"ለጥገኝነት ጥየቃ በተሰፋርንባት የአሮጌ ጀልባ ጉዞ ከሞት አፋፍ ላይ ደርሰን ነበር"ቤተልሔም ጥበቡ

Betelhem Tibebu Naru.jpg

Betelhem Tibebu, Nauru Detention Centre in 2013. Credit: B.Tibebu

ቤተልሔም ጥበቡ፤ ከጂግጂጋ ተነስታ፣ ከኢንዶኔዥያ በምታፈስ ትንሽዬ ጀልባ ውቅያኖስን አቋርጣ የአገረ አውስትራሊያን ምድር የረገጠችው አስከፊነቱ በብርቱ በሚነገርለት የናሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች ማቆያ ለሁለት ዓመታት በዕግት ቆይታ ነው። *አስጨናቂ ታሪክ ሲሰሙ መንፈስዎ የሚታወክ ከሆነ ይህን ቃለ ምልልስ አያድምጡ፤ ከታች ያለውንም ፅሑፍ አያንቡ።


አንኳሮች
  • ውልደትና ዕድገት
  • ከነፃ ትምህርት ወደ ስደት
  • የጥገኝነት ጠያቂና የስደተኛ ሕይወት ፈተናዎች
ውልደትና ዕድገት

ቤተልሔም ለወላጆቿ የበኩር ልጅ ናት።

ትውልድና ዕድገቷ ጂግጂጋ ነው። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም ያጠናቀቀችው እዚያው ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ትምህርቷን የጀመረችው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ነው።

በቀለም መግፋቷ በጅቷት ለነፃ ትምህርት ዕድል በር ከፈተላት። ለአዲስ የከፍተኛ ተቋም ዕውቀት ግብይትም ለአውስትራሊያ አጎራባች ለሆነችው አገረ ኢንዶኔዥያ አበቃት።

ይሁንና የኢንዶኔዥያ ቆይታዋ ከሳምንት ዕድሜ እልፍ አላለም።

የኢንዶኔዥያ አዲስ ወዳጆቿ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አውስትራሊያ በ"መርከብ" ለማቅናት መሰናዶ ላይ ነበሩና አብራቸው መሔድ ትሻ እንደሁ ጠየቋት።

አቅማማች። አሰበች። ወሰነች።

ከነፃ ትምህርት ወደ ስደት

ቤተልሔምና ጓደኞቿ ወደ አውስትራሊያ ለመዝለቅ ያሰቡት በመርከብ ቢሆንም ማጓጓዣቸው ሆና የቀረበችው ግና የጭነት መጠኗ ከ15 እስከ 20 የማያልፍ ትንሽ አሮጌ ጀልባ ነበረች።

64 ሆነው ተሳፈሩባት።

የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አውስትራሊያ በተንጣለለው ውቅያኖስ ላይ ቀዘፉ።

ከኢንዶኔዥያ ከመነሳታቸው በፊት በባለ ጀልባዎቹ ቃል እንደተገባላቸው ጉዞው በአንድ ቀን አላበቃም።

ስድስት ፈታኝ ቀናት ፈጅቷል።

ቤተልሔምና ጓደኞቿ ረሃብና ጥም ገጠማቸው። ጀልባይቱ መሰነጣጠቅ ጀመረች። ውኃ ወደ ጀልባይቱ መዝለቅ ያዘ። ትንሽዪት ጀልባ ሚዛኗን መሳት ቀጠለች።

የሞገድ ውዥቀትና የአሳ ነባሪዎች በዙሪያቸው መሽከርከር የሚገታ አልሆን አለ።

ሕይወትና ሞት በተፎካካሪነት ተደቀኑ።

ቤተልሔምን ጨምሮ የተሳፋሪዎቹ ልብና አዕምሮ በፍርሃት ተዋጡ።

የጀልባ ጉዞ በጀመሩ በአራተኛው ቀን ቤተልሔም መዳከም ጀመረች።

በአምስተኛው ቀን ዕይታዋ ወደ ብዥታ ተለወጠ። ሰመመን ውስጥ ገባች።

በስድስተኛው ቀን የምታስታውሰው ከውቅያኖስ ዳርቻ ነቅታ ቀና ስትል ከአውስትራሊያ ድንበር አስከባሪዎች የአንዱን የወታደር ጫማ ተመለከተች።

የድንበር አስከባሪው ኃይል ቤተልሔምን አክሎ 64ቱንም የጀልባ ተሳፋሪዎች ታድጎ በመርከብ ወደ ዳርዊን - አውስትራሊያ አግልሎ ማቆያ ማዕከል አደረሳቸው።

ከአምስት ቀናት የዳርዊን ቆይታ በኋላ አውስትራሊያ በጀልባ የባሕር በሯን አቋርጠው የሚመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከምድሯ አርቃ ለማቆየት አዲስ እያዘጋጀችው ወደ ነበረው የሰሎሞን ደሴቶች አካል ወደ ሆነችው የናሩ ደሴት ዕገታ ማዕከል እንዲወሰዱ ወሰነች።

ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ኖቬምበር 16 ቀን 2013 የናሩ ደሴትን ረገጡ።

ቤተልሔም የሙቀት መጠኗ ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ በሚያሻቅብባት ደሴት ብቸኛይቱ ኢትዮጵያዊት ሆና ለ15 ወራት ድንኳን ቤቷ ሆኖ ቆየች።

ለሁለት ዓመታት ጥገኝነት ጠያቂና ስደተኛ ሆና ከረመች።

በናሩ ደሴት የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ከእሷ በስተቀር ማንም ስላልነበረና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቷም አነስ ያለ በመሆኑ ከሌሎች ጋር ለመግባባት፣ የተላለፉ ውሳኔዎችን ለመረዳትና ችግሯን ለማጋራት ታውካ ነበር።

ምንም እንኳ ከ15 ወራት የጥገኝነት ጠያቂ ሕይወት በኋላ የስደተኝነት ዕውቅና ብታገኝም፤ ከደም ግፊት፣ የስኳር ሕመምና የመንፈስ ጭንቀት አልታደጋትም።

ሕመሟ ስለጠና ለአዕምሮና የውስጥ ሕመም ሕክምና ወደ አውስትራሊያ እንድትጓዝ ሐኪሞቿ ወሰኑ።

ወደ ብሪስበን አውስትራሊያ አቀናች።

የቤተልሔም ሕይወት ታሪክ መንፈስዎን ካወከ ወደ  Lifeline በ 13 11 14 ወይም ወደ Beyond Blue 1300 22 4636 ይደውሉ።

Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service