አቶ ተስፋዬና አቶ ደስታ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከዝቅተኛ ኑሮ ነዋሪ ቤተሰብ የወጡ ናቸው።
ወላጆቻቸው አቅሙ ኖሯቸው ቀልባቸውን ለገዛውና ክፍያን ግድ ለሚለው የሜዳ ቴኒስ ንዋይ ባያፈሱላቸውም ወንድማማቾቹ ወጣቶች ግና በኳስ አቀባይነት ለቴኒስ ሜዳ ቅርብ ሆነው ራኬት ለመጨበጥ ቆይተዋል።
ያም አስባብ ሆኖ ረጂ አግኝተው፤ ጥረቶቻቸውን አክለው ሕልማቸው ጉም መጨበጥ ሆኖ እንዳይቀር አድርገዋል።
ሩጫና እግር ኳስ በገነነባት አገር ፕሮፌሽናል የቴኒስ ተጫዋቾች ለመሆን በቅተውም ባሕር ማዶ ተሻግረው ተወዳድረዋል። የአገራቸውን ኢትዮጵያ ስምም በዓለም አቀፍ መድረክ አስጠርተዋል።
ሁለቱ ወንማማቾች ማንነታቸውን ቸል ያሉ፤ አስተዳደጋቸውን የዘነጉ አልነበሩም። ሲልም "መስጠትን የማያውቅ፤ መቀበል ማን አስተማረው?" እንዳይሆን የከእጅ ወደ አፍ ኑሮአቸው ወቅት በችሮታቸው በታደጓቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሳቢያ ለባለሙያተኛነት እንደበቁ ሁሉ፤ ውለታ የሚገባቸው፤ መቀበልን ብቻ ሳይሆን መስጠንም የሚያውቁ መሆናቸውን በግብር ሊያውሉ ተነሱ።

Tariku Tesfaye. Source: T.Tesfaye
የታሪኩ ተስፋዬና ደስታ ተስፋዬ የሕፃናት ትምህርት የቴኒስ ዕድገት ማሕበር በጎ አድራጎት ድርጅትን በጋራ መሠረቱ። የተረጂ ረጂ ሆኑ።
ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥም 300 ኢትዮጵያውያን ሕፃናትን ለቴኒስ ተጫዋችነት አብቅተዋል። በቀለም ትምህርትም ዕውቀት አስቀስመዋል።
በስልጠና ያፈሯቸው ወጣት ቴኒስ ተጫዋቾች በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች ተሰልፈው በርካታ ድሎችን በመንሳት የ487 ዋንጫ ባለቤቶች ለመሆን በቅተዋል።
ከ500 በላይ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን በአገር ውስጥ ውድድሮች ለአዲስ አበባ መስተዳድር፤ 68 የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።
እኒህን ሁሉ ውጤቶችን በአገር ቤትና በባሕር ማዶ ያስገኙና ወደፊትም ለላቀ ውጤት አልመው ያሉ ልጆች በተስፋ ዓለም እንዳይቀሩባቸውም የኢትዮጵያውያን ረድኤት እንሻለን ይላሉ።