ብዕሊ አድሃኖም፤ ከአራዳ እስከ አውስትራሊያ

Biely Pic I.png

Engineer Biely Adhanom. Credit: SBS Amharic

"ልቤን ተከትዬ ጥፋት ሠራሁ" የምትለዋ ብዕሊ አድሃኖም ግለ ታሪክ መነሻ ከአዲስ አበባ ዕምብርት አራዳ ነው። አውስትራሊያን ሁለተኛ አገሯ ለማድረግ የበቃችው በለጋ ዕድሜዋ ፈታኙን የስደት ሕይወትን በአገረ ሱዳን ተቋቁማ ነው።


ብዕሊን ቀድመው የተጋፈጧት የሱዳን የስደት ሕይወት ተግዳሮቶች የአየር ንብረት ለውጥ፣ የባሕል፣ ቋንቋና የሴትነት የፆታ ፈተናዎች አንድ ላይ ተደራርበው ነው።

እምብዛም ሳትቆይ ሱዳንን ትታ ወደ ሊቢያ ለማቅናት ሞከረች።

ሳንካ ገጠማት። ቀረች።

'ቁርጥ ያጠግባል' እንዲሉ፤ ቀልቧን ሰብስባ ሱዳን ውስጥ ሥራ ፍለጋ ጀመረች።

በለስ ቀንቷት የቤት ሠራተኛነት ሥራ አገኘች።

የመጀመሪያ ሥራዋን የጀመረችበት ቤት ውስጥ ላሉ ወንዶች ዓይነ ገብ በመሆኗ ሊደፍሯት ሞከሩ።

በየዕለቱ በፀሐይ ጥልቀት ብርሃን በድቅድቅ ጨለማ ሲዋጥ፤ ከተቃራኒ ፆታ ጥቃት ራሷን ለመከላከል ከዕንቅልፍ ይልቅ ትንፋሽዋን ውጣ ነቅታ አያሌ ውድቅት ለሊቶችን አሳለፈች።

ጭንቀት በዛ፤ ሌላ ዕድል መጣ።

ብዕሊ ከሱዳን ወደ ባሕር ማዶ ስልክ መደወል ለሚሹ ስደተኞች ስልክ አስደዋይ ሆነች።

ዕፎይታ ተሰማት። በአካልም፤ በገቢም።

በስልክ ማስደወሉ እምብዛም ሳትቆይ ለአንድ የአካባቢው የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ኮሚሽን ባለስልጣን የቤት ሠራተኛነት ተቀጠረች።

ብዕሊና የቀጣሪዋ ሴት ልጅ የዕድሜ ዕኩዮች ናቸው።

ዕጣ ፈንታቸው ግና የተለያየ ነው።

አንዲቷ ተማሪ፤ ሌላይቱ የቤት ሠራተኛ።

ቀጣሪዋ ይህንኑ በንፅፅሮሽ አስተውሎ ያዝንላት ነበር።

ዕድል ሲገጥማት ከመማር ወደ ኋላ እንዳትል የቸራት ምክር በቀጣይ ሕይወቷ በጅቷታል።

የብዕሊ የሱዳን ሕይወት በሥራ ብቻ የታጠረ አልነበረም።

የሱዳን መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆና ሳለች ከአንድ ጎልማሳ ጋር ተዋወቀች።

አፍላ ስሜትና የደህንነት ዋስትና አስባብ ሆነው የፍቅር ሕይወት ጀመረች።

ወደደችው፤ ወደዳት፤ ተዋደዱ።

እ.አ.አ በ2003 አውስትራሊያ ከፍቅረኛዋ አስቀድማ ብዕሊን በስደተኝነት ተቀበለች።

አውሮፕላን ላይ ሳለች ሕመም ተሰማት።

የአውስትራሊያን ምድር እንደረገጠች ወደ ሆስፒታል ተወሰደች።

እርጉዝ መሆኗ ተነገራት።

ሐኪሞቿ ለአቅመ ሔዋን ስላልደረሰች ፅንሱን እንድታስወርድ አሳሰቧት።

ብዕሊ "እምቢኝ" አለች።

ሐኪሞችዋ ውሳኔዋን አከበሩ።

በአክስቷ ዘንድ ግና ይሁንታ ሳይቸረው ቀረ። ከቶውንም ብርቱ ቅሬታን አሳደረ።

አካላዊና ውስጣዊ ጭንቀት ተባባሰ።

ሆኖም አበረታች የመንፈሳዊ አባት ድጋፍ አላጣችም ነበር። ያ ውስጣዊ ፅንዓትንና መንፈሳዊ መረጋጋትን ፈጠረላት።

በሂደት ከአክስቷ ጋር ዕርቅ ቢወርድም፤ አብራ መኖርን ግና አልወደደችም።

በአክስቷ አጋዥነት የመንግሥት ቤት አገኘች። ከቤት ወጣች።

የመጀመሪያ ወንድ ልጇን እዚያ ሳለች ተገላገለች።

እንዲያ ሲሆን፤ የልጇ አባት ሱዳን ውስጥ የስደት ሕይወት እየገፋ ነበር።

ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ አውስትራሊያ መጥቶ ከብዕሊና ወንድ ልጁ ጋር ተቀላቀለ።

በአዋኪ ሁኔታም ቢሆን አዲስ ቤተሰባዊ ሕይወት ተጀመረ።
Biely Pic II.png
Engineer Biely Adhanom. Credit: SBS Amharic
ቤተሰባዊ ትስስሮሹ በብዕሊ ቤተሰብ ዘንድ ውዴታን ያሳደረ፤ ምርቃትን የተላበሰ አለመሆንና የጎሣ ዕይታንም ያጋመደ በመሆኑ አዋኪ ነበር።

ብዕሊ የልቧ መንገድ ለሁከት ወጀብ ቢዳርጋትም በአዕምሮዋ የሕይወት አቅጣጫዋን ለአክስቷ በካሣነት፤ ለእራሷም መመንደጊያነት እንዲሆናት ውጥን ዘረጋች።

ትምህርት ጀመረች።

ጅማሮዋ በመደበኛ ትምህርት የታገዘና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት የሰላ ባለመሆኑ አነሳሱ ከዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ሳይሆን ከምስክር ወረቀት ነበር።

ያም ለኑሮ ድጎማና ሲልም ለምሕንድስና ሙያ ጉዞ ጥርጊያ መንገድ ሆናት።




Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
ብዕሊ አድሃኖም፤ ከአራዳ እስከ አውስትራሊያ | SBS Amharic