የኔ ታሪክ፤ከያዮ እስከ አውስትራሊያ - ዶ/ር ሸሪፍ ሰዒድ

My Story: Dr Sherif Seid

Dr Sherif Seid Source: SBS Amharic

ዶ/ር ሸሪፍ ሰዒድ፤ የአውስትራሊያን ምድር ረግጠው፤ ዓለም አቀፍ ደረጃን ከጠበቀ ዩኒቨርሲቲዋ የPhD ካባ ከመደረባቸው ዓመታት ርቆ መነሻቸው የቀድሞዋ ኢሉባቦር የአሁኗ ኢሉ አባቦር ናት። ዕትብታቸው የተቀበረው ያዮ ቀዬ ውስጥ ነው።


ከያዮ ወደ አዲስ አበባ

 ለዶ/ር ሸሪፍ ያዮ መወለድ አስባቡ የአባታቸው ሰዒድ ወደ ያዮ ለንግድ ሥራ መሔድ ነው። ወላጆቻቸው ወሎዬዎች ናቸው። አፈር ፈጭተው፤ ጭቃ አቡክተው ያደጉትና ለአቅመ አዳምና ሔዋን ሲደርሱም ለጋብቻ የበቁት እዚያው ወሎ ነው።

 ወጣቱ ሸሪፍ በትምህርት ዘጠነኛ ክፍል እስከደረሰ ድረስ አፍላ ኮበሌ ሕይወቱን ያጣጣመው በትውልድ ቀዬው ያዮ ነው። ሸሪፍ ዘጠነኛ ክፍል ሳለ ግና የየካቲት 66’ቱ አብዮት ‘ፈነዳ’።

 ኢትዮጵያ የመጨረሻውን ንጉሠ ነገሥቷን ከሥልጣን አወረደች። የዘውዳዊው አገዛዝም አብሮ አከተመ። የሥርዓቱም መለያ ከዘውድ ወደ ማጭድና መዶሻ ምልክትነት ዞረ። ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ታወጀ። የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወዝ አደራዊ አምባገነን ሥርዓትን ለማቆም ቆርጦ ተነሳ።

 በወዝ አደራዊ አምባገነን ዓላሚ ሥርዓት ውስጥ ጥቂት የመሐለቅ ጥሪቶችን ቋጥረው የነበሩ በአድኃሪነት ተፈረጁ። ከእነዚያም ውስጥ አንዱ የሸሪፍ አባት ነጋዴው ሰዒድ ነበሩ። የአብዮቱ ሰይፍ ያዮ ላይ እንዳይቀላቸው ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ ዘለቁ።

 የያዮ ትውስታ

 ወጣቱ ሸሪፍና ቤተሰቡ አዲስ አበባን አዲሱ የመኖሪያ አድራሻቸው ቢያደርጉም እንኳ፤ ያዮን በትውስታ ማንሳታቸው አልቀረም።

ያዮ - ለወጣቱ ሸሪፍ የመድብለ ባሕልና ቋንቋ ምንጩ ናት። በጎሣ ያልተቧደኑ ጓደኞችን አፍርቶባታል። አማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎችን እኩል እየተናገረ አድጎባታል። ሙስሊም አባቱ ሰዒድ ከያዮ የያኔው ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪው መምሬ ምሕረቱ ጋር ጥብቅ ወዳጆች ነበሩ። አንዳቸው - አንዳቸው ቤት ሔደው የሚበሉ፤ የሚጠጡ።

 ዶ/ር ሸሪፍ ዛሬ ላይ ቆመው በምልሰት የያዮ ጓደኞቻቸውን ሲያስቡ በስማቸው እንጂ በዘራቸው ለይተው መጥራት አይችሉም። የአንድ ቀዬና አንድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ከማሰብ በስተቀር።

 አብዮትና እሥር ቤት

 የ66ቱ አብዮት መነሻ የዘርና የሃይማኖት መስመር የያዘ አልነበረምና በ1967 ወጣቱ ሸሪፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ወጣቶች ክንፍ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ወጣቶች ሊግ (ኢሕአወሊ) አባል ሆነ። በሥልጣን ላይ ያለው ጊዜያዊ ወታደራዊ  አስተዳደር ደርግ ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ወገነ። ሁለቱ የፖለቲካ ካምፖች በ“አብዮተኛነት” እና “ፀረ - አብዮተኛነት” እየተተቻቹ አንዳቸው በአንዱ ላይ አፈሙዝ ማነጣጠር ጀመሩ። ሲልም፤ በቀን ብርሃንና በድቅድቅ ጨለማ ሕይወቶችን ለመነጣጠቅ በቁ።

My Story: Dr Sherif Seid
EPRP Source: Courtesy of PD

የኢሕአወሊው አባል ሸሪፍም አንድ ቀን ከጓደኞቹ ጋር ሻይ ቤት ቁጭ እንዳለ ከተተኮሰበት ጥይት አመለጠ። ሌላም ጊዜ ለእሱ የታለመች ጥይት የቅርብ ዘመዱን ለጋ ሕይወት ቀጠፈች።

 ሸሪፍ - ምንም እንኳ ከሞት ቢያመልጥም፤ ዘብጥያ ከመውረድ ግና አላመለጠም። ለስድስት ዓመታት የፖለቲካ እስረኛነት ተዳርጓል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ያጠናቀቀው እዚያው እሥር ቤት ሆኖ ነው።

 ከእሥር እንደወጣም የእሥር ቤት ሕይወቱ የፍትሕ ጉድለት ተፅዕኖ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በሕግ ትምህርት እንዲመረቅ ብርቱ ምክንያት ሆኖታል።

 ሥራ፣ የነጻ ትምህርት ዕድልና ጋብቻ

 አቶ ሸሪፍ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ የውጭ ኢኮኖሚ ትብብር ጽሕፈት ቤት መሥሪያ ቤት ተመደቡ። እዚያ ሆነው ወደ ውጭ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች የነጻ ትምህርት ዕድል ማመልከቻዎቻቸውን መላክ ጀመሩ።

 ካመለከቱባቸው ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በአውስትራሊያ መዲና ካንብራ የሚገኘው የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ከሌሎች ቀድሞ ምላሽ ሰጣቸው። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መሥራት የሚያስችል የነጻ ትምህርት ዕድል አገኙ። ከወቅቱ ዕጮኛቸው ጋር ተጋብተው ወደ ካንብራ - አውስትራሊያ አቀኑ።

 አውስትራሊያ

 አውስትራሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባሕር ማዶ ተሻግረው  የውጭ አገር ሕይወይትን ያዩባት አገር ናት። ከጉልትና መርካቶ ገበያ አልፈው የሱፐር ማርኬት ግብይት ሲያደርጉ ግርታ አድሮባቸዋል። በነጻ የትምህርት ዕድላቸው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመሥራት የመጡበት የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ እንደዘመናይነቱ ኮምፒዩተር ቢያቀርብላቸውም አጠቃቀሙን ግና አላወቁበትም።

 የመጀመሪያ ሴት ልጃቸው ስትወለድም ባለቤታቸውን የሚያርስ ወዳጅ ዘመድ ከጎናቸው አልነበረም። ምግብ እንደምን ማብሰል በውል የማያውቁት ሸሪፍ ማዕድ ቤት ገብተው የሚቻላቸውን ጥረቶች አድርገዋል። አንዳንዴም አገር ቤት እየደወሉ ምን ማድረግ አንዳለባቸው መጠየቅ ግድ ነበር። ልጆቻቸው እያደጉ ሲሄዱም የኢትዮጵያንና የአውስትራሊያ ባሕሎችን አስታርቆ ማሳደጉ እንዲሁ ሌላ የወላጅነት ፈተና ሆኖባቸዋል።

 የአገር ቤት ናፍቆትና አውስትራሊያ የመቅረት ውሳኔ

 ኢትዮጵያውያን ከአገርና ሕዝባቸው ዕቅፍ ወጥተው ባሕር ማዶኛ ሲሆኑ፤ ከአገራቸው ናፍቆትና ፍቅር ጋር አብረው ውለው ማደራቸው እንግዳ ደራሽ ክስተት አይደለም። ከማንነታቸው ጋር የተዋሃደ ነው። የእነ ሸሪፍ ቤተሰብም እንዲያ ነውና በወር $1000 ድረስ ለስልክ ያወጡ ነበር።   

የኢሕዲሪ ሥርዓት ፈርሶ የኢሕአዴግ አገዛዝ ሲተካ እንዲያ የሚናፍቋትንና የሚያፈቅሯትን አገር ትተው አውስትራሊያ ለመቅረት ወሰኑ።

 ትምህርታቸውን ጨርሰው ‘በውጭ አገር የቀጥታ ሙዋዕለ ንዋይ ፍሰት ድንጋጌ’ በPhD ከተመረቁ በኋላ እስካሁን ድረስ በተለያዩ የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች እየሠሩ ይገኛሉ።’

My Story: Dr Sherif Seid
Dr Sherief Seid Source: Courtesy of SS

ዛሬና ነገ

 ዶ/ር ሸሪፍ ዛሬ ላይ ቆመው የኢትዮጵያን የለውጥ ሂደት አስመልክቶ ያላቸው አተያይ ተስፋና ሐዘኔታን ያዛነቀ ነው።

 ተስፋቸው ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ እንደምትወጣ፤ ሐዘኔታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ ተቋም ምሥረታ ትልማቸውን አጣቅሰው ለባሕር ማዶ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች ጥሪ ቢያቀርቡም በኃላፊነት ላይ ያሉ ረዳቶቻቸው ግና ሙያዊ እገዛዎችን ለማስተናገድ ፈቃደኝነት የጎደላቸው ሆነው ያገኟቸው መሆኑ ነው።

 እንዲያም ሆኖ ግና ተስፋቸው የተሟጠጠ አይደለም። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ አገር ቤት ተመልሰው በዩኒቨርሲቲ መምሕርነት፣ በአማካሪነት፣ በምርምር ሥራዎች ወይም በሥልጠና መስክ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ማገልገል ይሻሉ።  


Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service