ።

1. ገፅ 13፣ አንቀፅ 1፣ መስመር 2፡ ያለተነገረ -> ያልተነገረ

2. ገፅ 41፣ ከታች አምስተኛው መስመር፡ ስለፈልገው

3. ገፆች 82 -84 “የልጅነት ...ይኖራል” የሚለው የተደገመ ነው።

4. ገፅ 96፣ ሁለተኛው አንቀፅ ላይ የቀረ ሀሳብ ያለ ይመስላል።

5. ገፅ 104፡ የመጀመሪያው አንቀፅ እና ቀጣዩ የሀሳብ ድግግም አለው። በመግቢያው አካባቢ ከቀረበው ተመሳሳይ ሀሳብ ጋር በንፅፅር ይመልከቱ።

6. ገፅ 130፣ ከታችኛው መስመር 2፡ ወደፊም -> ወደፊትም

7. ገፅ 150፣ የመጨረሻ አንቀፅ፣ መስመር 2፡ አንዳንዴለሰዎች -> አንዳንዴ ለሰዎች

8. ገፅ 162፣ መስመር 2፡ የሰፋ -> የተስፋ

7. ገፅ 162፣ መስመር 3፡ ዓለምአንድ -> ዓለምአንድ

በዚህ መፅሀፍ ላይ ምነው እንዲህ ባይሆን ያልኩት ርእሱን ብቻ ነው።

ምነው “እኔ” የሚል ነጠላ ተውላጠ ስም ከማድረግ ይልቅ ትንሽ አንባቢን የሚስብ አታደርገውም ነበር አልኩኝ። እኔን ስላልሳበ አንባቢን አይስብም ብዬ ማሰቤ ስህተት ሊሆን ይችላል። በእርግጠኝነት ምንም ስለዚህ መፅሀፍ ባልሰማ፣ ርእሱን አይቼ እንኳዋን ልገዛው ለማየት ጓጉቼ የማገላብጠውም አይመስለኝም። እንደእኔ እምነት ርዕስ ቢቻል ማራኪ፣ ባይሆን ጠቋሚ ቢሆን መልካም ነው። ርዕስ ያንድ ነገር እጅግ የተጨመቀ ጭብጥ/ይዘት ነው።
I.jpg
ምናልባት ደግሞ በተቃራኒ መፅሀፉን ቀረብ ብዬ እንዳየው ሊያደርገኝ የሚችል ነገር ካለ ከርዕሱ ይልቅ የሽፋን ስዕሉ ነው።

የሽፋን ስዕሉ እጅግ ጥበብ የተሞላው የመፅሀፉን ይዘት ነጋሪ ድንቅ ስራ ነው። ሰዓሊውን/ቀራፂውን እንዳናደንቅ በመፅሀፉ ውስጥ ስሙ አልተጠቀሰም። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። በስም መጠቀስ አልፈልግም ቢል/ብትልም እንኳ ይኸው ጉዳይ መገለፅ ነበረበት። ከፈጠራ ባለመብትነት አንፃርም—የኢትዮጵያን ባላውቅም—የምዕራቡ ሀገራት ህግ ይህ እንዲሆን ያስገድዳል።

ማጠቃለያ

“እኔ” እያንዳንዱ አረፍተነገር በጥሞና የሚነበብ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ለጥቅስ የሚበቁ በርካታ አባባሎችን አይቼበታለሁ። ይህን የመሰለ የመፃፍ ችሎታ ያለው ሰው፣ ይህን የመሰለ የማገናዘብ ችሎታ ያለው ሰው፣ እና ጥልቅ አንባቢ የሆነ ሰው፣ እንዴት ከራስ ጋር ግብግብ ሊፈጥር ቻለ የሚለው ከእኔ መረዳት አቅም በላይ ነው።

ደራሲዋ ስላሳለፈቺው ችግር ወይም ከራስ ጋር ፈተና ለዚች ልጅ ይህ አይገባትም ነበር ከማለት በዘለለ የምለው ነገር የለኝም።

በዚህ ስራ አሀዱ ብላለችና፣ ዋናው ነገር ከዚያ ሁሉ ፈተና አልፋ ብዙ ወደምታመርትበት ጉዞ መጀመሯ ነው።

 በዚህ መፅሀፍ ባጠቃላይ ደራሲዋ ሶስት ነገሮችን—(1) ልዩ የመፃፍ ችሎታ እንዳላት፣ (2) አንባቢ መሆኗንና፣ (3) ጥልቅ የማገናዘብ ችሎታ እንዳላት—መገንዘብ ችያለሁ። የእነዚህ ሶስት ነገሮች ባለቤት መሆን መታደል ነው።

ሚስጥረ በአንዲት ፅሁፍ ተሰጥኦን ከእውቀት ያዋሀደች ታላቅ ፀሀፊ/ባለ ቅኔ መሆኗን አስመስክራለች። አሁን ማኖ ነክታለች። ተሰጥኦዋን እያደነቁ የስነፅሁፍ እርካታ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ከእውቀቷም ለመጋራት አንባቢ ከደራሲዋ በቀጣይ ብዙ ስራ የሚጠብቅ ይመስለኛል። እኔ እጠብቃለሁ።

Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service