ኢንጂነር ብዕሊ አድሃኖም፤ በቀዳሚው ክፍለ ዝግጅት በለጋ የወጣትነት ዘመን ከአዲስ አበባ - አራዳ ተንስታ፤ የሱዳንን አዋኪ የስደት ሕይወት ገፍታና ለአቅመ ሔዋን ሳትደርስ የመጀመሪያ ልጇን አገረ አውስትራሊያ ውስጥ ለመገላገል እንደምን እንደበቃች አውግታለች። በቀጣዩ ትረካዋ የአውስትራሊያ የሠፈራ ኑሮን ተቋቁማ እንደምን ለምሕንድስና ባለሙያነት እንደበቃች አንኳር የሕይወት ጉዞ ተግዳሮቶችና ስኬቶቿን በመንቀስ ታነሳለች።
ትምህርት
ብዕሊ አድሃኖም፤ የ11ኛ ክፍል ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደገመች።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዳለፈች ሁለተኛ ልጇን ፀነሰች።
የሁለት ልጆች እናት ሆነች።
አንድ ዓመት ቆይታ ለሊት እየሠራች፤ ቀን የቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪክ ምሕንድስና ተማሪ ሆነች።
ቤተሰባዊ ሕይወቷ ግና የተናጋ ነበር።
ፍቺና ምረቃ
ብዕሊ - የሁለት ልጆችና የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለች ትዳሯ ፈረሰ።
ትምህርቷም ተቋረጠ።
ጥቂት ቆይታ RMIT ዩኒቨርሲቲ ገባች።
ትምህርቷን ቀጠለች።
ወድቃ ተነሳች። አገገመች።
እምብዛም ሳትቆይ ከRMIT ወደ ቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ዞረች።
የአራተኛ ዓመት የመመረቂያ ፅሑፍ ለማቅረብ Qbot ሮቦት ላይ ጥናታዊ ግኝቷን ማስፈር የምረቃ ፕሮጄክት ድርሻዋ ሆነ።

የQbot ሮቦት ፕሮጄክት ሥራዋ ግና በጊዜ ተሻሚነቱና አዲስ ቴክኖሎጂነቱ ሳቢያ ሰፊ የምርምር ማጣቀሻ ፈልጎ አለማግኘት አዕምሮዋን በብርቱ ፈተነው።

ሆኖም በማለፊያ ፕሮፌሰሯ አይታክቴ ሙያዊ ድጋፍና አቅጣጫ አመላካችነት፤ በግሏ ያላሰለሰ ጥረት በክብር ማዕረግ ለምረቃ በቃች።






