ጉዞ ተውኔት
ተስፋዬ፤ በ "የውጫሌ ውል" ታሪካዊ ተውኔት ዝናና ሞገስ፤ "በአባትዬው" የማኅበራዊ ሕይወት ትወና ድምቀት ተወስኖ አልቀረም።
ከቶውንም ከተውኔት - ተውኔት፤ ከገፀ ባሕሪይ - ገፀ ባሕሪይ ለዋውጧል።
ሐሙስ፣ ኅምሌት፣ ባለ ካባና ባለ ዳባ፣ መስተዋት፣ የጨረቃ ቤት፣ ውድቅት፣ እርጉም ሐዋሪያ፣ የአመፃ ልጆችና ነፃ ወንጀሎችን በብሔራዊና የሀገር ፍቅር ቲአትር ቤት መድረኮች ተውኗል።
ለተስፋዬ ሀገር ድፍን ኢትዮጵያ ናትና ክፍለ አገራቷን አዳርሷል፤ የጥበብ ማዕዱን አቋድሷል።
ታላቁ የብዕር ዘንገኛ ሎሬየት ፀጋዬ ገብረመድኅን በፑሽኪን አንደበት "መድረክ መቅደስ ነው" እንደሚሉት ሁሉ፤ ለተስፋዬ ታዳሚ የተዋናይ ምስ ነው፤ እስትንፋስ ነው።
ለታዳሚም ተዋናይ የጥበብ ምትሃት ነው፤ እራሱን መድረክ ላይ የሚያይበት መስተዋት።
ያኔ የሀገር ቤት ታዳሚ ከምሳ በኋላ ለሚከፈት የመድረክ መጋረጃ የሚሰለፈው ማልዶ በቁርስ ሰዓት ነው።
ይፈላለጋሉ።
አንደኛው 'መድረክህ ከምን?' ሲል፤ ሌላኛው 'እንሆኝ' ብሎ ሊተውን።
የጥበብ ሰው ሃብቱ ሕዝብ፤ የሕዝብ ቅርሱ ሥነ ጥበብ እንደመሆናቸው።
ለጥበብ ሰው አንዱን የሕይወት መድረክ ከሌላው ማበላለጥ አዋኪ ነው።
"ኅምሌት" ግና ለተስፋዬ ግዝፈት አለው።
በሎሬየት ፀጋዬ ገብረመድኅን የብዕር ፍሰት ከልሳነ እንግልጣር በአማርኛ አንደበት ለመድረክ የበቃ፤ ለተዋናዮቹም የትምህርት ክፍለ ጊዜ ያህል ነበርና።

የደመቀባቸው የመድረኩ "የውጫሌ ውል"፣ የቴሌቪዥን ድራማው "ቃል" እና በጥይት እሩምታ ተደናግጦ አንደበቱ የታሰረበት የሀገር ፍቅር ቲአትሩ "መስተዋት" ትውስታዎች ዛሬም ድረስ በአዕምሮ ማኅደሩ ልዩ ሥፍራ ይዘው አሉ።
"ነፃ ወንጀሎች"ን ግና የተውኔት ዓለሙ መሠረት አድርጎ ያነሳል።
በጥበብ በረከትነቱ ብቻ ሳይሆን፤ ለ26 ዓመታት የፍቅር እስትንፋሱ ሆና ካለችው ዝነኛይቱ ድምፃዊት ብፅዓት ስዩም ጋር ሕይወቱ ለትስስሮሽ የበቃውም በ "ነፃ ወንጀለኞች" ተውኔት ጭምር ነውና።

በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን የሚያወጋውም ይህንኑ የፍቅር ሕይወት ጉዞ አስመልክቶ ይሆናል።







